በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞትን የምንፈራው ለምንድን ነው?

ሞትን የምንፈራው ለምንድን ነው?

ሞትን የምንፈራው ለምንድን ነው?

“ሞት የሕይወት ፍጻሜ ስለሆነ ከምንም ነገር በላይ አስከፊ ነው።”—አርስቶትል

በእኩዮቿ ዘንድ ለሃይማኖቷ ያደረችና እውነተኛ አማኝ እንደሆነች ተደርጋ ትታይ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች “የቤተ ክርስቲያኗ ዓምድ” ብለው ይጠሯታል። ሞት በእርግጥ የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን ከሞት በኋላ ወዳለው ሕይወት መሸጋገሪያ እንደሆነ ተምራ ነበር። ሆኖም የምትሞትበት ጊዜ የቀረበ መስሎ ሲሰማት በፍርሃት ተዋጠች። ይህች ሴት በአእምሮዋ ውስጥ የሚጉላላው ጥርጣሬ ስላስጨነቃት መንፈሳዊ አማካሪዋን እንዲህ በማለት ጠየቀቻቸው:- “[በሞት ጊዜ ስለሚሆነው ነገር የሚናገሩ] በጣም ብዙ [እምነቶች] አሉ፤ ትክክለኛው የቱ እንደሆነ እንዴት ያውቃሉ?”

ሁሉም ሃይማኖቶችና ማኅበረሰቦች ማለት ይቻላል፣ ሰዎች ከሞቱ በኋላ መኖራቸውን ይቀጥላሉ ወይም እንደገና መኖር ይጀምራሉ የሚለውን ሐሳብ ይቀበላሉ። በዚህ ረገድ ካሉት ብዙ እምነቶች መካከል ትክክለኛው የቱ ነው? ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ሕይወት መኖሩን እስከጭራሹ ይጠራጠራሉ። አንተስ? ሰው ከሞተ በኋላም ሕይወቱ እንደሚቀጥል ተምረሃል? በዚህ ትምህርት ታምናለህ? ሞትንስ ትፈራለህ?

ከሕልውና ውጭ መሆንን መፍራት

በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ከሞት ፍርሃት ጋር የተያያዙ ብዙ መጻሕፍትና ሳይንሳዊ ዘገባዎች ተጽፈዋል። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ሞት አለማሰቡን ይመርጣሉ። ይሁን እንጂ ሞት የማይቀር ነገር መሆኑ ውሎ አድሮ ስለ ሞት እንድናስብ ያስገድደናል። የሰው ሕይወት እንደ ተሰባሪ ዕቃ ነው፤ በእያንዳንዱ ቀን በአማካይ ከ160,000 በላይ ሰዎች ይሞታሉ! እገሌ ከገሌ ሳይባል ሁሉም ሰው ሟች ሲሆን ይህ ሐቅ ደግሞ ብዙዎችን ያስፈራቸዋል።

ምሑራን የሞትን ፍርሃት በተለያዩ ክፍሎች ይመድቡታል። ከእነዚህም መካከል ሥቃይን መፍራት፣ የማያውቁትን ነገር መፍራት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትን መፍራት እንዲሁም የአንድ ሰው ሞት በቤተሰቦቹና በወዳጆቹ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መፍራት ይገኙበታል።

ከእነዚህ ጭንቀቶች መካከል ዋነኛውን ቦታ የሚይዘው ከሕልውና ውጭ መሆንን መፍራት ነው። ብዙ ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ሞት የሕይወት ፍጻሜ ነው የሚለው ሐሳብ ያስፈራቸዋል። ሳይንስ ደግሞ ይህን ፍርሃት ያባብሰዋል። በአሁኑ ጊዜ የሰው አካል የሚያከናውናቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ሳይንስ መግለጽ ችሏል። ሆኖም የትኛውም የባዮሎጂ፣ የፊዚክስ ወይም የኬሚስትሪ ሊቅ ሰው ሲሞት በሕይወት የምትቀጥል በዓይን የማትታይ አካል በውስጣችን እንዳለች የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘም። በመሆኑም ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ሞት በአካላችን ላይ የሚከናወን ለውጥ እንደሆነ ከመግለጽ ያለፈ ማብራሪያ አይሰጡም።

እንግዲያውስ ከሞት በኋላ ሕይወት መኖሩን በጥልቅ እንደሚያምኑ የሚገልጹ ብዙ ሰዎች ሞተው ከሕልውና ውጭ መሆንን መፍራታቸው ምንም አያስደንቅም። የጥንቱ ንጉሥ ሰሎሞን በጽሑፎቹ ላይ ሞት የሰው ልጅ መጨረሻ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ይህም አንዳንድ ሰዎችን ያስፈራቸው ይሆናል።

መጨረሻችን “ዐፈር” መሆን ነው?

የ3,000 ዓመታት ዕድሜ ባስቆጠረው የመክብብ መጽሐፍ ላይ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ መታሰቢያቸው ይረሳል፤ ምንም ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል።” አክሎም “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና” ብሏል።—መክብብ 9:5, 6, 10

ሰሎሞን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ብሏል:- “የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው፤ አንዱ እንደሚሞት፣ ሌላውም እንዲሁ ይሞታል። . . . ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ . . . ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ሁሉም ከዐፈር እንደ ሆኑ፣ ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ።”—መክብብ 3:19, 20

ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ የጻፈው ንጉሥ ሰሎሞን ቢሆንም ይህንን የጻፈው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ከመሆኑም በላይ ጥቅሶቹም የአምላክ ቃል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ናቸው። እነዚህም ሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች በርካታ ጥቅሶች በውስጣችን ያለች አንዲት ነገር ከሞት ተርፋ በሌላ መልክ ትኖራለች የሚለውን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እምነት አይደግፉም። (ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19፤ ሕዝቅኤል 18:4) ይህ ሲባል ታዲያ አምላክ የሰው ሁሉ መጨረሻ “ዐፈር” ወይም ከሕልውና ውጭ መሆን ነው እያለን ነው ማለት ነው? በጭራሽ!

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከሞት የምትተርፍ አካል እንዳለቻቸው ባያስተምርም የሞቱ ሰዎች የማያሻማ ተስፋ እንዳላቸው ይገልጻል። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ሞት የሰው ሕይወት መጨረሻ ነው ብለህ መፍራት የሌለብህ ለምን እንደሆነ ያብራራል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የማያመልጡት ጠላት

ሞት የሰው ልጆች ጠላት እየተባለ ይጠራል። በእርግጥም እውነተኛ ጠላታችን መሆኑ አሌ የሚባል ነገር አይደለም። በየዓመቱ 59 ሚሊዮን ያህል ሰዎች እንደሚሞቱ የሚገመት ሲሆን ይህም በእያንዳንዱ ሴኮንድ በአማካይ 2 ሰው ይሞታል ማለት ነው። እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ስለ ሞት የሚገልጹ አኃዛዊ መረጃዎች ተመልከት።

▪ በእያንዳንዱ 102 ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው በጦርነት ምክንያት ይሞታል።

▪ በእያንዳንዱ 61 ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው ይገደላል።

▪ በእያንዳንዱ 39 ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው ራሱን ይገድላል።

▪ በእያንዳንዱ 26 ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው በመኪና አደጋ ምክንያት ይሞታል።

▪ በእያንዳንዱ ሦስት ሴኮንድ ውስጥ አንድ ሰው ከረሀብ ጋር በተያያዘ ምክንያት ይሞታል።

▪ በእያንዳንዱ ሦስት ሴኮንድ ውስጥ አምስት ዓመት ያልሞላው አንድ ሕፃን ይሞታል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከንቱ ልፋት

ኅዳር 9, 1949 ጄምስ ኪድ የተባሉ መዳብ ቆፍሮ በማውጣት ሥራ ላይ የተሠማሩ የ70 ዓመት አዛውንት በዩናይትድ ስቴትስ፣ አሪዞና ተራሮች ላይ በመሥራት ላይ እያሉ ጠፉ። አስከሬናቸው ባለመገኘቱ የአካባቢው ፍርድ ቤት እንደሞቱ ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ከገለጸ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እኚህ ሰው በእርሳስ የጻፉት ኑዛዜ እንዲሁም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ያለው የአክሲዮን ሰነድ ተገኘ። ኪድ ገንዘባቸው “ሰው ሲሞት ከአካሉ ተለይታ የምትሄድ ነፍስ በውስጡ መኖሯን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ” ለማግኘት ምርምር ለማካሄድ እንዲውል እንደሚፈልጉ በኑዛዜያቸው ላይ በግልጽ አስፍረዋል።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከ100 በላይ ተመራማሪዎችና የሳይንስ ሊቃውንት ነን ባዮች ገንዘቡ እንዲሰጣቸው አመለከቱ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ለብዙ ወራት የታየ ሲሆን በዓይን የማትታይ ነፍስ መኖሯን የሚገልጹ በሺህ የሚቆጠሩ ሐሳቦች ተደመጡ። በመጨረሻም ዳኛው ገንዘቡ ለሁለት ስመ ጥር የምርምር ድርጅቶች እንዲሰጥ ወሰኑ። ይህ ከሆነ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ቢያልፍም እነዚያ ተመራማሪዎች “ሰው ሲሞት ከአካሉ ተለይታ የምትሄድ ነፍስ በውስጡ መኖሯን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ” እስካሁን ድረስ አላገኙም።