በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ138ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ138ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት

መጋቢት 14 ቀን 2015 በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ማዕከል ውስጥ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ138ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ ነበር። የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በተለያዩ አካባቢዎች ሆነው በቪዲዮ በቀጥታ የተመለከቱትን ጨምሮ ከ14,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ አራት አዳዲስ መዝሙሮች የተሰሙ ሲሆን በኋላ ላይ ተሰብሳቢዎቹ እነዚህን መዝሙሮች በአንድነት ዘምረዋል። a

የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ጄፍሪ ጃክሰን ነው። በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ እውቀታቸውን ከመደበቅ ይልቅ ያገኙትን ሥልጠና ሌሎችን ለመርዳት እንዲጠቀሙበት አበረታታቸው።—2 ጢሞቴዎስ 2:2

ወንድም ጃክሰን ሙሴ የተወውን ምሳሌ አብራርቶ ነበር። የሙሴ ድንኳን ለተወሰነ ጊዜ ለእስራኤል ብሔር የአምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሎ ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና የማደሪያው ድንኳን ተሠርቶ ሲጠናቀቅ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆነ። ሙሴ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ወደሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን የመግባት መብት የነበረው አይመስልም፤ ይህ መብት የተሰጠው ለሊቀ ካህናቱ ነበር። ሆኖም ሙሴ ይህ ማስተካከያ በመደረጉ ቅር እንደተሰኘ የሚጠቁም ዘገባ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ አሮንን ሊቀ ካህናት ሆኖ ሲያገለግል በታማኝነት ደግፎታል። (ዘፀአት 33:7-11፤ 40:34, 35) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ወንድም ጃክሰን “ያላችሁ መብት ምንም ይሁን ምን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤ ሆኖም ያላችሁን መብት ለራሳችሁ ሸሽጋችሁ አትያዙ” ሲል ተናግሯል።

“የቅጠል ኮሽታ ያስበረግጋችኋል?” ይህን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ኬነዝ ፍሎዲን ነው። ተማሪዎቹ እንደ ስደት ወይም ፈታኝ የሥራ ምድብ ያሉ አስፈሪ የሚመስሉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ጠቀሰ። ዘሌዋውያን 26:36 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በመጠቀም ተማሪዎቹ እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎችን ሊወጧቸው እንደማይችሉ ነገሮች አድርገው ከመመልከት ይልቅ እንደደረቀ ቅጠል አድርገው እንዲመለከቷቸው መክሯቸዋል። ከዚያም ወንድም ፍሎዲን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ጎላ አድርጎ ገለጸ፤ ጳውሎስ በይሖዋ በመታመን ያጋጠሙትን በርካታ ፈተናዎች ተቋቁሟል።—2 ቆሮንቶስ 1:8, 10

“የምትፈልጉት ምንድን ነው?” የበላይ አካል አባል የሆነው ማርክ ሳንደርሰን ቀጣዩን ንግግር አቀረበ። “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” የሚለውን ምሳሌ 13:12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት አብራራ። ብዙ ሰዎች እንደ ሀብት ወይም ዝና ያሉ ሊያገኟቸው የማይችሉ ነገሮችን ግብ አድርገው ስለሚያሳድዱ ሕይወታቸውን ሙሉ እንዳዘኑ ይኖራሉ።

በኢየሱስ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ከአጥማቂው ዮሐንስ ጋር በተያያዘ የጠበቁት ነገር የተሳሳተ ነበር። (ሉቃስ 7:24-28) ለምሳሌ ያህል የተወሳሰቡ ትምህርቶችን የሚያስተምር ፈላስፋ ይሆናል ብለው ጠብቀው ሊሆን ይችላል። እንዲህ አስበው ከነበረ ዮሐንስ ግልጽ የሆነ የእውነት መልእክት ስላስተማረ ቅር ተሰኝተው መሆን አለበት። ሌሎች ደግሞ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ሰው ይሆናል ብለው ጠብቀው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ዮሐንስ ይለብስ የነበረው ድሃ የሆኑ ሰዎች ይለብሱት የነበረውን ዓይነት ልብስ ነው። ነቢይ ነው ብለው የጠበቁ ሰዎች ግን ቅር አልተሰኙም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ነበር!—ዮሐንስ 1:29

ወንድም ሳንደርሰን ይህን ምሳሌ በመጠቀም ተማሪዎቹ ትክክለኛውን ነገር እንዲጠብቁ ወይም እንዲፈልጉ አሳሰባቸው። የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የተለየ ክብር ወይም ቦታ እንዲሰጣቸው ከመጠበቅ ይልቅ ያገኙትን ሥልጠና ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀሙበት ይገባል። በጊልያድ የቀሰሙትን ትምህርት ለሌሎች በማካፈል፣ የወንድሞቻቸውና የእህቶቻቸው እምነት እንዲጠናከር በመርዳትና ለእነሱ ፍቅር በማሳየት ይህን ማድረግ ይችላሉ። “ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በትሕትና ለማገልገል እንዲሁም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ፈጽሞ ቅር አትሰኙም” ሲል ወንድም ሳንደርሰን ተናግሯል።

“የተራቡትን መግቡ።” ይህን ንግግር ያቀረበው ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን በሚከታተለው ክፍል ውስጥ አስተማሪ ሆኖ የሚያገለግለው ጀምስ ኮቶን ነው። ወንድም ኮቶን ሁሉም ሰው ፍቅርንና አድናቆትን እንደሚራብ እንዲሁም እውቅና ማግኘት እንደሚፈልግ ገለጸ። ኢየሱስም እንኳ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት የነበረው ሲሆን በተጠመቀበት ጊዜ ይሖዋ ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን ቃላት በመናገር ይህን ፍላጎቱን አሟልቶለታል።—ማቴዎስ 3:16, 17

ይሖዋ ሌሎችን በአንደበታችን ማበረታታትና ማጠናከር የምንችልበት ጥሩ ችሎታ ሰጥቶናል፤ ይህን ችሎታችንን ደግሞ እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። (ምሳሌ 3:27) ወንድም ኮቶን “የሌሎችን መልካም ጎን የማየት ልማድ ለማዳበር ጥረት አድርጉ፤ መልካም ጎናቸውን ጠቅሳችሁ ከማመስገንም ወደኋላ አትበሉ” ሲል ተማሪዎቹን አሳስቧል። የእምነት ባልንጀሮቻችንን ከልብ የምናመሰግናቸው ከሆነ ጥረታቸው ከንቱ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።

“ሙሉ አቅማችሁን ተጠቀሙ።” ይህን ንግግር ያቀረበው የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ማርክ ኑሜር ነው። ወንድም ኑሜር የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በመጠቀም ተማሪዎቹ አነስተኛ ነገር በማድረግ ብቻ እንዳይረኩ አሳሰባቸው። ከዚህ ይልቅ እንደ ጳውሎስ ራሳቸውን ለሌሎች ‘እንደ መጠጥ መባ’ ካፈሰሱ እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ።—ፊልጵስዩስ 2:17, 18

ጳውሎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ተስፋ አልቆረጠም። እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በትጋት ያገለግል ስለነበር ሙሉ አቅሙን ተጠቅሟል ማለት ይቻላል። በመሆኑም በእርግጠኝነት “ሩጫውን ጨርሻለሁ” ማለት ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:6, 7) ወንድም ኑሜር በተመደቡበት የአገልግሎት መስክ የመንግሥቱን ሥራ በታማኝነት በመደገፍ የጳውሎስን ምሳሌ እንዲከተሉ ተማሪዎቹን አበረታቷቸዋል።

ተሞክሮዎች። ቀጣዩን ክፍል ያቀረበው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ማይክል በርኔት ሲሆን ተማሪዎቹ በፓተርሰን በነበሩበት ወቅት በአገልግሎት ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ አቅርበዋል።

ተማሪዎቹ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሚገባ በመጠቀምና እውነትን ለሰዎች “ልባቸውን ሊነካ በሚችል ቋንቋ” ማለትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለመናገር ጥረት በማድረግ በተደጋጋሚ ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ለምሳሌ አንድ ተማሪ እሱ በሚያገለግልበት ክልል ውስጥ ስፓንኛ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ሰማ። ስለዚህ አንድ ቀን ወደ አገልግሎት ከመውጣቱ በፊት ጄደብሊው ላንግዌጅ የተባለውን አፕሊኬሽን በመጠቀም ጥቂት የስፓንኛ ቃላትን አጠና። በዚያው ቀን መንገድ ላይ ስፓንኛ የሚናገር ሰው አገኘ። ያጠናቸውን ጥቂት የስፓንኛ ቃላት በመጠቀም ከሰውየው ጋር ውይይት የጀመረ ሲሆን በዚህ የተነሳ ግለሰቡና አራት የቤተሰቡ አባላት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምረዋል።

ቃለ መጠይቅ። በመቀጠል የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ዊሊያም ተርነር ወደ ጊልያድ ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸውን ተሞክሮና በትምህርት ቤቱ ያገኙትን ሥልጠና በተመለከተ ለአራት ተማሪዎች ቃለ መጠይቅ አደረገ።

ተማሪዎቹ ከትምህርቱ ያገኟቸውን የሚያበረታቱ ነጥቦች ጠቀሱ። ለምሳሌ አንደኛው ተማሪ በሉቃስ ምዕራፍ 10 ላይ ከሰፈረው ዘገባ ምን ትምህርት እንዳገኘ ገልጿል። ኢየሱስ የላካቸው 70 ደቀ መዛሙርት በአገልግሎታቸው ጥሩ ውጤት በማግኘታቸው ተደስተው ነበር። ኢየሱስም በዚህ የተደሰተ ቢሆንም ደስታቸው ባገኙት ውጤት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዳልሆነ ገልጾላቸዋል፤ ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት ሊያስደስታቸው የሚገባው፣ ይሖዋ ባደረጉት ጥረት እንደሚደሰት ማወቃቸው መሆን እንዳለበት አስተምሯቸዋል። ይህ ዘገባ እውነተኛ ደስታ የተመካው በእኛ ሁኔታ ላይ ሳይሆን የይሖዋን ሞገስ በማግኘታችን ላይ እንደሆነ ያስተምረናል።

ወንድም ተርነር ፊልጵስዩስ 1:6ን በመጠቀም ይሖዋ በእነሱ አማካኝነት “መልካም ሥራ” ማከናወን እንደጀመረ እንዲሁም ይሖዋ ምንጊዜም ከእነሱ ጋር እንደሚሆን ለተማሪዎቹ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።

“ዓይናችሁ በይሖዋ ላይ እንዲያተኩር አድርጉ።” የፕሮግራሙን ዋነኛ ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ ነው። ይሖዋን ቃል በቃል ልናየው እንደማንችል ገልጿል። ታዲያ ዓይናችን በእሱ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋን ማየት የምንችልበት አንደኛው መንገድ ስለ እሱ የሚያስተምሩንን የፍጥረት ሥራዎቹን መመርመር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ‘የልባችን ዓይኖች እንዲበሩ አድርጓል።’ (ኤፌሶን 1:18) መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብን መጠን ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንማራለን። ስለ ይሖዋ በተማርን መጠን ደግሞ ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን።

በተለይ በወንጌሎች ላይ ለሚገኙት ዘገባዎች ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፤ ምክንያቱም እነዚህ ዘገባዎች ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርትና ባደረጋቸው ነገሮች አማካኝነት ያንጸባረቀውን የይሖዋን ማንነት ይበልጥ እንድንረዳ ያስችሉናል። ኢየሱስ የይሖዋን ባሕርያት በሚገባ ስላንጸባረቀ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ማለት ችሏል።—ዮሐንስ 14:9

ወንድም ኸርድ ተሰብሳቢዎቹ የኢየሱስን ምሳሌ በመመርመር ይሖዋን ማየት ብቻ ሳይሆን ያዩትን ለመከተል ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። ለምሳሌ ኢየሱስ ሌሎችን ለመመገብ በትጋት እንደሠራ ሁሉ እኛም ያገኘነውን መንፈሳዊ ምግብ ለሌሎች ለማካፈል ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል።

ዓይናችን በይሖዋ ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችን ምን ጥቅም አለው? “ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ። እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም” በማለት እንደጻፈው መዝሙራዊ ዓይነት የመተማመን ስሜት ያድርብናል።—መዝሙር 16:8

መደምደሚያ። ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከተመራቂዎቹ መካከል አንዱ የተማሪዎቹን የምስጋና ደብዳቤ አነበበ። ከዚያም ወንድም ጃክሰን በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ ተመራቂዎቹ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ወይም ጥልቀት ያለው ትምህርት ማስተማር እንዳለባቸው ሆኖ ሊሰማቸው እንደማይገባ ተናገረ። አብዛኛውን ጊዜ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ቀድሞውኑ የሚያውቁትን ነገር እንዲያስታውሱ መርዳት ነው። በተጨማሪም ወንድም ጃክሰን የትሕትናን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገለጸ። ተመራቂዎቹ ሌሎች ሰዎች በእነሱ ወይም በጊልያድ ባገኙት ሥልጠና ላይ እንዲያተኩሩ ከማድረግ ይልቅ በአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ተመራቂዎቹ በጊልያድ ትምህርት ቤት የመማር አጋጣሚ የሌላቸው ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ ከማድረግ ይልቅ ሊያገኙት ከሚችሉት መንፈሳዊ ዝግጅት እንዲጠቀሙ በመርዳት የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ሊያበረታቷቸው ይገባል። ፕሮግራሙ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እንዲታነጹ እንዲሁም ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማገልገል እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

a አዳዲሶቹ መዝሙሮች በፕሮግራሙ ላይ ለሚገኙት ወንድሞች በዚያው ሳምንት ቀደም ብሎ እንዲላኩላቸው ተደርጎ ነበር።

b በካርታው ላይ ሁሉም አገሮች አልተካተቱም።

c ሁሉም የተመራቂዎቹ ስሞች አልተካተቱም።