በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስቴር ፓርከር | የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት እፈልግ ነበር

በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት እፈልግ ነበር

 ውድ ወላጆቼ ከሕፃንነቴ አንስቶ እውነትን ስላስተማሩኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከጠፋችው ገነት ወደምትመለሰው ገነት (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርገዋል። የተማርኩትን ነገር ጎረቤታችን ላሉ ልጆች በቅንዓት እነግራቸው ነበር፤ አያቴ ሊጠይቀን ሲመጣም ለእሱ እነግረዋለሁ። ወላጆቼ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ነበራቸው፤ ይህም ቤተሰባችን ከአስመራ፣ ኤርትራ ወደ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ተዛውሮ መኖር ሲጀምር በጣም ጠቅሞናል።

 ገና ልጅ ሳለሁ ጀምሮ ለእውነት ፍቅር ነበረኝ። ራሴን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ እፈልግ ነበር። በ13 ዓመቴ እዚህ ግብ ላይ መድረስ በመቻሌ በጣም ተደሰትኩ። በ14 ዓመቴ ወንድም ሄልየ ሊንክ a አቅኚ ስለመሆን አስቤ አውቅ እንደሆነ ጠየቀኝ። ያን ጊዜ በደንብ አስታውሰዋለሁ። አባቴና እናቴ ጊዜያዊ አቅኚ (በአሁኑ ጊዜ ረዳት አቅኚ በመባል ይታወቃል) ሆነው ያገለገሉ ቢሆንም ስለ ዘወትር አቅኚነት ግን ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ወንድም ሊንክ የጠየቀኝ ጥያቄ በልቤ ውስጥ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ይበልጥ እንዲቀሰቀስብኝ አደረገ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ ከወንድሜ ከኢዮስያስ ጋር

ለስደት መዘጋጀት

 በ1974 በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ እስራት፣ ግድያና ብጥብጥ የተለመዱ ነገሮች ሆነው ነበር። ከጊዜ በኋላ ከቤት ወደ ቤት መስበክም ሆነ በዛ ብሎ መሰብሰብ አስቸጋሪ ሆነ። ወላጆቻችን ወደፊት ሊያጋጥመን ለሚችለው የከፋ ተቃውሞ ያዘጋጁን ጀመር። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን መጠበቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ረድተውናል። ይሖዋ ለሚቀርቡልን ጥያቄዎች ምን ብለን መመለስ እንዳለብን ለማወቅ እንደሚረዳን እንዲሁም አንዳንዴ ዝም ማለት ሊያስፈልገን እንደሚችል ተምረናል።—ማቴዎስ 10:19፤ 27:12, 14

AFP PHOTO

በ1974 አለመረጋጋቱ በተከሰተበት ወቅት

 ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። አንድ ቀን ጠዋት ወደ ሥራ ስገባ የሥራ ባልደረቦቼ፣ በወቅቱ የነበረው መንግሥት የተቋቋመበትን ዓመት ለማክበር የሚደረገውን ሰልፍ እንድመራ በመመረጤ ደስታቸውን ገለጹልኝ። እኔም ወዲያውኑ፣ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቴ ምክንያት በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደማልካፈል ለአለቃዬ ነገርኩት።

 በቀጣዩ ቀን፣ በአየር ማረፊያው እየሠራሁ ሳለ በትከሻቸው ጠመንጃ ያነገቱ ሰዎች ወደ ቲኬት መቁረጫው ሲመጡ ከሩቅ አየሁ። ሰዎቹ የመጡት ከአገር ለመውጣት የሚሞክርን ሰው ለማሰር ነው ብዬ አሰብኩ። እነሱ ግን ጣታቸውን እኔ ላይ ቀሰሩብኝ! ምን ፈልገው እንደሆነ ግራ ገባኝ። አገር ሰላም ብዬ የጀመርኩት የሥራ ቀን በፍጥነት ተቀየረ።

በእስር ቤት ያገኘሁት እርዳታ

 ወታደሮቹ ወደ አንድ ቢሮ ወስደው ለሰዓታት ምርመራ አካሄዱብኝ። “የይሖዋ ምሥክሮችን የሚከፍላቸው ማን ነው?” ብለው አፋጠጡኝ። በተጨማሪም “ለኤርትራ ነፃነት ግንባር ነው የምትሠሪው? አንቺ ወይም አባትሽ የምትሠሩት ለአሜሪካ መንግሥት ነው?” ብለው ጠየቁኝ። ሁኔታው ውጥረት የሚፈጥር ቢሆንም ይሖዋ ስለረዳኝ በጣም ተረጋግቼ ነበር።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

 ምርመራውን ከጨረስኩ በኋላ ወታደሮቹ ወደ እስር ቤትነት ወደተለወጠ መኖሪያ ቤት በመኪና ወሰዱኝ፤ ከዚያም 28 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ክፍል ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ ከሆኑ ሌሎች 15 ወጣት ሴቶች ጋር አብረው አሰሩኝ።

የአየር መንገድ ሠራተኛ ሆኜ

 ያን ምሽት የአየር መንገድ ዩኒፎርሜን እንደለበስኩ በዚያ ደረቅ ወለል ላይ ጋደም ብዬ ወላጆቼና ታናናሾቼ ምን ያህል ሊጨነቁ እንደሚችሉ አስብ ነበር። እንደታሰርኩ ቢያውቁም የት እንዳለሁ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይሖዋ በሆነ መንገድ ለቤተሰቦቼ የታሰርኩበትን ቦታ እንዲያሳውቃቸው ለመንኩት።

 በቀጣዩ ጠዋት ስነሳ አንድ የማውቀውን ወጣት ጠባቂ አየሁ። እሱም በድንጋጤ እያየኝ “አስቴር፣ እዚህ ምን ታደርጊያለሽ?” አለኝ። እኔም ወደ ወላጆቼ ቤት ሄዶ የት እንዳለሁ እንዲነግራቸው ለመንኩት። በዚያው ዕለት ወላጆቼ ምግብና ልብስ ላኩልኝ። ጠባቂው ያለሁበትን ነግሯቸው ነበር። ይሖዋ ጸሎቴን መለሰልኝ! ይህ አጋጣሚ ብቻዬን እንዳልሆንኩ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።

 እስር ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ጽሑፍ ይዞ መገኘት ክልክል ነበር፤ ወላጆቼና ጓደኞቼም እኔን መጠየቅ አይፈቀድላቸውም ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ አብረውኝ በታሰሩ ሰዎች አማካኝነት አበረታቶኛል። በየዕለቱ እሰብክላቸው የነበረ ሲሆን እነሱም ስለ አምላክ መንግሥት በሚገልጸው እውነት ይገረሙ ነበር። በተደጋጋሚ እንዲህ ይሉኛል፦ “እኛ የምንዋጋው ለሰብዓዊ መንግሥት ነው፤ አንቺ ግን የምትዋጊው ለአምላክ መንግሥት ነው። እንደሚገድሉሽ ቢዝቱብሽ እንኳ ፈጽሞ ከአቋምሽ ፍንክች እንዳትዪ!”

 አንዳንድ ጊዜ ጠባቂዎች በእስረኞቹ ላይ ምርመራ ያካሂዱባቸውና ይደበድቧቸው ነበር። አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ ወደ እኔ መጡ። ወደ ምርመራ ክፍሉ ከወሰዱኝ በኋላ በብዙ ክሶች ይወነጅሉኝ ጀመር። መንግሥትን እንደማልደግፍ ይናገሩ ነበር። ከዚያም የፖለቲካ መፈክር ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆኔ ሁለት ወንድ ጠባቂዎች ደበደቡኝ። ጠባቂዎቹ በተደጋጋሚ እንዲህ ያሉ ምርመራዎች አካሂደውብኛል። ለምርመራ በምወሰድበት ጊዜ ሁሉ ወደ ይሖዋ አጥብቄ እጸልያለሁ፤ እሱም ከጎኔ ሆኖ እንደደገፈኝ ይሰማኛል።

 ከሦስት ወራት በኋላ አንዱ ጠባቂ መጥቶ ነፃ እንደተለቀቅኩ ነገረኝ። በዚህ ብደሰትም እስር ቤት ከነበሩት ወጣት ሴቶች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት ተስፋ መወያየት ያስደስተኝ ስለነበር የተወሰነ ቅሬታ ተሰማኝ።

 ከእስር ከተፈታሁ ከጥቂት ወራት በኋላ እኔ ቤት ባልነበርኩበት ሰዓት ወታደሮች መጥተው ቤታችን ያሉትን ወጣቶች በሙሉ አሰሩ! ሁለት እህቶቼንና አንድ ወንድሜን ወደ እስር ቤት ወሰዷቸው። በዚህ ጊዜ፣ ከአገሪቱ መሸሽ እንዳለብኝ ወሰንኩ። ድጋሚ ከቤተሰቤ መለየቱን ሳስብ በጣም ቢከብደኝም እናቴ ጠንካራ እንድሆንና በይሖዋ እንድታመን አበረታታችኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ ተነሳሁ። በዚያው ምሽት ወታደሮች ለሁለተኛ ጊዜ እኔን ለማሰር ወደ ቤታችን መጡ። ቤት ሲያጡኝ እየተጣደፉ ወደ አየር ማረፊያው ሄዱ። እዚያ በደረሱበት ሰዓት ግን የተሳፈርኩበት አውሮፕላን ተነስቶ ነበር።

 ሜሪላንድ ስደርስ ወላጆቼን ያስጠኗቸው ሄይዉድ እና ጆን ዋርድ የተባሉት ሚስዮናውያን ተቀበሉኝ። ከአምስት ወር በኋላ አቅኚ የመሆን ግቤ ላይ መድረስ ቻልኩ። የሄይዉድና የጆን ልጅ የሆነችው ሲንዲ አቅኚ ስለነበረች ጥሩ የአገልግሎት ጓደኛ ሆናኛለች፤ በአገልግሎት ብዙ አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል።

የአቅኚነት አገልግሎት ጓደኛዬ ከሆነችው ከሲንዲ ዋርድ ጋር

በቤቴል በአምላክ አገልግሎት መጠመድ

በኒው ዮርክ፣ ዎልኪል በሚገኘው ቤቴል ከባለቤቴ ጋር ስናገለግል

 በ1979 የበጋ ወራት በኒው ዮርክ ያለውን ቤቴል ስጎበኝ ዌስሊ ፓርከር ከተባለ ወንድም ጋር ተዋወቅኩ። ያለው ግሩም ባሕርይና መንፈሳዊ ግቦቹ ማረኩኝ። በ1981 ትዳር የመሠረትን ሲሆን ወደ ዎልኪል፣ ኒው ዮርክ ተዛውሬ ከዌስሊ ጋር በቤቴል ማገልገል ጀመርኩ። በቤት ጽዳትና በደረቅ እጥበት አገልግሎት፣ በኋላም በኮምፒውተር ዲፓርትመንት ውስጥ ከሜፕስ ጋር የተያያዘ ሥራ ከሚሠራው ቡድን ጋር ሠርቻለሁ። በቤቴል ማገልገሌ በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በመሉ ለመጠመድና የዕድሜ ልክ ጓደኞች ለማፍራት አስችሎኛል።

 በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን በኢትዮጵያ ያሉት ቤተሰቦቼ ከባድ ስደት ውስጥ መሆናቸው በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። ታስረው የነበሩት እህቶቼና ወንድሜ ከእስር አልተለቀቁም ነበር። b እስር ቤቱ ምግብ ስለማያቀርብ እናቴ በየቀኑ ምግብ እያዘጋጀች ማድረስ ነበረባት።

 በዚያ አስጨናቂ ጊዜ ይሖዋ መጠጊያ ሆኖልኛል፤ የቤቴል ቤተሰብ አባላትም ማጽናኛና ማበረታቻ ሰጥተውኛል። (ማርቆስ 10:29, 30) አንድ ቀን ወንድም ጆን ቡዝ እንዲህ አለኝ፦ “በቤቴል በማገልገልሽ በጣም ደስተኞች ነን። እዚህ መገኘት የቻልሽው ይሖዋ ስለባረከሽ ነው።” c እነዚህ ደግነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ይሖዋ ኢትዮጵያን ለቅቄ ለመውጣት ያደረግኩትን ውሳኔ እንደባረከልኝና ቤተሰቤን እንደሚንከባከብልኝ እርግጠኛ እንድሆን አድርገውኛል።

በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማገልገል

 ጥር 1989፣ እርጉዝ እንደሆንኩ አወቅን። መጀመሪያ ላይ ተደናግጠን ነበር! ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ጭንቀታችን በደስታ ተተካ። ያም ሆኖ ‘ጥሩ ወላጆች እንሆን ይሆን? የት ነው የምንኖረው? ከቤቴል ከወጣን በኋላ ቤተሰባችንን እንዴት ነው የምናስተዳድረው?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦን ነበር።

 ሚያዝያ 15, 1989 ዕቃችንን መኪናችን ላይ ጭነን ወደ ኦሪገን አመራን፤ በዚያ በአቅኚነት ለመቀጠል አስበን ነበር። እዚያ ከደረስን ብዙም ሳይቆይ ግን አንዳንድ ወዳጆቻችን ለእኛ በጎ በማሰብ አቅኚ መሆናችን ምክንያታዊ እንዳልሆነ ነገሩን። እውነት ነው፣ በቁሳዊ ያለን ጥቂት ከመሆኑም ሌላ በቅርቡ ልጃችን ይወለዳል። ምን ብናደርግ ይሻል ይሆን? ልክ በዚያ ጊዜ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን ወንድም ጋይ ፒርስ እና ባለቤቱ ፔኒ ሊጠይቁን መጡ። d እነሱም በግባችን እንድንጸና አበረታቱን። ስለዚህ ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን። (ሚልክያስ 3:10) የመጀመሪያው ልጃችን ለሙኤል እንዲሁም ሁለተኛው ልጃችን ጄደን ከተወለዱ በኋላም በአቅኚነት ማገልገላችንን ቀጠልን።

 ልጆቻችን ገና ትናንሽ እያሉ በአቅኚነት ያሳለፍነው ጊዜ በጣም አስደሳች ነበር። የአቅኚነት አገልግሎት በአካባቢያችን ላሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር መንፈሳዊ እውነቶችን መንገር የምንችልበት ብዙ አጋጣሚ ሰጥቶናል። (ዘዳግም 11:19) ሦስተኛው ልጃችን ጄፈት ሲወለድ ግን ለተወሰነ ጊዜ አቅኚነት ለማቆም ተገደድን።—ሚክያስ 6:8

ልጆቻችን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ማስተማር

 ወላጆች እንደመሆናችን መጠን ያለብን ትልቁ ኃላፊነት ልጆቻችን በግለሰብ ደረጃ ይሖዋ እውን እንዲሆንላቸውና ከእሱ ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱ መርዳት እንደሆነ ተገነዘብን። ለዚህም ስንል፣ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን አጓጊ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አደረግን። ልጆቻችን ገና ትናንሽ እያሉ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባሉትን መጻሕፍት አብረን እናነብ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹን ታሪኮች በድራማ መልክ እንሠራቸዋለን። በቤቱ ውስጥ ያለሁት ሴት እኔ ብቻ ስለሆንኩ ስለ ኤልዛቤል የሚናገረው ታሪክ ላይ ኤልዛቤልን ሆኜ የምተውነው እኔ ነበርኩ። ልጆቻችን እኔን ከሶፋ ላይ መጣልና እንደ ውሻ ሆነው መተወን ያስደስታቸው ነበር! ከቤተሰብ አምልኮ በተጨማሪ ዌስሊ ልጆቻችንን ለየብቻ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናቸው ነበር።

 ልጆቻችንን እንወዳቸውና እንንከባከባቸው ነበር፤ ደግሞም ይሖዋ ቤተሰባችን እርስ በርሱ የሚቀራረብ እንዲሆን እንዲረዳን እንጸልይ ነበር። ልጆቻችን ከፍ እያሉ ሲሄዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሙያዎችን አስተማርናቸው። ዕቃ ያጥቡ፣ ክፍላቸውን ያጸዱና ልብሳቸውን ያጥቡ ነበር። ምግብ ማብሰልም ተምረዋል።

 መማር ያስፈለጋቸው ልጆቻችን ብቻ አልነበሩም፤ እኛ ወላጆችም መማር አስፈልጎናል። ስሜታዊ ሆነን ለልጆቻችንም ሆነ እርስ በርስ ደግነት የጎደላቸው ቃላት የተናገርንባቸው ጊዜያት አሉ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ትሑት በመሆን ይቅርታ እንጠይቃለን።

 በየጊዜው የጉባኤ ወንድሞችንና እህቶችን፣ ቤቴላውያንን፣ ሚስዮናውያንን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው የሚያገለግሉትን ቤታችን እንጋብዝ ነበር። (ሮም 12:13) ከእንግዶች ጋር ስንጨዋወት ልጆቻችን ወደሌላ ክፍል ሄደው እንዲጫወቱ አናደርግም። ከዚህ ይልቅ አብረውን ሆነው እንዲጫወቱና ተሞክሮ እንዲያዳምጡ እናደርጋለን። እንዲያውም በአብዛኛው ስላደረግናቸው ጭውውቶች በደንብ የሚያስታውሱት ከእኛ ይልቅ ልጆቻችን ናቸው።

 እኔና ዌስሊ በይሖዋ አገልግሎት አስደሳች ሕይወት ለመምራት የቻልነውን ሁሉ ጥረት አድርገናል። ለምሳሌ አስቀድመን ዕቅድ በማውጣት እንዲሁም ገንዘብና የእረፍት ቀን በማጠራቀም የተለያዩ አገሮችን እንጎበኛለን። በሄድንበት አገር ሁሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንጎበኛለን፣ ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን እንዲሁም በአገልግሎት እንካፈላለን። ይህም ለዓለም አቀፉ የይሖዋ ድርጅት ያለን አድናቆት እንዲጨምርና ቤተሰባችን ይበልጥ እንዲቀራረብ አድርጓል።

በ2013 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤት በቤተሰብ ሆነን ስንጎበኝ

በአገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራታችንን ቀጠልን

 በምንኖርበት አካባቢ ብዙ ስፓንኛ ተናጋሪዎች እንዳሉና የሚመሠክርላቸው በቂ ሰው እንደሌለ አስተዋልን። በወቅቱ ልጆቻችን ገና ትናንሽ የነበሩ ቢሆንም በስፓንኛ ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ተዛውረን ለማገልገል እንዳሰብን ወንድም ፒርስን አማከርነው። እሱም ፈገግ ብሎ “መቼም ዓሣ አጥማጆች ከሆናችሁ የምትሄዱት ዓሣዎች ወዳሉበት ነው” አለን። እኛም በተሰጠን ማበረታቻ መሠረት በዉድበርን፣ ኦሪገን ወደሚገኝ ስፓንኛ ቋንቋ ጉባኤ ተዛወርን። በዚያም እድገት የሚያደርጉ በርካታ ጥናቶችን የመምራት፣ አንዳንዶቹን እንዲጠመቁ የመርዳትና ትንሽ የነበረው የስፓንኛ ቡድን አድጎ ጉባኤ ሲሆን የማየት ግሩም አጋጣሚ አግኝተናል።

 በአንድ ወቅት ዌስሊ ከሥራ ተቀነሰ፤ ከዚያም ባገኘው አዲስ ሥራ ምክንያት ወደ ካሊፎርኒያ ተዛወርን። ከሁለት ዓመት በኋላ እኔ፣ ለሙኤልና ጄደን አቅኚነት ለመጀመር ወሰንን። በ2007 ከልጆቼ ጋር በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አግኝቻለሁ። በአቅኚዎች ትምህርት ቤት ከተካፈልን ብዙም ሳይቆይ፣ በምንኖርበት አካባቢ ብዙ አረብኛ ተናጋሪ ሰዎች እንዳሉ አስተዋልን። በመሆኑም ቤተሰባችን ለ13 ዓመት በስፓንኛ ቋንቋ መስክ ላይ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በአረብኛ ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ለመዛወር ወሰነ። በአካባቢያችን ለሚገኙ አረብኛ ተናጋሪ ስደተኞች እውነትን ማስተማር በመቻላችን ተደስተናል፤ በሌሎች አገሮች በሚደረጉ ልዩ የስብከት ዘመቻዎች በመካፈል በዚሁ ቋንቋ የመስበክ አጋጣሚም አግኝተናል። አሁንም በሳን ዲዬጎ፣ ካሊፎርኒያ በአረብኛ ቋንቋ መስክ በአቅኚነት እያገለገልን ነው።

 ዌስሊ ጥሩ ባልና ጎበዝ የቤተሰብ ራስ ነው። ለይሖዋ ድርጅት ጥልቅ አክብሮት አለው። በቤቴልም ሆነ በጉባኤ ስላለው አሠራር ምንም አሉታዊ ነገር ተናግሮ አያውቅም። እንዲያውም ሁሌም የሚጠቅሰው አዎንታዊ ነገር አያጣም። አብሮኝ የመጸለይ ልማድ አለው፤ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የሚያቀርበው ጸሎት እንድጽናናና እንድረጋጋ ይረዳኛል።

 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት፣ ልጆች በማሳደግና ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልጉባቸው ጉባኤዎች በማገልገል ያሳለፍነውን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስብ በደስታ እሞላለሁ። ይሖዋ እሱን ለማገልገል ቅድሚያ የሚሰጡትን እንደሚባርክ በግልጽ ማየት ችለናል፤ ምንም ነገር ጎድሎብን አያውቅም። (መዝሙር 37:25) ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ያደረኩት ውሳኔ ምንም የማያስቆጭ እንደሆነ አይቻለሁ።—መዝሙር 84:10

ፎቶግራፉ ላይ አብረውኝ ያሉት ከግራ ወደ ቀኝ፦ ጄፈት፣ ለሙኤል፣ ጄደን እና ዌስሊ

a ወንድም ሊንክ በኢትዮጵያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይከታተል በነበረው በኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ያገለግል ነበር።

b ከአራት ዓመት በኋላ እህቶቼና ወንድሜ ከእስር ተለቀቁ።

c ወንድም ቡዝ በ1996 ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል።

d ወንድም ፒርስ ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በ2014 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቋል።