በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው?

ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው?

 ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው?

ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ነገር የሚነሳውን ጥያቄ ያህል አደናጋሪና ዘመናት ያስቆጠረ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ያለ አይመስልም። በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የኖሩ አስተዋይ ሰዎች ይህንኑ ጥያቄ ሲያወጡና ሲያወርዱ ኖረዋል። ይሁን እንጂ የሰዎች ፍልስፍናና ሳይንሳዊ ምርምር ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ጽንሰ ሐሳቦችንና አፈ ታሪኮችን ከመፍጠር ያለፈ የፈየደው ነገር የለም።

ይህን ርዕስ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ትምህርትስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንድ ሰዎች ሞትንና ከዚያ በኋላ ያለውን ሕይወት በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርትም ቢሆን ግራ የሚያጋባ ነው ብለው ይከራከሩ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ግራ መጋባቱ የተፈጠረው በርካታ ሃይማኖቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ ትምህርት ከተሳሳተ እምነትና አፈ ታሪክ ጋር በመቀላቀል ስላደፈረሱት ነው። ወጎችንና አፈ ታሪኮችን ገሸሽ አድርገህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ብቻ ብትመረምር ትምህርቱ ትርጉም ያለውና ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ትገነዘባለህ።

ወደ ሕልውና ከመምጣትህ በፊት

ለምሳሌ ያህል፣ በፊተኛው ርዕሰ ትምህርት ላይ የቀረቡትን ንጉሥ ሰሎሞን የጻፋቸውን ሁለት ጥቅሶች እንመልከት። ጥቅሶቹ፣ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ከሞቱ በኋላ ምንም እንደማያውቁ ይናገራሉ። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰው ሲሞት ምንም ዓይነት ሥራ አይሠራም፣ ራሱን አያውቅም፣ ስሜት አይኖረውም እንዲሁም ምንም ማሰብ አይችልም።—መክብብ 9:5, 6, 10

ይህ ለማመን አዳጋች ይሆንብሃል? እስቲ የሚከተለውን አስብ:- አንድ ሰው ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር? ከወላጆችህ የተገኙት ጥቃቅን ሴሎች ተዋህደው አንተን ከማስገኘታቸው በፊት የት ነበርክ? ሰው ሲሞት መኖሯን የምትቀጥል በዓይን የማትታይ አካል በውስጡ ካለች ይህች ነገር ግለሰቡ ከመጸነሱ በፊት የት ነበረች? ሰው ሆነህ ከመፈጠርህ በፊት ሕልውና ስላልነበረህ ከመጸነስህ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ምንም ትዝ የሚልህ ነገር የለም። እውነታው አጭርና ግልጽ ነው፤ ከመጸነስህ በፊት ሕልውና አልነበረህም።

ስለዚህ በምንሞትበት ጊዜ፣ ወደ ሕልውና ከመምጣታችን በፊት እንደነበረው ምንም ወደማናውቅበት ሁኔታ እንመለሳለን ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። አዳም ባመጸ ጊዜ አምላክ “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሎት ነበር፤ ይህ አባባል ስንሞት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንሆን ለመረዳት ያስችለናል። (ዘፍጥረት 3:19) በዚህ ረገድ ሰዎች ከእንስሳት የተለዩ አይደሉም።  ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም” ይላል።—መክብብ 3:19, 20

ይህ ሲባል ታዲያ የሰው ልጆች ለጥቂት አሥርተ ዓመታት በሕይወት ከኖሩ በኋላ ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ሆነው ይቀራሉ ማለት ነው? ወይስ ሙታን ተስፋ ይኖራቸው ይሆን? ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት።

አብሮን የተወለደ የመኖር ፍላጎት

ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ስለ ሞት ማውራት ደስ አይለውም። አብዛኞቹ ሰዎች በተለይ ስለ ራሳቸው ሞት ማውራት ሌላው ቀርቶ ማሰብ እንኳ አይፈልጉም። በሌላ በኩል ግን በቴሌቪዥንና በፊልሞች ላይ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲሞቱ የሚያሳዩ ትእይንቶችን ይመለከታሉ፤ ወይም በገሃዱ ዓለም ስለሞቱ ሰዎች የሚገልጹ በርከት ያሉ ታሪኮችና ምስሎች በመገናኛ ብዙኃን ይቀርቡላቸዋል።

በመሆኑም የማያውቁት ሰው መሞቱ የተለመደ የሕይወት ገጽታ መስሎ ሊታይ ይችላል። የምንወደውን ሰው በሞት ስለ ማጣት ወይም ስለ ራሳችን ሞት ስናስብ ግን ሞት የተለመደ የሕይወት ክፍል እንደሆነ አድርገን ልንቀበለው አንችልም። ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች አብሯቸው የተወለደ የመኖር ፍላጎት ስላላቸው ነው። ሁላችንም ስለ ጊዜና ስለ ዘላለማዊነት የመረዳት ችሎታ አለን። ንጉሥ ሰሎሞን፣ አምላክ “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ” በማለት ጽፏል። (መክብብ 3:11) ሁኔታዎች ጥሩ እስከሆኑ ድረስ ምንጊዜም ለዘላለም መኖር እንፈልጋለን። ቀነ ገደብ የሌለው ሕይወት እንዲኖረን እንሻለን። እንስሳት እንዲህ ዓይነት ምኞት እንዳላቸው የሚያመለክት ምንም ፍንጭ የለም። እንስሳት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ዓይነት ግንዛቤ የላቸውም።

ሰዎች ይህ ነው የማይባል ችሎታ አላቸው

ሰዎች ለዘላለም የመኖር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በሥራ አስጠምደው ውጤት ያለው ሥራ እየሠሩ ለዘላለም የመኖር ችሎታም አላቸው። የሰው የመማር ችሎታ ገደብ ያለው አይመስልም። በውስብስብነቱና ከማንኛውም ሁኔታ ጋር በቀላሉ በመላመድ ችሎታው ረገድ ከሰው አንጎል ጋር የሚተካከል ምንም ነገር እንደሌለ ይነገራል። እኛ ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ ማመዛዘንና ረቂቅ ጽንሰ ሐሳቦችን መረዳት የሚችል የፈጠራ ችሎታ ያለው አእምሮ አለን። የሳይንስ ሊቃውንት የሰው አንጎል ያለውን ችሎታ በመረዳት ረገድ ገና ብዙ ይቀራቸዋል።

ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድም ከዚህ ችሎታችን የምናጣው ጥቂቱን ብቻ ነው። ስለ ሥርዓተ ነርቭ የሚያጠኑ ሊቃውንት በቅርቡ እንደደረሱበት አብዛኛው የአእምሮ ሥራ በእርጅና ምክንያት ምንም ጉዳት አይደርስበትም። በፍራንክሊን ኢንስቲትዩት ውስጥ ሴንተር ፎር ኢኖቬሽን ኢን ሳይንስ ለርኒንግ በሚባለው ክፍል የሚሠሩ ተመራማሪዎች እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “የሰው አንጎል ያለማቋረጥ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን ማላመድና አዳዲስ የነርቭ ቅጥያዎችን መሥራት ይችላል። በእርጅና ዘመንም እንኳ አእምሯችን አዳዲስ የነርቭ ሕዋሶች እንዲያድጉ ማድረግ ይችላል። በአብዛኛው በጣም ከባድ የሆነ የአእምሮ ችሎታ መቀነስ የሚከሰተው በበሽታ ምክንያት ሲሆን ከእርጅና ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የማስታወስ ችሎታ ማጣት ወይም የቅልጥፍና መቀነስ ብዙውን ጊዜ መንስኤ የሚሆኑት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንዲሁም አእምሮን አለማሠራትና ተነሳሽነት ማጣት ናቸው።”

በሌላ አነጋገር አእምሯችንን እንዲማር ካደረግነውና በበሽታ ካልተጠቃ ለዘላለም እየሠራ ሊቀጥል ይችላል። “ዲ ኤን ኤ የተዋቀረበትን መንገድ ካገኙት ጠበብት አንዱ የሆኑት ጄምስ ዋትሰን የተባሉ የሞለኪውላር ባዮሎጂ ሊቅ ‘አንጎል በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ እስካሁን ከደረስንባቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ውስብስብ ነው’ ብለዋል።” በነርቭ ጥናት ሊቅ የሆኑት ጀራልድ ኤድልማን ያዘጋጁት መጽሐፍ እንደሚገልጸው የክብሪት ራስ የሚያህል መጠን ያለው የአንጎል ክፍል “አንድ ቢሊዮን ያህል እርስ በርስ የተያያዙ ነርቮች ያሉት ሲሆን እነዚህ ነርቮች ደግሞ በአኃዝ ለማስቀመጥ በሚያስቸግር መንገድ፣ ይኸውም አሥር ቁጥርን ጽፎ ከጎኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜሮዎችን መደርደር የሚጠይቅ ጊዜ ያህል እርስ በርስ ሊያያዙ ይችላሉ።”

ታዲያ ሰዎች ይህን ያህል ችሎታ ታድለው ሳለ ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ብቻ መኖራቸው ምክንያታዊ ነው? ይህ በርካታ የዕቃ ማመላለሻ ፉርጎዎች ያሉት ባቡር ላይ ትንሽ አሸዋ ጭኖ ጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ብቻ ከተጓዘ በኋላ እንዲቆም የማድረግን ያህል ምክንያተ ቢስ ነው! ታዲያ የሰው  ልጅ ይህን ያህል ከፍተኛ የፈጠራና የመማር ችሎታ ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? ከእንስሳት በተለየ መልኩ ሰዎች ፈጽሞ እንዳይሞቱ ማለትም ለዘላለም እንዲኖሩ ስለተፈጠሩ ይሆን?

የሕይወት ፈጣሪ የሰጠው ተስፋ

አብሮን የተፈጠረ የመኖር ፍላጎት እንዲሁም ከፍተኛ የመማር ችሎታ ያለን መሆኑ ወደ አንድ ምክንያታዊ ድምዳሜ ያደርሰናል:- ሰዎች የተፈጠሩት ከ70 ወይም 80 ዓመታት እጅግ ለሚበልጥ ረዥም ጊዜ እንዲኖሩ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ሌላ መደምደሚያ ይመራናል:- አንድ ንድፍ አውጪ፣ ፈጣሪ እንዲሁም አምላክ አለ። የግዑዙ አጽናፈ ዓለም የማይለዋወጡ ሕጎችም ሆኑ በምድር ላይ ያሉት ሕያዋን ነገሮች ያላቸው ውስብስብ ንድፍ፣ ፈጣሪ መኖሩን እንድናምን የሚያደርጉ ጠንካራ ማስረጃ ናቸው።

ታዲያ አምላክ ለዘላለም መኖር እንድንችል አድርጎ ከፈጠረን የምንሞተው ለምንድን ነው? ከሞትን በኋላስ ምን እንሆናለን? አምላክ ሙታንን ወደ ሕይወት የመመለስ ዓላማ አለው? ጥበበኛና ኃያል የሆነ አምላክ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው፤ ደግሞም መልስ ሰጥቷል። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ የሰው ልጆች እንዲሞቱ አልነበረም። ሞት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ሁኔታ፣ አምላክ ከመጀመሪያው የሰው ልጆች እንዲሞቱ አስቦ እንዳልነበረ ያመለክታል። በዘፍጥረት ላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አምላክ፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲሁም ታማኝነት እንዲያሳዩ አጋጣሚ ለመስጠት ሲል አንድ ቀላል ፈተና እንደሰጣቸው ይገልጻል። ፈተናው ከአንድ የተወሰነ ዛፍ እንዳይበሉ የሚከለክል ነበር። አምላክ አዳምን “ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አዳምና ሔዋን የሚሞቱት በአምላክ ላይ ካመጹና በፈተናው ከወደቁ ብቻ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚገልጸው አዳምና ሔዋን ለአምላክ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሞቱ። በዚህ መንገድ ሰብዓዊው ቤተሰብ ፍጽምና ለጎደለው ሕይወትና ለሞት ተጋለጠ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር ያመሳስለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሞት እንቅልፍ ስለመተኛት’ ይናገራል። (መዝሙር 13:3) ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ በፊት ለሐዋርያቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ ያደረገው ይህንኑ ነበር! “የሞተውም  ሰው [አልዓዛር]” ኢየሱስ ሲጠራው እንደገና ሙሉ በሙሉ ሕያው ሆኖ ‘ከመቃብር እንደወጣ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል!—ዮሐንስ 11:11, 38-44

ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ያመሳሰለው ለምን ነበር? ምክንያቱም እንቅልፍ የወሰደው ሰው እንቅስቃሴ አልባ ስለሆነ ነው። አንድ ሰው ኃይለኛ እንቅልፍ ከወሰደው በዙሪያው ስለሚከናወነው ነገር ወይም ስለ ጊዜ ማለፍ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ምንም ዓይነት ሕመም ወይም ሥቃይ አይሰማውም። በተመሳሳይም ሰው ሲሞት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አያደርግም ወይም ምንም አያውቅም። ይሁን እንጂ ንጽጽሩ በዚህ አያበቃም። አንድ ሰው ሲተኛ እንደሚነቃ ይታወቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሙታን የሚሰጠው ተስፋም ይኸው ነው።

ፈጣሪ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል:- “ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ?” (ሆሴዕ 13:14) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ደግሞ አምላክ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 25:8) ይህ ሙታንን ወደ ሕይወት የመመለስ ሂደት ትንሣኤ ተብሎ ይጠራል።

ከሞት የሚነሱ ሰዎች የሚኖሩት የት ነው? ከላይ እንደተመለከትነው የሰው ልጅ ለዘላለም የመኖር ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለው። አንተ ለዘላለም መኖር የምትፈልገው የት ነው? አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት ከሞትክ በኋላ በጽንፈ ዓለም ውስጥ በማንኛውም ቦታ የሚገኝ ኃይል ሆነህ መኖር ትቀጥላለህ ብትባል ደስ ይልሃል? ወይም ደግሞ ከመሞትህ በፊት የነበረህን ማንነትህን ማስታወስ በማትችልበት ሁኔታ ሌላ ሰው ሆነህ ለመኖር ትመኛለህ? እንስሳ ወይም ዛፍ ሆነህ እንደገና በሕይወት መኖር ትፈልጋለህ? ምርጫ ቢሰጥህ አሁን ሰው ሆነህ በምትኖርበት ጊዜ የለመድካቸውና የምትደሰትባቸው ነገሮች በሌሉበት ዓለም ላይ መኖር ትፈልግ ነበር?

በምድር ላይ በገነት ብትኖር በጣም ደስ እንደሚልህ ጥርጥር የለውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ተስፋም ይኸው ነው፤ እዚችው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይቻላል። አምላክ ምድርን የፈጠራት ለዚሁ ዓላማ ማለትም እሱን የሚወዱትና የሚያገለግሉት ሰዎች ለዘላለም እየተደሰቱ እንዲኖሩባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው ለዚህ ነው።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18፤ 65:21-24

ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? ሞት ከእንቅልፍ ጋር መመሳሰሉ ብዙውን ጊዜ ትንሣኤ የሚከናወነው ግለሰቡ እንደሞተ ወዲያው አለመሆኑን ያመለክታል። በሞትና በትንሣኤ መካከል “የእንቅልፍ” ወቅት ይኖራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር።  ከዚያም ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ “እድሳቴ እስከሚመጣ ድረስ፣ . . . [በመቃብር ውስጥ] እታገሣለሁ። ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ” ብሏል። (ኢዮብ 14:14, 15) ያ ጊዜ ደርሶ ሙታን ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ሲገናኙ ማየት እንዴት እንደሚያስደስት መገመት ትችላለህ!

በፍርሃት መዋጥ አያስፈልግም

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ የሞትን ፍርሃት ሙሉ በሙሉ እንደማያስወግድ አይካድም። አንዳንድ ጊዜ ከሞት በፊት የሚመጣውን ሕመምና ሥቃይ መፍራት ተፈጥሯዊ ነው። የምትወደውን ሰው በሞት ማጣትም የሚያስፈራ ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። የአንተ መሞት በምትወዳቸው ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መፍራትም ያለ ነገር ነው።

ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል እንድናውቅ በማድረግ ስለ ሞት በማሰብ በፍርሃት እንዳንዋጥ ይረዳናል። ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት አጋንንት በሚያቃጥል ሲኦል ውስጥ ያሠቃዩናል ብለን መፍራት አያስፈልገንም። እንዲሁም ነፍስ ጨለማ በሆነ የሙታን ዓለም ውስጥ ለዘላለም ስትንከራተት ትኖራለች በሚል ፍርሃት አንዋጥም። በተጨማሪም ከሞትክ ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ሆነህ እንደምትቀር በማሰብ መፍራት አያስፈልግህም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ ወሰን የሌለው የማስታወስ ችሎታ ስላለውና እሱ የሚያስባቸውን ሰዎች በሙሉ እዚህ ምድር ላይ እንዲኖሩ ወደ ሕይወት ለመመለስ ቃል ስለገባ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ዋስትና ይሰጣል:- “አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው፤ ከሞት ማምለጥ የሚቻለውም በጌታ በእግዚአብሔር ነው።”—መዝሙር 68:20

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”—ዘፍጥረት 3:19

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ።”—መክብብ 3:11

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ስለ ሞት ያሉህ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ያገኛሉ

እርግጥ ሞትንና ትንሣኤን በሚመለከት በዚህ እትም ላይ በቀረቡት ርዕሶች ያልተዳሰሱ ጥያቄዎች አሉ። ብዙ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በማጥናት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አግኝተዋል። አንተም እንዲሁ እንድታደርግ እናበረታታሃለን። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና መልስ ከምታገኝላቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል:-

▪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት “ገሃነም” እና ‘የእሳት ባሕር’ የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

▪ እሳታማ ሲኦል ከሌለ ክፉ ሰዎች የሚቀጡት እንዴት ነው?

▪ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰው ሲሞት መንፈስ ከሰውነቱ ይወጣል። ታዲያ ይህ መንፈስ ምንድን ነው?

▪ ከሙታን ጋር የተነጋገሩ ሰዎች እንዳሉ የሚገልጽ ብዙ ወሬ የሚሰማው ለምንድን ነው?

▪ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “ነፍስ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?

▪ የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚኖሩት መቼ ነው?

▪ በሕይወት ዘመናቸው ምንም ይሥሩ ምን የሞቱ ሰዎች በሙሉ ይነሣሉ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ ግልጽና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ እንዴት ማግኘት እንደምትችል ለማወቅ እባክህ የዚህን መጽሔት የኋላ ሽፋን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አልዓዛርን ‘ከእንቅልፉ እንደሚያስነሳው’ ተናግሯል

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት ሲነሱ የሚኖረውን ደስታ እስቲ አስበው!