ኤርምያስ 39:1-18

  • በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት (1-10)

    • ሴዴቅያስ ሲሸሽ ተያዘ (4-7)

  • ኤርምያስ ጥበቃ አገኘ (11-14)

  • ኤቤድሜሌክ ሕይወቱ እንደሚተርፍ ተነገረው (15-18)

39  የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾርና* መላው ሠራዊቱ መጥተው ኢየሩሳሌምን ከበቧት።+  በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በ11ኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማዋን ቅጥር ነደሉ።+  የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ ይኸውም ሳምጋሩ ኔርጋልሻሬጸር፣ ራብሳሪስ የሆነው ነቦሳርሰኪም፣* ራብማግ* የሆነው ኔርጋልሻሬጸርና የቀሩት የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ ገብተው በመካከለኛው በር አጠገብ ተቀመጡ።+  የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ፣ በንጉሡ የአትክልት ቦታ ባለው መንገድ፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር በኩል በሌሊት ከከተማዋ ወጥተው ሸሹ፤+ ወደ አረባ የሚወስደውንም መንገድ ተከትለው ሄዱ።+  የከለዳውያን ሠራዊት ግን አሳደዳቸው፤ ሴዴቅያስንም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት።+ ከያዙት በኋላ በሃማት+ ምድር በሪብላ+ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነጾር* አመጡት፤ እሱም በዚያ ፈረደበት።  የባቢሎን ንጉሥ በሪብላ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አሳረዳቸው፤ በተጨማሪም የባቢሎን ንጉሥ የይሁዳን ታላላቅ ሰዎች ሁሉ አሳረደ።+  የሴዴቅያስንም ዓይን አሳወረ፤ ከዚያም ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በመዳብ የእግር ብረት አሰረው።+  ከለዳውያንም የንጉሡን ቤትና* የሕዝቡን ቤቶች አቃጠሉ፤+ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች አፈረሱ።+  የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን+ በከተማዋ ውስጥ የቀሩትን በሕይወት የተረፉ ሰዎችና ከድተው ለእሱ እጃቸውን የሰጡትን ሰዎች እንዲሁም የቀሩትን ሁሉ በግዞት ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 10  ሆኖም የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን ምንም ነገር ያልነበራቸውን አንዳንድ ያጡ የነጡ ድሆች በይሁዳ ምድር እንዲኖሩ ተዋቸው። ደግሞም በዚያ ቀን የወይን እርሻዎችና የሚያርሱት የእርሻ መሬት* ሰጣቸው።+ 11  በዚህ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ኤርምያስን አስመልክቶ የዘቦች አለቃ ለሆነው ለናቡዛራዳን እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠ፦ 12  “ወስደህ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ አድርግለት፤ ክፉ ነገር አታድርግበት፤ የሚጠይቅህንም ነገር ሁሉ አድርግለት።”+ 13  በመሆኑም የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን፣ ራብሳሪስ* የሆነው ናቡሻዝባን፣ ራብማግ* የሆነው ኔርጋልሻሬጸር እንዲሁም የባቢሎን ንጉሥ ሹማምንት ሁሉ ልከው 14  ኤርምያስን ከክብር ዘቦቹ ግቢ+ አስወጡት፤ ደግሞም ወደ ቤቱ እንዲወስደው ለሳፋን+ ልጅ፣ ለአኪቃም+ ልጅ፣ ለጎዶልያስ+ ሰጡት። በመሆኑም ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ተቀመጠ። 15  ኤርምያስ በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ተዘግቶበት በነበረ ጊዜ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦ 16  “ሂድና ለኢትዮጵያዊው ለኤቤድሜሌክ+ እንዲህ በለው፦ ‘የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በዚህች ከተማ ላይ ለመልካም ሳይሆን ለጥፋት ቃሌን እፈጽማለሁ፤ በዚያም ቀን ይህ ሲፈጸም ታያለህ።”’ 17  “‘አንተን ግን በዚያ ቀን እታደግሃለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለምትፈራቸውም ሰዎች አልፈህ አትሰጥም።’ 18  “‘የምታመልጥበትን መንገድ አዘጋጅልሃለሁ፤ በሰይፍም አትወድቅም። በእኔ ስለታመንክ+ ሕይወትህ* እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች’*+ ይላል ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾርና።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
በዕብራይስጡ ጽሑፍ ላይ ያሉት ቃላት በሚከተለውም መንገድ ሊቀመጡ ይችላሉ፦ “ኔርጋልሻሬጸር፣ ሳምጋርነቦ፣ ሳርሰኪም፣ ራብሳሪስ።”
ወይም “የአስማተኞች አለቃ (ኮከብ ቆጣሪ)።”
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “ቤተ መንግሥትና።”
“የግዳጅ አገልግሎት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “የቤተ መንግሥት ዋና ባለሥልጣን።”
ወይም “የአስማተኞች አለቃ (ኮከብ ቆጣሪ)።”
ወይም “ነፍስህ።”
ወይም “ሕይወትህን ታተርፋለህ።”