በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 49

ትንሣኤ—አስተማማኝ ተስፋ!

ትንሣኤ—አስተማማኝ ተስፋ!

“[ሰዎች] ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።”​—ሥራ 24:15

መዝሙር 151 አምላክ ይጣራል

ማስተዋወቂያ *

1-2. የይሖዋ አገልጋዮች ምን ግሩም ተስፋ አላቸው?

ተስፋ በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። አንዳንዶች የሰመረ ትዳር እንደሚመሠርቱ፣ ልጆቻቸው ጤናማ እንደሚሆኑ ወይም ከከባድ ሕመም እንደሚድኑ ተስፋ ያደርጋሉ። እኛ ክርስቲያኖችም እነዚህኑ ነገሮች ተስፋ እናደርግ ይሆናል። ሆኖም ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ተስፋ ከእነዚህ ነገሮች በእጅጉ የላቀ ነው፤ የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ እንዲሁም በሞት ያጣናቸው ሰዎች ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ እናደርጋለን።

2 ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 24:15) ስለ ትንሣኤ ተስፋ የተናገረው የመጀመሪያው ሰው ጳውሎስ አልነበረም። በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብም ስለ ትንሣኤ ተናግሯል። ኢዮብ አምላክ እንደሚያስታውሰውና ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነበር።—ኢዮብ 14:7-10, 12-15

3. አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 የሚጠቅመን እንዴት ነው?

3 ‘የሙታን ትንሣኤ’ ለክርስትና “መሠረት” ከሆኑት ትምህርቶች አንዱ ነው። (ዕብ. 6:1, 2) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ስለ ትንሣኤ ማብራሪያ ሰጥቷል። የጳውሎስ መልእክት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች አበረታቷቸው መሆን አለበት። ይህ ምዕራፍ እኛንም ሊያበረታታን እና ለረጅም ጊዜ የነበረንን ተስፋ ሊያጠናክርልን ይችላል።

4. በሞት ያጣናቸው ሰዎች እንደሚነሱ ዋስትና የሚሰጠን ምንድን ነው?

4 የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ በሞት ያጣናቸው ሰዎች እንደሚነሱ ዋስትና ይሰጠናል፤ እንዲሁም እኛ ራሳችን እንኳ ብንሞት ትንሣኤ እንደምናገኝ ያረጋግጥልናል። የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የሰበከው “ምሥራች” ክፍል ነበር። (1 ቆሮ. 15:1, 2) እንዲያውም ጳውሎስ፣ አንድ ክርስቲያን በኢየሱስ ትንሣኤ ካላመነ እምነቱ ከንቱ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:17) ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ማመን፣ በትንሣኤ ተስፋ ለማመን መሠረት ይሆናል።

5-6. በ1 ቆሮንቶስ 15:3, 4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

5 ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ማብራሪያ ሲጀምር ሦስት እውነታዎችን ገልጿል። (1) “ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ።” (2) “ተቀበረ።” (3) “ቅዱሳን መጻሕፍት [እንደሚሉት] በሦስተኛው ቀን ተነሳ።”1 ቆሮንቶስ 15:3, 4ን አንብብ።

6 የኢየሱስ መሞት፣ መቀበርና መነሳት ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ነቢዩ ኢሳይያስ፣ መሲሑ ‘ከሕያዋን ምድር እንደሚወገድ’ እና ‘የመቃብር ቦታው ከክፉዎች ጋር እንደሚሆን’ በትንቢት ተናግሯል። ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። ኢሳይያስ አክሎም መሲሑ ‘የብዙ ሰዎችን ኃጢአት እንደሚሸከም’ ገልጿል። ኢየሱስ ይህን ያደረገው ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው። (ኢሳ. 53:8, 9, 12፤ ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:8) በመሆኑም የኢየሱስ መሞት፣ መቀበርና መነሳት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንደምንወጣ እንዲሁም በሞት ካጣናቸው ሰዎች ጋር መልሰን እንደምንገናኝ ላለን ተስፋ ጠንካራ መሠረት ይሆናል።

የብዙ ምሥክሮች ምሥክርነት

7-8. ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እርግጠኛ እንዲሆኑ የሚረዳቸው ምንድን ነው?

7 የትንሣኤ ተስፋችን፣ ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋር የተቆራኘ ነው። ስለዚህ በትንሣኤ ለማመን፣ ኢየሱስ እንደተነሳ በእርግጠኝነት ማመን ይኖርብናል። ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የመሠከሩ ብዙ የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። (1 ቆሮ. 15:5-7) ጳውሎስ መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ምሥክር፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ (ኬፋ) ነው። ጴጥሮስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን እንዳየው ሌሎች ደቀ መዛሙርትም መሥክረዋል። (ሉቃስ 24:33, 34) በተጨማሪም “አሥራ ሁለቱ” ማለትም ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስን ከሞት ከተነሳ በኋላ አይተውታል። ከዚያም ክርስቶስ “በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” ታየ፤ ይህ የሆነው በማቴዎስ 28:16-20 ላይ በተገለጸውና በገሊላ በተከናወነው አስደሳች ስብሰባ ወቅት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ‘ለያዕቆብም ታይቷል’፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ የኢየሱስ ወንድም መሆን አለበት። ያዕቆብ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ቀደም ሲል አላመነም ነበር። (ዮሐ. 7:5) ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ካየ በኋላ ግን በእሱ አመነ። በ55 ዓ.ም. ገደማ ማለትም ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት፣ ለኢየሱስ ትንሣኤ የዓይን ምሥክር ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሕይወት የነበሩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ስለዚህ ጥርጣሬ ያደረበት ማንኛውም ሰው፣ በወቅቱ በሕይወት የነበሩትን እምነት የሚጣልባቸው የዓይን ምሥክሮች ማነጋገር ይችል ነበር።

9. በሐዋርያት ሥራ 9:3-5 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ ለኢየሱስ ትንሣኤ ተጨማሪ ምሥክር የሆነው እንዴት ነው?

9 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ ለጳውሎስ ለራሱ ተገልጦለታል። (1 ቆሮ. 15:8) ጳውሎስ (ሳኦል) ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ሳለ፣ ከሞት የተነሳውን የኢየሱስን ድምፅ ሰማ፤ እንዲሁም በሰማይ ያለውን ኢየሱስን በራእይ ተመለከተው። (የሐዋርያት ሥራ 9:3-5ን አንብብ።) ጳውሎስ ያጋጠመው ነገር፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—ሥራ 26:12-15

10. ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ መሆኑ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

10 በተለይ የጳውሎስ ምሥክርነት የአንዳንዶችን ትኩረት ስቦ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በአንድ ወቅት ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር። ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን አምኖ ከተቀበለ በኋላ ግን ሌሎችም ይህን እንዲያምኑ ለመርዳት በትጋት ሠርቷል። ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሚገልጸውን እውነት በሚሰብክበት ወቅት ተደብድቧል፣ ታስሯል እንዲሁም የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞታል። (1 ቆሮ. 15:9-11፤ 2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ስለዚህ ጉዳይ ለመስበክ ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ ነበር። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሰጡት ይህ ምሥክርነት ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ እንድትሆን አያደርግህም? በትንሣኤ ላይ ያለህን እምነትስ አያጠናክረውም?

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስተካከል

11. በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

11 በግሪክ በምትገኘው በቆሮንቶስ ከተማ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው፤ እንዲያውም “የሙታን ትንሣኤ የለም” እስከማለት ደርሰው ነበር። ለምን? (1 ቆሮ. 15:12) በሌላኛዋ የግሪክ ከተማ በአቴንስ የሚኖሩ ፈላስፎች፣ ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል በሚለው ሐሳብ አሹፈዋል። ይህ አስተሳሰብ በቆሮንቶስ ባሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 17:18, 31, 32) ሌሎች ደግሞ የትንሣኤ ትምህርት ምሳሌያዊ እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል፤ በእነሱ አመለካከት አንድ ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በኃጢአቱ ምክንያት እንደ “ሞተ” ይቆጠር ነበር፤ ክርስቲያን ሲሆን ግን “ሕያው” ሆኗል። እነዚህ ክርስቲያኖች ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ የትንሣኤን ትምህርት ካልተቀበሉ እምነታቸው ከንቱ ነው። አምላክ ኢየሱስን ከሞት ካላስነሳው፣ ቤዛው አልተከፈለም እንዲሁም ማንም ሰው ከኃጢአቱ ይቅርታ አያገኝም ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የትንሣኤን ትምህርት መቀበል የማይፈልጉ ሰዎች እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ሊኖራቸው አይችልም።—1 ቆሮ. 15:13-19፤ ዕብ. 9:12, 14

12. በ1 ጴጥሮስ 3:18, 22 መሠረት የኢየሱስ ትንሣኤ ከዚያ ቀደም ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የሚለየው እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ ‘ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ’ በእርግጠኝነት ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ትንሣኤ ከዚያ ቀደም ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የላቀ ነበር፤ ምክንያቱም ከሞት የተነሱት ሌሎቹ ሰዎች በድጋሚ ሞተዋል። ኢየሱስ “በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ” ከሞት እንደተነሳ ጳውሎስ ተናግሯል። ኢየሱስ በኩራት የተባለው ከምን አንጻር ነው? መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት ለመነሳትም ሆነ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ለመሄድ የመጀመሪያው ሰው እሱ ነው።—1 ቆሮ. 15:20፤ ሥራ 26:23፤ 1 ጴጥሮስ 3:18, 22ን አንብብ።

‘ሕያው የሚሆኑት’ እነማን ናቸው?

13. ጳውሎስ አዳምንና ኢየሱስን ያነጻጸረው እንዴት ነው?

13 የአንድ ሰው ሞት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ሰጥቷል። ሐዋርያው፣ አዳም በሰው ልጆች ላይ ያመጣውን ችግር፣ ክርስቶስ ካስገኘው በረከት ጋር በንጽጽር አስቀምጧል። ጳውሎስ አዳምን አስመልክቶ ሲናገር “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል [ነው]” ብሏል። አዳም ኃጢአት በመሥራቱ በራሱም ሆነ በዘሮቹ ላይ ሞት አምጥቷል። የእሱ አለመታዘዝ ያስከተለው መዘዝ አሁንም አልለቀቀንም። አምላክ ልጁን ከሞት ማስነሳቱ ያስገኘው ውጤት ግን ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! ጳውሎስ “የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው [በኢየሱስ] በኩል ነው። ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና” የሚል አሳማኝ ነጥብ አቅርቧል።—1 ቆሮ. 15:21, 22

14. አዳም ከሞት ይነሳል? አብራራ።

14 ጳውሎስ ‘ሁሉም በአዳም ይሞታሉ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ስለ አዳም ዘሮች መናገሩ ነበር፤ ሁሉም የአዳም ዘሮች ኃጢአትንና አለፍጽምናን ከአዳም ስለወረሱ እንደሚሞቱ ገልጿል። (ሮም 5:12) አዳም ‘ሕያው ከሚሆኑት’ መካከል አይካተትም። አዳም ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም አያገኝም፤ ምክንያቱም አዳም ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ሆን ብሎ በአምላክ ላይ ዓምጿል። የአዳም ዕጣ ፈንታ፣ ኢየሱስ ‘ፍየሎች’ እንደሆኑ ከሚፈርድባቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፤ የሁሉም ፍርድ ‘የዘላለም ጥፋት’ ነው።—ማቴ. 25:31-33, 46፤ ዕብ. 5:9

ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በርካታ ሰዎች የመጀመሪያው ነው (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. “ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” ከተባሉት መካከል እነማን ይገኙበታል?

15 ጳውሎስ “ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” እንዳለ ልብ እንበል። (1 ቆሮ. 15:22) ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች ደግሞ ተስፋቸው ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ መሄድ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላቸው አንድነት የተቀደሱ እና ቅዱሳን ለመሆን የተጠሩ’ ናቸው። እንዲሁም ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት [ስላንቀላፉ]” ሰዎች ተናግሯል። (1 ቆሮ. 1:2፤ 15:18፤ 2 ቆሮ. 5:17) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ፣ ‘ሞቱን በሚመስል ሞት ከኢየሱስ ጋር አንድ የሆኑ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደሚሆኑ’ ገልጿል። (ሮም 6:3-5) ኢየሱስ መንፈስ ሆኖ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሄዷል። ስለዚህ “ከክርስቶስ ጋር አንድነት” ያላቸው ሁሉ ማለትም ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።

16. ጳውሎስ ኢየሱስን “በኩራት” ብሎ መጥራቱ ምን ያመለክታል?

16 ጳውሎስ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል” በማለት ጽፏል። እርግጥ ነው፣ አልዓዛርን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ኖረዋል፤ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ከሞት ለመነሳትና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ነበር። ኢየሱስ፣ እስራኤላውያን ለአምላክ ያቀርቡ ከነበረው የፍሬ በኩራት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በተጨማሪም ጳውሎስ ኢየሱስን “በኩራት” ብሎ መጥራቱ ከእሱ በኋላ ሌሎች ሰዎችም ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ይጠቁማል። ሐዋርያትን ጨምሮ ‘ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው’ ሌሎች ሰዎች ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ዓይነት ትንሣኤ ያገኛሉ።

17. ‘ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው’ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን የሚያገኙት መቼ ነው?

17 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ‘ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው’ ክርስቲያኖች የሚያገኙት ሰማያዊ ትንሣኤ አልጀመረም ነበር። ጳውሎስ ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው ወደፊት እንደሆነ ጠቁሟል። እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።” (1 ቆሮ. 15:23፤ 1 ተሰ. 4:15, 16) አሁን የምንኖረው ጳውሎስ “ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ” ብሎ በጠቀሰው ዘመን ውስጥ ነው። ሐዋርያትም ሆኑ በሞት ያንቀላፉ ሌሎች በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች፣ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለማግኘትና ‘የኢየሱስን ትንሣኤ በሚመስል ትንሣኤ ከእሱ ጋር አንድ ለመሆን’ ‘የክርስቶስ መገኘት’ እስኪጀምር ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።

አስተማማኝ ተስፋ አለን!

18. (ሀ) ከሰማያዊው ትንሣኤ በኋላ ሌላ ትንሣኤ እንደሚከናወን መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በ1 ቆሮንቶስ 15:24-26 መሠረት በሰማይ ምን ይከናወናል?

18 ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመኖር ተስፋ ስለሌላቸው ታማኝ ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስና ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሌሎች ክርስቲያኖች “መጀመሪያ ላይ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል” እንደሚሆኑ ይናገራል። (ፊልጵ. 3:11) ይህ ሐሳብ ከዚያ በኋላ ሌላ ትንሣኤ እንደሚከናወን የሚጠቁም አይደለም? ይህ መደምደሚያ ኢዮብ ስለ ተስፋው ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ኢዮብ 14:15) “ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት” ቅቡዓን፣ ኢየሱስ ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን በሚያጠፋበት ጊዜ ከእሱ ጋር በሰማይ ላይ ይሆናሉ። “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት” እንኳ ይደመሰሳል። ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች ዳግመኛ እንደማይሞቱ ግልጽ ነው። ግን ስለ ሌሎቹስ ምን ማለት ይቻላል?1 ቆሮንቶስ 15:24-26ን አንብብ።

19. ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ምን እንደሚያገኙ መጠበቅ ይችላሉ?

19 ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎችስ ምን እንደሚያገኙ መጠበቅ ይችላሉ? ጳውሎስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። (ሥራ 24:15) ዓመፀኞች ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ወደፊት በምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚኖር ይጠቁማል።

በትንሣኤ ተስፋ ማመናችን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ ያስችለናል (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት) *

20. በትንሣኤ ላይ ያለህ እምነት የተጠናከረው እንዴት ነው?

20 ሰዎች “ከሞት እንደሚነሱ” ምንም ጥርጥር የለውም! በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። በዚህ ተስፋ ላይ መተማመን እንችላለን። በሞት ስላጣናቸው ሰዎች ስናስብ ይህ ተስፋ ያጽናናናል። እነዚህ ሰዎች፣ ክርስቶስና ቅቡዓኑ ‘ለ1,000 ዓመት በሚነግሡበት’ ወቅት ከሞት ይነሳሉ። (ራእይ 20:6) እኛም የሺህ ዓመቱ ግዛት ከመጀመሩ በፊት በሞት ካንቀላፋን፣ ትንሣኤ እንደምናገኝ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይህ ተስፋ “ሳይፈጸም ቀርቶ ለሐዘን አይዳርገንም።” (ሮም 5:5) በአሁኑ ጊዜ ብርታት ይሰጠናል፤ እንዲሁም አምላክን በደስታ እንድናገለግል ይረዳናል። ሆኖም ከ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 የምናገኛቸው ሌሎች ትምህርቶችም አሉ፤ ቀጣዩ ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

መዝሙር 147 የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሰጥቶናል

^ አን.5 አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 በትንሣኤ ላይ ያተኮረ ነው። የትንሣኤ ትምህርት ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ የጥናት ርዕስ ለእነዚህና ስለ ትንሣኤ ለሚነሱ ሌሎች አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ ወደ ሰማይ የሄደው የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ነው። (ሥራ 1:9) እንደ እሱ ወደ ሰማይ ከሄዱ ደቀ መዛሙርቱ መካከል ቶማስ፣ ያዕቆብ፣ ሊዲያ፣ ዮሐንስ፣ ማርያም እና ጳውሎስ ይገኙበታል።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ለረጅም ጊዜ አብራው ያገለገለችውን ውድ ባለቤቱን በሞት አጥቷል። ሆኖም ባለቤቱ ትንሣኤ እንደምታገኝ በመተማመን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል።