በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

የተለመዱት መልሶች፦

▪ “አዎ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው።”

▪ “አምላክ በሥጋ የተገለጠው ኢየሱስን ሆኖ ነው።”

ኢየሱስ ምን ብሏል?

“የምትወዱኝ ቢሆን ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣል።” (ዮሐንስ 14:28) ኢየሱስ፣ እሱና አባቱ እኩል እንዳልሆኑ ተናግሯል።

▪ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው።” (ዮሐንስ 20:17) ኢየሱስ እሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ አልተናገረም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ራሱን የቻለ አካል እንደሆነ ገልጿል።

▪ “እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው።” (ዮሐንስ 12:49) ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ከራሱ ሳይሆን ከአባቱ የመነጨ ነበር።

ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተናገረ እንጂ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ ብሎ አያውቅም። ኢየሱስ ራሱ አምላክ ከሆነ እዚህ ምድር ሳለ ይጸልይ የነበረው ወደ ማን ነው? (ማቴዎስ 14:23፤ 26:26-29) ኢየሱስ ከሌላ አካል ጋር እየተነጋገረ እንዳለ ለማስመሰል እየሞከረ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም!

ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ውስጥ የተለየ ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁት ጊዜ “በቀኜ ወይም በግራዬ የመቀመጡ ጉዳይ . . . አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” ሲል መለሰላቸው። (ማቴዎስ 20:23) ኢየሱስ የጠየቁትን ነገር የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው በተናገረ ጊዜ እየዋሻቸው ነበር? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን የማድረግ ሥልጣን ያለው አባቱ ብቻ እንደሆነ በትሕትና ገልጿል። በተጨማሪም ኢየሱስ ከአባቱ በስተቀር እሱም ሆነ መላእክት የማያውቋቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ተናግሯል።—ማርቆስ 13:32

ኢየሱስ ከአምላክ ያንስ የነበረው ሰው ሆኖ እዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብቻ ነው? አይደለም። ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ በኋላም እንኳ ከአምላክ እንደሚያንስ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አምላክ በክርስቶስ ላይ ሥልጣን እንዳለው’ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 11:3 የ1980 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት “ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ከሆነ በኋላ፣ እግዚአብሔር አብ በሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው፣ ወልድ ራሱ፣ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር በአደረገለት በእግዚአብሔር አብ ሥልጣን ሥር ይሆናል” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 15:28 የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። ከዚህም የተነሳ አባቱን “አምላኬ” በማለት ጠርቶታል።—ራእይ 3:2, 12፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ ገጽ 201-204⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ ከአባቱ በስተቀር እሱም ሆነ መላእክት የማያውቋቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ተናግሯል