በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ታመን—እሱም ይረዳሃል

በይሖዋ ታመን—እሱም ይረዳሃል

በይሖዋ ታመን—እሱም ይረዳሃል

ኤድመንት ሽሚት እንደተናገሩት

ጥቅምት 1943 ኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ስቀርብ ከላይ ያለው ምክር ወደ አእምሮዬ መጥቶ ነበር። ሃያ አምስት ዓመት ሳይሞላኝ በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት ወደ አራት ለሚጠጉ ዓመታት ታስሬያለሁ። እንደ ጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥ አድርጌ ለመታዘዝ’ ቁርጥ አቋም ወስጄ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ስለዚህ ጉዳይ ከመናገሬ በፊት በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ሊኖረኝ የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።

ሚያዝያ 23, 1922 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ በሚገኘው የአባቴ ዳቦ ቤት አናት ላይ ባለው መኖሪያ ቤታችን ውስጥ ተወለድኩ። ከአራት ወር በኋላ አባቴ ኤድመንት፣ በሳንደስኪ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘውና ከቤታችን 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ባለችው በሴዳር ፖይንት በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘ።

በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ “[የአምላክን] ንጉሥና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። በቀጣዩ እሁድ አባቴ በስብከቱ ሥራ መካፈል የጀመረ ሲሆን ሕይወቱ እስካለፈችበት እስከ ሐምሌ 4, 1988 ድረስ ለ66 ዓመታት መስበኩን ቀጥሎ ነበር። እናቴ ሜሪም በ1981 እስካረፈችበት ጊዜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ነበረች።

ከወላጆቼ ጋር አምላክን ማምለክ ጀመርኩ

ቤተሰባችን ክሌቭላንድ በሚገኘው በፖላንድ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ውስጥ ይሰበሰብ ነበር። ሁልጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በርካታ ልጆች ከትልልቆቹ ጋር በመሆን ከቤት ወደ ቤት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ እንካፈል ነበር። እሁድ እሁድ ደግሞ ወላጆቻችን በዋናው የመሰብሰቢያ አዳራሻችን የሚሰጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ያዳምጡ ነበር። በዚሁ ሰዓት ተሞክሮ ያለው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ወደ 30 የምንጠጋ ልጆችን የአምላክ በገና (ዘ ሃርፕ ኦቭ ጎድ) * በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ነበር። ብዙም ሳይቆይ እኔ ራሴ ጥናቶችን መምራት የጀመርኩ ሲሆን ጥሩ ውጤትም አግኝቼ ነበር።

በሐምሌ 1931 ታናሽ ወንድሜን ፍራንክን ጨምሮ ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ባደረጉት ሌላ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘ፤ በዚህ ጊዜ የተካፈልነው በስተደቡብ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኮሎምበስ በተደረገው ስብሰባ ላይ ነበር። ይህ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም በሙሉ ልብ የተቀበሉበት ጊዜ ነበር። (ኢሳይያስ 43:10-12) በዚያን ወቅት፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ጆሴፍ ራዘርፎርድ በሚያቀርበው ልዩ ንግግር ላይ እንዲገኙ ሰዎችን ለመጋበዝ በተደረገው የስብከት እንቅስቃሴ ተካፍያለሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላሉት ከ79 ለሚበልጡ ዓመታት ሕይወቴ ያተኮረው ይሖዋን ከሕዝቦቹ ጋር በማገልገል ላይ ነው።

በአስቸጋሪ ጊዜያትም የሚክስ አገልግሎት ማከናወን

በ1933 ዓለም በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ተዘፍቃ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ማለትም ከሠራተኛው አንድ አራተኛው ሥራ አጥ ሆኖ ነበር። በከተማዎች ውስጥ ኪሳራ ስለደረሰ ለአረጋውያንና ለድሆች ይሰጥ የነበረው የገንዘብ ድጎማ ቀረ። ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች እርስ በርስ ይረዳዱ ነበር። እሁድ እሁድ ቤተሰቦቼ በዳቦ ቤታችን የተጋገሩ ዳቦዎችንና የተለያዩ ብስኩቶችን ወደ ስብሰባ ቦታዎች በመውሰድ ለወንድሞች ይሰጡ ነበር። አባታችን በወሩ መጨረሻ ላይ ወጪውን ሁሉ ከከፈለ በኋላ ትርፉን ብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ይልክ ነበር። የሚልከው ገንዘብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማተሙ ሥራ እንደሚውል ያውቅ ነበር።

በእነዚህ ዓመታት የሬዲዮ ማሰራጫዎች አገልግሎታችንን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከ400 በላይ የሚሆኑ የሬዲዮ ጣቢያዎች በትልልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች አሰራጭተዋል። በ1930ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ብሩክሊን በሚገኘው ፋብሪካ ውስጥ የሸክላ ማጫወቻዎችን ያመርቱ ብሎም የተቀዱ ንግግሮችን ያዘጋጁ ነበር። ንግግሮቹን በአገልግሎታችን ላይ እንጠቀምባቸው የነበረ ሲሆን የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች ምን ያህል ጊዜ እንዳሰማንና ምን ያህል ሰዎች እንዳዳመጡ ሪፖርት እናደርግ ነበር።

በ1933 አዶልፍ ሂትለርና የናዚ ፓርቲ በጀርመን ሥልጣን ተቆናጠጡ። በዚያ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ለከባድ ስደት ተዳረጉ። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14) በጀርመን ያሉት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ወይም ሃይል ሂትለር (ሂትለር አዳኝ ነው) ለማለት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወህኒ ገብተዋል፤ አሊያም በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተጥለዋል። ብዙዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ በመገደዳቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተፈጸመባቸው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የተነሳ ብዙዎች ከእስር ተለቀው ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ሕይወታቸው አልፏል። ሆኖም ብዙ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለደረሰው በደል የሚያውቁት ነገር የለም።

በ1940 ዲትሮይት፣ ሚሺገን ውስጥ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘን። ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን ለማሳየት እዚያው ስብሰባ ላይ ሐምሌ 28 ተጠመቅኩ። ከዚያ የአውራጃ ስብሰባ አንድ ወር ቀደም ብሎ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለባንዲራ ሰላምታ አለመስጠት ሕገ ወጥ ድርጊት እንደሆነና እንዲህ የሚያደርግ ተማሪ ከትምህርት ቤት እንደሚባረር የሚደነግግ ሕግ አውጥቶ ነበር። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ምን አደረጉ? አብዛኞቹ ልጆቻቸውን ለማስተማር የራሳቸውን ትምህርት ቤቶች ያቋቋሙ ሲሆን ትምህርት ቤቶቹ የአምላክ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ተብለው ይጠሩ ነበር።

በ1939 በመስከረም ወር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ሲቀሰቀስ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ተቀጣጠለ። ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስለ ገለልተኝነት አቋማችን ትክክለኛ ግንዛቤ ባልነበራቸው ወጣቶችና አዋቂዎች እንግልት እንዲሁም ድብደባ ደርሶባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ከ1940 እስከ 1944 ባለው ጊዜ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከ2,500 በላይ የዓመፅ ድርጊትና ጥቃት እንደተፈጸመ ሪፖርት ተደርጓል። ጃፓን ታኅሣሥ 7, 1941 ፐርል ሃርበር በተባለችው ወደብ ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ስደቱ ይበልጥ ተባባሰ። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኜ ማገልገል ጀምሬ ነበር። ገንዘብ አጠራቅሜ 7 ሜትር ርዝመት ያለው ተንቀሳቃሽ ቤት ከገዛሁ በኋላ በሉዊዚያና ለማገልገል ከሌሎች ጋር ወደዚያ አቀናን።

በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል የተነሳው ስደት

ጄንሬት በምትባል ከተማ አቅራቢያ የአካባቢውን ነዋሪዎች አስፈቅደን ተንቀሳቃሽ ቤታችንን በአንድ የለውዝ እርሻ ላይ አቆምን። አንድ ቅዳሜ ቀን ከመንገድ ወደ መንገድ ለማገልገል ወሰንን፤ ይሁንና የፖሊስ አዛዡ ፖሊስ ልኮ እንደ እስረኞች ወደ ከተማው ማዘጋጃ ቤት አስመጣን። ከዚያ ስንወጣ 200 የሚያክሉ ለረብሻ የተዘጋጁ ሰዎች ውጪ እየጠበቁን ቢሆንም ፖሊሶቹ ምንም ጥበቃ ሊያደርጉልን አልሞከሩም። ደስ የሚለው ግን የተሰበሰቡት ሰዎች እንድናልፍ መንገድ ለቀቁልን። ያጋጠመንን ለእምነት አጋሮቻችን ለመንገር በማግስቱ በአቅራቢያችን ወዳለው ባቶን ሩዥ ወደሚባል ትልቅ ከተማ ሄድን።

ወደ ጄንሬት ስንመለስ “እባካችሁ ወደ ዘይት ማውጫው ሠራተኞች ካምፕ መጥታችሁ አነጋግሩኝ” የሚል መልእክት ተጎታች ቤታችን በር ላይ ተለጥፎ አገኘን። ከታች “ኢ. ኤም. ቮን” የሚል ስም ተጽፎበት ነበር። እዚያም ሄደን ሚስተር ቮንን ያገኘነው ከመሆኑም በላይ እሱና ባለቤቱ ምግብ ጋበዙን። ቅዳሜ ዕለት ተሰብስበው ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱና ጓደኞቹ እንደነበሩና ችግር ቢፈጠር ኖሮ እኛን ለመርዳት ተዘጋጅተው እንደነበር ነገረን። እኛም ለማበረታቻውና ላደረገልን ድጋፍ ምስጋናችንን ገለጽንለት።

በሚቀጥለው ቀን መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች መጥተው የያዙን ከመሆኑም ሌላ ጽሑፎቻችንን ወረሱብን። የተጎታች ቤቴን ቁልፍ የወሰዱብኝ ሲሆን ለ17 ቀናት በጣም ጥቂት ምግብ እየተሰጠኝ በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን እንድታሰር አደረጉ። ሚስተር ቮን ሊረዳን የሞከረ ቢሆንም አልተሳካለትም። ታስረን እያለ ረብሸኞቹ ንብረታችንን የዘረፉን ሲሆን ተጎታች ቤቴንና የቀረውን ነገር በሙሉ አቃጠሉት። ይሖዋ በቅርቡ ለሚያጋጥመኝ ነገር እያዘጋጀኝ እንዳለ በወቅቱ አልተገነዘብኩም ነበር።

በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል መታሰር

ከሉዊዚያና ከተመለስኩ ከአንድ ወር በኋላ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ኒው ዮርክ በምትገኘው በኦሊያን ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ እያለሁ በወታደራዊ አገልግሎት እንድካፈል መንግሥት ጥሪ አቀረበልኝ፤ በኋላ ላይ ግን በሕሊናዬ ምክንያት በዚህ አገልግሎት ያለመካፈል መብት ተሰጠኝ። ይሁንና የተደረገልኝን የአካልና የአእምሮ ጤና ምርመራ በማለፌ በማስረጃ ወረቀቴ ላይ “የመኮንኖች ማሠልጠኛ ማዕከል እጩ” የሚል ማኅተም ተደረገበት።

ከዚያ በኋላ ለአንድ ዓመት ገደማ በአቅኚነት ሥራ መቀጠል የቻልኩ ቢሆንም በ1943 አገልግሎቴን አቁሜ ወታደራዊ ሥልጠና ለመጀመር ሪፖርት ባለማድረጌ በፌዴራል የምርመራ ቢሮ (FBI) ተይዤ በሚቀጥለው ሳምንት ኒው ዮርክ በምትገኘው በሲራክዩስ ከተማ ባለው ፍርድ ቤት እንድቀርብ ታዘዝኩ። ወዲያውኑ ክስ የተመሠረተብኝ ሲሆን ከሁለት ቀን በኋላ ችሎት ፊት እንድቀርብ ተቀጠርኩ።

ፍርድ ቤት ስቀርብ ጠበቃ ማቆም አላስፈለገኝም። ምክንያቱም እኛ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ፍርድ ቤት በምንቀርብበት ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን በተገቢው መንገድ እንዴት ማስረዳት እንደምንችል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሥልጠና ተሰጥቶን ነበር። በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩትን ምክር ደጋግሜ አስታውሰው ነበር። እንዲያውም አቃቢ ሕግ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከእነሱ የተሻለ ሕጉን እንደሚያውቁ በምሬት ተናግረዋል! እንደዚያም ሆኖ እማኝ ዳኞቹ ጥፋተኛ ነህ ብለው ፈረዱብኝ። በመጨረሻም ዳኛው ‘መናገር የምትፈልገው ነገር አለ?’ ብለው ሲጠይቁኝ “ዛሬ መንግሥት የአምላክን አገልጋዮች ስለሚይዝበት መንገድ መልስ ለመስጠት በአምላክ ፊት ቀርቧል” አልኳቸው።

ቺሊካቴ፣ ኦሃዮ በሚገኘው የፌዴራል እስር ቤት አራት ዓመት እንድታሰር ተፈረደብኝ። እስር ቤቱ ውስጥ የአንደኛው ባለሥልጣን ጸሐፊ ሆኜ እንድሠራ ተመደብኩ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አንድ ልዩ መርማሪ ከዋሽንግተን ዲ. ሲ. መጥቶ የሃይደን ኮቪንግተንን ጉዳይ እየመረመሩ እንደሆነ ነገረኝ። ሚስተር ኮቪንግተን የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ የሚሟገት ጠበቃ የነበረ ሲሆን በአሜሪካ ውስጥ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ በጣም ታዋቂ ከሆኑት አንቱ የተባሉ ጠበቆች አንዱ ነበር።

መርማሪው፣ ዳኒ ኸርታዶ እና ኤድመንት ሽሚት የተባሉትን እስረኞች የተሟላ መዝገብ እንደሚፈልግ ተናገረ። አለቃዬ በመደነቅ “የሚገርም አጋጣሚ ነው! ይሄ እኮ ሚስተር ሽሚት ነው” አለ። መርማሪው ተልእኮው ሚስጥር የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን እኛ እንዳወቅንበት ተረዳ። በዚህ ምክንያት ወዲያውኑ ይህን ሥራ ለቅቄ ኩሽና ውስጥ እንድሠራ ተደረገ።

አቅኚ፣ ቤቴላዊ ከዚያም ባለትዳር መሆን

መስከረም 26, 1946 በአመክሮ ከተለቀቅኩ በኋላ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ሃይላንድ ፓርክ በተባለው ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት ማገልገሌን ቀጠልኩ። በኋላም መስከረም 1948 ለረጅም ጊዜ ስመኘው የነበረው ግቤ ላይ ደረስኩ። ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራችን የምንጠቀምባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚዘጋጁበት በብሩክሊን ቤቴል በዳቦ ጋጋሪነት እንዳገለግል ተጠራሁ። በግሌንዴል ባለ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ በዋና ጋጋሪነት የማከናውነውን ሥራ ወዲያውኑ ለቅቄ ቤቴል ገባሁ።

ከሰባት ዓመት በኋላ በ1955 በአውሮፓ ውስጥ በርካታ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ተካሂደው ነበር። ቤተሰቦቼ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ የሚያስፈልገኝን ወጪ ሸፍነውልኝ ነበር። በለንደን፤ በፓሪስና በሮም በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ በጣም አስደስቶኛል፤ በተለይ ደግሞ ሂትለር ወታደሮቹ በፊቱ ሲያልፉ በኩራት ይቃኝበት በነበረው ኑረምበርግ፣ ጀርመን በሚገኘው ትልቅ ስታዲየም ውስጥ ከ107,000 በላይ ከሚሆኑ ተሰብሳቢዎች ጋር መሰብሰብ እጅግ ያስደስት ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል ሂትለር ጠራርጎ እንደሚያጠፋቸው ሲዝትባቸው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። ከእነዚህ ወንድሞች ጋር አብሮ መሰብሰብ እንዴት ያለ አስደሳች አጋጣሚ ነው!

ኑረምበርግ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተዋወቅኳት ብሪጊቴ ገርቪን ከተባለች አንዲት ጀርመናዊት ወጣት ጋር ተዋደድን። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጋባን ሲሆን ወላጆቼ አቅራቢያ ለመኖር ወደ ግሌንዴል ሄድን። የመጀመሪያው ልጃችን ቶም በ1957፣ ሁለተኛው ልጃችን ዶን በ1958 እንዲሁም ሴት ልጃችን ሳቢና በ1960 ተወለዱ።

ትርጉም ያለው አርኪ ሕይወት

አንዳንዶች አምላክን ለማገልገል ስል የወጣትነት ሕይወቴን በእስርና በስደት ማሳለፌ ይቆጨኝ እንደሆነ ይጠይቁኛል። በፍጹም አይቆጨኝም! እንዲያውም አምላክ ከብዙ ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር አብሬ እንዳገለግለው መብት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ። ተሞክሮዬም ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡና ከእሱ ጋር ተጣብቀው እንዲኖሩ እንደሚያበረታታ ተስፋ አደርጋለሁ።

በርካታ የአምላክ አገልጋዮች እሱን ለማገልገል ሲሉ ከባድ መከራ ይደርስባቸዋል። ታዲያ ይህ እንድንጠብቀው የተነገረን ነገር አይደለም? መጽሐፍ ቅዱስ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ሆኖም “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” የሚለው በ⁠መዝሙር 34:19 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በሉዊዚያና ስናገለግል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዋናው መሥሪያ ቤት በዳቦ ጋጋሪነት ሳገለግል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከብሪጊቴ ጋር