በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በባሕር ዳርቻ አካባቢ ያሳለፍነው ዕለት

በባሕር ዳርቻ አካባቢ ያሳለፍነው ዕለት

ከግሬኔዳ የተላከ ደብዳቤ

በባሕር ዳርቻ አካባቢ ያሳለፍነው ዕለት

በውጪ አገር ሚስዮናዊ ሆነህ እንድታገለግል ብትመደብ ደስታህ ወደር የሌለው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ለማወቅ እንደሚጓጓ ሕፃን አንተም ሕዝቡ፣ አካባቢውና በአገልግሎት ላይ የምታገኘው ተሞክሮ ምን ሊመስል እንደሚችል ለማወቅ ትጓጓለህ።

እኔና ባለቤቴ ውብ ጠረፍ ባላት ግሬኔዳ በተመደብን ጊዜ በዚያ ያሉት ወደ 45 የሚጠጉ የባሕር ዳርቻዎች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ቀን ከሌት እናስብ ነበር። ይሁን እንጂ ከእነዚህ የባሕር ዳርቻዎች በአንዱ አስደሳች ቀን የምናሳልፍበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አልነበረም፤ ይበልጥ የተደሰትነው ግን በፀሐይዋና በማዕበሉ ሳይሆን በሰዎቹ ነበር።

በግሬኔዳ ያለው ቤታችን ለግራንድ አንሴ የባሕር ዳርቻ ቅርብ ነው፤ ሆኖም ብዙ የሚታይ ነገር ስላለ በዚያ መንገድ መንዳት ልዩ ስሜት ይፈጥራል። ጠመዝማዛ በሆነው መንገድ ስንጓዝ ከምናስበው በላይ እጅግ ውብ የሆነ ተፈጥሮ እንመለከት ነበር። ከኮረብታዎቹ ሥር ያሉት ስፍራዎች ያላቸውን ልምላሜ መግለጽ ያቅታል። እያንዳንዱን ኩርባ ታጥፈን ብቅ ስንል ተራሮች፣ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ፣ ፏፏቴዎችና ከርቀት የሚታየው የተንጣለለው ውቅያኖስ ይቀበሉን ነበር። ቱሪስቶች ከመላው ዓለም ይህን ቦታ ለመጎብኘት መምጣታቸው የሚያስደንቅ አይደለም! በአካባቢው የሚታየው ተፈጥሯዊ ውበት እጅግ የሚማርክ ከመሆኑ የተነሳ አንድ አሽከርካሪ ትኩረቱ እንዳይሰረቅ መጠንቀቅ አለበት። መንገዶቹ የተጠማዘዙ አልፎ ተርፎም ጠባብ በመሆናቸው መኪናዎች ሳይጋጩ መተላለፍ መቻላቸው የሚገርም ነው።

ወደ ግራንድ አንሴ የባሕር ዳርቻ በሚወስደው መንገድ ላይ ወደሚገኘውና አውራጃ ስብሰባ ወደምናካሂድበት አንድ የንግድ ማዕከል ደረስን። ብዙም ሳይቆይ ወደ 600 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች አብረው አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍና መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር ተሰበሰቡ። በተለይ ዕለቱ ሌስሊ እና ዳፍኒ ለሚባሉ በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ ባልና ሚስት ልዩ ትርጉም ነበረው። ሌስሊ የሚጠመቁት ያን ዕለት ነበር። ዳፍኒ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር የሆኑት በ1958 ስለነበር ይህን ዕለት ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠብቁት ኖረዋል።

ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ የሚከናወነው ጥምቀት ለይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ትርጉም አለው። አንድ ሰው ይህን እርምጃ የሚወስደው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አግኝቶ የተማረውን በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ሲያደርግ ነው። ስለዚህ ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን በሕዝብ ፊት የሚያሳይበት ሥነ ሥርዓት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ምን እንደሚያስተምር የሚያብራራ ንግግር የማቅረብ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። በንግግሩ መጨረሻ ላይ ሌስሊና ሌሎች ሁለት ተጠማቂዎች ቆሙ። ሌስሊ ግሩም ሆኖ የተተኮሰ ነጭ ሸሚዝ ለብሰው ክራቫት አስረዋል፤ ፊታቸውም ላይ ብሩሕ ፈገግታ ይነበባል። “ከኃጢአታችሁ ንስሐ ገብታችሁ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችሁን ወስናችኋል?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩላቸው። ሌስሊም ሆኑ ሌሎቹ ተጠማቂዎች ከልብ በመነጨ ስሜት “አዎን!” ብለው ሲመልሱ በእነሱ ላይ የሚታየውን ቅንነትና ለአምላክ የማደር ባሕርይ ማስተዋል ቀላል ነበር።

በተለይ የሌስሊን የኋላ ታሪክ ሳውቅ ልቤ በአድናቆት ስሜት ተሞላ። ሌስሊ ከባለቤታቸው ጋር ወደ ሌላ ደሴት ለጉብኝት እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ ለብዙ አሥርተ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ግብዣ አልተቀበሉም ነበር። ባልና ሚስቱ ለጉብኝት ወደ ሌላ ደሴት በሄዱበት ጊዜ ሌስሊ ለዳፍኒ “አንቺም ወደ ቤተ ክርስቲያንሽ ሂጂ፤ እኔም ወደ ራሴ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ” አሏቸው። በመሆኑም ሁለቱም የየራሳቸው ሃይማኖቶች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰኑ።

ሌስሊ፣ ዳፍኒን ወደ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ካደረሷቸው በኋላ እሳቸው እዚያው አካባቢ ወደሚገኝ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሄዱ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚካሄደው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሲያልቅ ሌስሊ ባለቤታቸውን ለመውሰድ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጡ። በመንግሥት አዳራሹም ከዚህ በፊት አይተዋቸው የማያውቁ ደግና ተግባቢ የሆኑ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉላቸው። በዚህ ሁኔታም ሌስሊ ልባቸው ተነካ። በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አንድም ሰው አላነጋገራቸውም ነበር። ሌስሊም ለዳፍኒ እንዲህ አሏቸው፦ “ሁለተኛ ወደዚያ ቤተ ክርስቲያን አልሄድም። አንድም ሰው ሌላው ቀርቶ ቄሱ እንኳን ከቁብ አልቆጠሩኝም። ሰላም ያለኝ ሰው የለም። ማንም ሰው ዞር ብሎ ሳያየኝ ገብቼ ወጣሁ።” ሌስሊ ከቤተ ክርስቲያኑ የወጡት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነበር።

ከዚያ በኋላ ሌስሊ የአምላክን ቃል በቁም ነገር ማጥናት ጀመሩ። ይኸው አሁን ለመጠመቅ ተዘጋጅተዋል። የጥምቀት እጩዎቹ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲሄዱ እኛም ተከትለናቸው ሄድን። ውቅያኖሱ ቅርብ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ እንደሚደረገው የመጠመቂያ ገንዳ ማዘጋጀት አላስፈለገም። መንገዱን እንደተሻገርን ውቅያኖሱ ጋ ደረስን።

የግራንድ አንሴ የባሕር ዳርቻ ሦስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ነጭ አሸዋና ከዓመት ዓመት ሰማያዊ ቀለም ባለው ለብ ያለ ውኃ አሸብርቋል። በባሕሩ ዳርቻ የሚዝናኑ ቱሪስቶች ሲያዩን ተገረሙ። ምክንያቱም ወንዶቹ ሸሚዝ ለብሰን ክራቫት አስረናል፤ ሴቶቹ ደግሞ ቀሚስ ለብሰዋል። ሌስሊ ልብሳቸውን ቀይረው ካናቴራና ቁምጣ ለብሰው ነበር። ዳፍኒ እሳቸው ከተጠመቁ ከ50 ዓመት በኋላ ባለቤታቸው ሲጠመቁ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት ይቻላል! ዳፍኒ እንደ ቀትሯ ፀሐይ ፊታቸው ፈክቶ ነበር። ቱሪስቶቹም እንኳን ሳይቀሩ የደስታችን ተካፋዮች ሆነዋል። እያንዳንዱ ተጠማቂ ሲጠመቅ አብረውን ያጨበጭቡ ነበር።

ሰማዩ ጥርት ብሎ የሚታይበት፣ ማዕበሉ በዝግታ የሚንቀሳቀስበትና ነጭ አሸዋ ያለው ይህ የባሕር ዳርቻ ለፈጣሪው ክብር ሲሰጥ ቆይቷል። ሦስቱ አዳዲስ ተጠማቂዎች ተጠምቀው ከውኃው ሲወጡ ደግሞ ይበልጥ ለፈጣሪው ክብር ሰጠ። ፀሐዩ ሰውነታችንን ካሞቀው የበለጠ ተጠማቂዎቹን መመልከት ልባችንን አሞቀው። በእርግጥም ዕለቱ ልዩ ነበር! በባሕሩ ዳርቻ ያሳለፍነው ይህ ቀን በተለይ ለሌስሊና ለዳፍኒ የማይረሳ ዕለት ነው።