በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ማጨስ ኃጢአት ነው?

ማጨስ ኃጢአት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማጨስም a ሆነ ትንባሆን በሌሎች መንገዶች ስለ መጠቀም አይናገርም። ሆኖም ጤናን የሚጎዱና ንጹሕ ያልሆኑ ልማዶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዟል፤ በመሆኑም ማጨስ በአምላክ ዘንድ ኃጢአት ነው።

  •   ለሕይወት አክብሮት ማሳየት፦ ‘ሕይወትንና እስትንፋስን ለሰው ሁሉ የሰጠው አምላክ ነው።’ (የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25) ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ስለሆነ ማጨስን ጨምሮ ዕድሜያችንን ሊያሳጥር የሚችል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን። ማጨስ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ሰዎች ያለዕድሜያቸው እንዲቀጩ ከሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ነው።

  •   ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር፦ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) ሌሎች ባሉበት ቦታ ማጨስ ለእነሱ ፍቅር እንዳለን አያሳይም። እንዲያውም ለሲጋራ ጭስ የተጋለጡ ሰዎች፣ የሚያጨሱ ሰዎችን በሚያጠቁ በሽታዎች የመያዝ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

  •   ቅዱስ ሆኖ መኖር፦ “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]።” (ሮም 12:1) “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ማጨስ ሰዎች ቅዱስ ወይም ንጹሕ ሆነው እንዳይኖሩ ያደርጋል፤ ምክንያቱም የሚያጨሱ ሰዎች አካላቸውን የሚጎዱ መርዛማ ነገሮችን ሆን ብለው ወደ ሰውነታቸው ያስገባሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ለመዝናናት ሲባል ማሪዋና ወይም ሌላ ዓይነት ዕፅ ስለ መውሰድ የሚናገረው ነገር አለ?

 መጽሐፍ ቅዱስ ማሪዋና (ዊድ ወይም ፖት ተብሎም ይጠራል) ወይም ሌላ ዓይነት ዕፅ ጠቅሶ አይናገርም። ይሁን እንጂ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን ለመዝናኛ ብሎ መውሰድን የሚከለክሉ መመሪያዎች ይዟል። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት መመሪያዎች በተጨማሪ የሚከተሉትም ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሠራሉ፦

  •   የማሰብ ችሎታችንን የመቆጣጠር አስፈላጊነት፦ “አምላክህን ይሖዋን . . . በሙሉ አእምሮህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:37, 38) “የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ።” (1 ጴጥሮስ 1:13) አንድ ሰው ዕፅ የሚወስድ ከሆነ የማሰብ ችሎታውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይችልም፤ እንዲያውም ብዙ ሰዎች የእነዚህ ዕፆች ሱሰኛ ሆነዋል። አእምሯቸው የሚያተኩረው ጥሩ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን ዕፅ ማግኘት በሚችሉበት መንገድ ላይ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:8

  •   ለመንግሥት ባለሥልጣናት መታዘዝ፦ ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት ታዘዙ።’ (ቲቶ 3:1) በብዙ አገራት ውስጥ አንዳንድ ዕፆችን መውሰድ በሕግ የተከለከለ ነው። አምላክን ማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንታዘዛለን።—ሮም 13:1

a ማጨስ ሲባል ሲጋራና ፒፓ ማጨስን፣ የትንባሆ ቅጠል ጠቅልሎ ማጨስን ወይም እንደ ሺሻ ባሉ ዕቃዎች ተጠቅሞ ማጨስን ይጨምራል። በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ላይ የተገለጸው ሐሳብ ትንባሆ ከማኘክ ወይም በአፍንጫ ከመሳብ እንዲሁም ኒኮቲን ያለው የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ እና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ከመጠቀም ጋር በተያያዘም በእኩል ደረጃ ይሠራል።