በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ኤርምያስ 11:11—“ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ”

ኤርምያስ 11:11—“ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ”

“ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ማምለጥ የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ። እርዳታ ለማግኘት ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውም።’”​—ኤርምያስ 11:11 አዲስ ዓለም ትርጉም

“ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፣ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፣ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም።”​—ኤርምያስ 11:11 የ1954 ትርጉም

ኤርምያስ 11:11 ትርጉም

 አምላክ ይህን ሐሳብ የተናገረው በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን ስለነበሩት አይሁዳውያን ነው። ሕዝቡ ይሖዋ a በነቢያቱ በኩል የሰጣቸውን የጽድቅ ሕጎችና ፍቅራዊ እርማቶች ችላ ብለዋል፤ በመሆኑም ይሖዋ መጥፎ አካሄዳቸው ከሚያስከትልባቸው መዘዝ ጥበቃ አያደርግላቸውም።​—ምሳሌ 1:24-32

 “ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል።” “ስለዚህ” የሚለው ቃል ከዚህ ዓረፍተ ነገር በፊት ያለውን ሐሳብ ቀጥሎ ከሚጠቀሰው ሐሳብ ጋር ያያይዘዋል። ይሖዋ፣ ኤርምያስ 11:1-10 ላይ አባቶቻቸው ከእሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ወይም ጽኑ ስምምነት እንዳፈረሱ ለሕዝቡ ነግሯቸዋል። (ዘፀአት 24:7) አይሁዳውያኑ ፈጣሪያቸውን ከማምለክ ይልቅ ወደ ጣዖት አምልኮ ዞር አሉ። ይህ ክህደት፣ ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን ጨምሮ ብዙ አስከፊ ነገሮችን ወደ መፈጸም መርቷቸዋል!​—ኤርምያስ 7:31

 “እነሆ . . . ጥፋት አመጣባቸዋለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ እንዲከናወኑ የፈቀዳቸው ነገሮች እሱ እንዳደረጋቸው ተደርገው የተገለጹባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ። እዚህ ጥቅስም ላይ ተመሳሳይ ነገር እናስተውላለን። ሕዝቡ ወደ ሐሰት አማልክት ዞር በማለትና ይሖዋ የሰጣቸውን ጠቃሚ መመሪያ ችላ በማለት በራሳቸው ላይ እጅግ አሳዛኝ መከራ አምጥተዋል። የአምላክንም ጥበቃ አጥተዋል። በውጤቱም ኃያል የሆነው ጠላታቸው ማለትም የባቢሎን ንጉሥ፣ ኢየሩሳሌምን ሊቆጣጠርና ነዋሪዎቿን በግዞት ሊወስድ ችሏል። ሕዝቡ የተማመኑባቸው የሐሰት አማልክት ሊያስጥሏቸው አልቻሉም።​—ኤርምያስ 11:12፤ 25:8, 9

 አምላክ ሕዝቡ እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ነገሮች እንዲደርሱባቸው መፍቀዱ ኢፍትሐዊ ወይም ክፉ አያስብለውም። ያዕቆብ 1:13 “አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም” በማለት ይናገራል። እርግጥ የ1954 ትርጉም አምላክ በአይሁዳውያኑ ላይ ‘ክፉ ነገር እንደሚያመጣባቸው’ ይገልጻል። ሆኖም ኤርምያስ 11:11 ላይ የገባው “ክፉ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ b “ጥፋት” ወይም “መዓት” የሚል ትርጉምም ሊያስተላልፍ ይችላል፤ ሁለቱም አገላለጾች በአይሁዳውያኑ ላይ የመጣውን መከራ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ።

 “እርዳታ ለማግኘት ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውም።” ይሖዋ ‘እጆቻቸው በደም የተሞሉ’ ወይም መዳን ለማግኘት በሐሰት አማልክት የሚታመኑ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት አይሰማም። (ኢሳይያስ 1:15፤ 42:17) ከልባቸው ተጸጽተው ከመጥፎ መንገዳቸው ንስሐ የሚገቡና በትሕትና ወደ እሱ የሚመለሱ ሰዎችን ጸሎት ግን ይሰማል።​—ኢሳይያስ 1:16-19፤ 55:6, 7

የኤርምያስ 11:11 አውድ

 በ647 ዓ.ዓ. ይሖዋ ኤርምያስን ነቢይ አድርጎ ሾመው። ለ40 ዓመታት ያህል ኤርምያስ የይሁዳን ሰዎች ስለ መጪው የአምላክ ፍርድ አስጠንቅቋል። እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም። ነቢዩ በኤርምያስ 11:11 ላይ የሚገኙትን ቃላት የጻፈው በዚህ ወቅት ነበር። በመጨረሻም በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ሲያጠፏት በትንቢት የተነገሩት ማስጠንቀቂያዎች ፍጻሜያቸውን አገኙ።​—ኤርምያስ 6:6-8፤ 39:1, 2, 8, 9

 የኤርምያስ መጽሐፍ ተስፋ የሚሰጥ መልእክትም ይዟል። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በባቢሎን የምትኖሩበት 70 ዓመት ሲፈጸም [ወደዚህ] ስፍራ [ወደ አይሁዳውያኑ የትውልድ አገር] መልሼ በማምጣት፣ የገባሁትን ቃል እፈጽማለሁ።” (ኤርምያስ 29:10) በ537 ዓ.ዓ. ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ስትደረግ ይሖዋ ይህን ‘ቃሉን ፈጽሟል።’ ይሖዋ በባቢሎን ግዛት ውስጥ ተበታትነው የነበሩት ሕዝቦቹ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱና እውነተኛውን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ አድርጓል።​—2 ዜና መዋዕል 36:22, 23፤ ኤርምያስ 29:14

 የኤርምያስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ፣ በዕብራይስጥ በአራት ፊደላት የተቀመጠው የአምላክ ስም የተለመደ የአማርኛ አጠራር ነው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአምላክ የግል ስም ከመጠቀም ይልቅ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም የመረጡት ለምን እንደሆነ ለማወቅ “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው የሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መጀመሪያ የተጻፉት በዕብራይስጥ እና በአረማይክ ነው።