በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አልማዝ በድብቅ ታዘዋውርና ከአሠሪዋ ንብረት ትዘርፍ የነበረች ሴት ሐቀኛ ሠራተኛ ለመሆን ያነሳሳት ምንድን ነው? ራሷን ለማጥፋት ከአንዴም ሁለቴ ሞክራ የነበረች ሴት ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት እንድትችል የረዳት ምንድን ነው? የአልኮልና የዕፅ ሱሰኛ የነበረ ሰው ከእነዚህ ጎጂ ሱሶች ለመላቀቅ ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነው? እስቲ እነዚህ ግለሰቦች የሚሉትን ነገር በትኩረት ተመልከት።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ማርገሬት ደቤርን

ዕድሜ፦ 45

አገር፦ ቦትስዋና

የኋላ ታሪክ፦ ውድ ማዕድናትን በድብቅ የምታዘዋውርና ሌባ የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ አባቴ የጀርመን ተወላጅ ሲሆን በኋላ ግን የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (የአሁኗ ናሚቢያ) ዜግነት አግኝቶ ነበር። እናቴ ደግሞ ቦትስዋና ውስጥ የሚገኘው የማንጎሎጋ ጎሳ ተወላጅ ነች። እኔ የተወለድኩት በናሚቢያ በሚገኝ ጎባቢስ በሚባል ከተማ ውስጥ ነው።

በ1970ዎቹ ዓመታት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በናሚቢያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድር የነበረ ከመሆኑም በላይ በከተሞችም ሆነ በመንደሮች ውስጥ የአፓርታይድን ሕጎች በጥብቅ ያስፈጽም ነበር። ወላጆቼ የተለያየ ዘር ያላቸው በመሆኑ እንዲለያዩ ግፊት ተደረገባቸው። በመሆኑም እናቴ እኔን፣ ወንድሞቼንና እህቶቼን ይዛ ወደ ቦትስዋና በመመለስ ጋንሲ ተብሎ በሚጠራ ቦታ መኖር ጀመርን።

በ1979፣ ትምህርቴን እስከጨርስ ድረስ ከአሳዳጊ ወላጆቼ ጋር ለመኖር ቦትስዋና ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ሎባትሴ ተዛወርኩ። ከጊዜ በኋላ በአንድ ጋራዥ ውስጥ የመጋዘን ኃላፊ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። አምላክ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አያሟላም የሚል እምነት ስላደረብኝ አንድ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት ሲል ጥሩም ሆነ መጥፎ ማንኛውንም ነገር ራሱ ማድረግ ይኖርበታል የሚል አመለካከት ነበረኝ።

በሥራ ቦታዬ ኃላፊነት ስለነበረኝ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ከአሠሪዬ ላይ የመኪና መለዋወጫዎችን እሰርቅ ነበር። በከተማው መሃል ምሽት ላይ ባቡር በሚያልፍበት ጊዜ እኔና ጓደኖቼ ባቡሩ ላይ ተሳፍረን ያገኘነውን ነገር ሁሉ እንሰርቃለን። ከዚህም በተጨማሪ አልማዝ፣ ወርቅና ነሐስ በድብቅ አዘዋውር ነበር። ዕፅ መውሰድ የጀመርኩ ከመሆኑም በላይ በጣም ዓመጸኛ ሰው ነበርኩ፤ ብዙ የወንድ ጓደኞችም ነበሩኝ።

በመጨረሻም በ1993 ስሰርቅ በመያዜ ከሥራ ተባረርኩ። “ጓደኞቼ” እነሱም እንዳይያዙ ፍርሃት ስላደረባቸው ራቁኝ። ይህ ያደረጉት ነገር ስሜቴን ጎዳው፤ በመሆኑም ማንንም ሰው ላለማመን ወሰንኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1994 ሚስዮናዊ ከነበሩት ቲምና ቨርጂኒያ ከሚባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። አዲሱ የሥራ ቦታዬ ድረስ እየመጡ ያነጋግሩኝ የነበረ ሲሆን በምሳ የእረፍት ሰዓቴ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምሩኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ እምነት ልጥልባቸው እንደምችል ስለተሰማኝ ቤቴ መጥተው እንዲያስጠኑኝ ፈቃደኛ ሆንኩ።

አምላክን ማስደሰት ከፈለግኩ በአኗኗሬ ላይ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። ለምሳሌ በ⁠1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ በተገለጸው መሠረት ‘ሴሰኞችም ሆኑ ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ተረዳሁ። መጥፎ ልማዶቼን አንድ በአንድ እርግፍ አድርጌ ተውኩ። መስረቅ አቆምኩ። አብረውኝ ካደጉት ዱርዬዎች ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። ከዚያም ከይሖዋ ባገኘሁት ብርታት የወንድ ጓደኞቼን ሙሉ በሙሉ ራቅኳቸው።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ከብዙ ጥረት በኋላ ስሜቴን መቆጣጠርና ልጆቼ በሚያጠፉበት ጊዜ በእነሱ ላይ ከመጮኽ መቆጠብ ቻልኩ። (ኤፌሶን 4:31) ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በሰከነ መንፈስ ለመናገር ጥረት አደርጋለሁ። በዚህ መንገድ መነጋገራችን ተፈላጊውን ውጤት የሚያስገኝ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰብ አንድነታችንን አጠናክሮልናል።

የቀድሞ ጓደኞቼ ሌላው ቀርቶ ጎረቤቶቼም እንኳ እምነት ሊጥሉብኝ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። በእጄ ላይ ያለውን እቃም ሆነ ገንዘብ በታማኝነት የምይዝ ሐቀኛና እምነት የሚጣልብኝ ሠራተኛ ሆኛለሁ። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜዬን ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር የማውል ብሆንም በኢኮኖሚ ራሴን መደገፍ ችያለሁ። በ⁠ምሳሌ 10:22 ላይ የሚገኘው “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” የሚለው ሐሳብ ትክክል መሆኑን ሙሉ በሙሉ እቀበላለሁ።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ግሎሪያ ኤሊሳራራስ ዴ ቾፔሬና

ዕድሜ፦ 37

አገር፦ ሜክሲኮ

የኋላ ታሪክ፦ ራሷን የማጥፋት ሙከራ አድርጋ የነበረች

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ በሚገኝ ሀብታሞች በሚኖሩበት ናዉካልፓን የሚባል አካባቢ ነበር። ከልጅነቴ አንስቶ በጣም ዓመጸኛ የነበርኩ ከመሆኑም ሌላ ጭፈራ ቤቶች መሄድ እወድ ነበር። በ12 ዓመቴ ማጨስ፣ በ14 ዓመቴ መጠጣት፣ በ16 ዓመቴ ደግሞ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከቤት ወጣሁ። አብዛኞቹ ጓደኞቼ ጥሩ ካልሆኑ ቤተሰቦች የመጡ ሲሆን አካላዊ ጥቃትና ስሜታዊ ጉዳት የደረሰባቸው ነበሩ። ሕይወት በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ስለታየኝ ከአንዴም ሁለቴ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር።

አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ ሞዴሊስት ሆኜ መሥራት ጀመርኩ፤ እንዲሁም አንዳንድ ማኅበራዊ ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ ወንዶችን ለማጀብ እቀጠር ነበር። ከዚህም የተነሳ በፖለቲካውና በመዝናኛው ዓለም ካሉ ሰዎች ጋር እገናኝ ነበር። በመጨረሻም አግብቼ ልጆች ወለድኩ፤ ሆኖም በቤተሰቤ ውስጥ ማንኛውንም ውሳኔ የማደርገው እኔ ነበርኩ። በተጨማሪም ማጨስና መጠጣቴን የቀጠልኩበት ከመሆኑም ሌላ በበርካታ ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ እሳተፍ ነበር። በንግግሬ ውስጥ ጸያፍ ቃላትን እጠቀም የነበረ ሲሆን የብልግና ቀልዶችን ማውራትም እወድ ነበር። ደግሞም በጣም ግልፍተኛ ሰው ነበርኩ።

አብዛኞቹ ጓደኞቼ የእኔው ዓይነት ሕይወት ነበራቸው። በእነሱ አስተሳሰብ ሁሉ ነገር የተሟላልኝ ይመስላቸው ነበር። ይሁንና ሕይወቴ ዓላማ የሌለው ስለነበር በውስጤ የሚሰማኝ የባዶነት ስሜት ሊወገድልኝ አልቻለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1998 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ሕይወት ዓላማ እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ። ይሖዋ አምላክ ምድርን መልሶ ገነት የማድረግ ዓላማ እንዳለው፣ የሞቱትን እንደሚያስነሳ እንዲሁም በዚያን ጊዜ እኔም በሕይወት የመኖር አጋጣሚ እንዳለኝ ተገነዘብኩ።

ከዚህም በተጨማሪ ለአምላክ ያለኝን ፍቅር መግለጽ የምችለው እሱን በመታዘዝ እንደሆነ ተረዳሁ። (1 ዮሐንስ 5:3) በሕይወቴ የማንንም መመሪያ ተቀብዬ ስለማላውቅ መጀመሪያ ላይ ይህን ማድረግ ከብዶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ፣ ሕይወቴን በራሴ እየመራሁ መቀጠል እንደማልችል ተገነዘብኩ። (ኤርምያስ 10:23) መመሪያ እንዲሰጠኝ ይሖዋን በጸሎት ጠየቅኩት። ሕይወቴን ከእሱ መመሪያ ጋር ማስማማትና ልጆቼ ከእኔ የተለየ ሕይወት እንዲኖሩ ማስተማር እንድችል እንዲረዳኝ ለመንኩት።

አስፈላጊዎቹን ለውጦች ማድረግ በጣም ከብዶኝ የነበረ ቢሆንም በ⁠ኤፌሶን 4:22-24 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር በሥራ ማዋል ጀመርኩ፦ “ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውን . . . አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ መጣል አለባችሁ፤ . . . እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” ለእኔ አዲሱን ስብዕና መልበስ እንደ ማጨስ ያሉ የሚያረክሱ ልማዶችን መተው እንዲሁም ጸያፍ ቃላትን በማስወገድ አነጋገሬን ማረም ጠይቆብኛል። አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወደ ሦስት ዓመት ገደማ ፈጅቶብኛል።

በተጨማሪም የሚስትነትና የእናትነት ኃላፊነቴን አክብጄ መመልከት ጀመርኩ። በ⁠1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር በሥራ ማዋል ጀመርኩ፦ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው።”

ያገኘሁት ጥቅም፦ በአሁኑ ጊዜ ሕይወት ትርጉም እንዳለው ስለተረዳሁ ይሖዋን ከልብ አመሰግነዋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዳደረግኩና ልጆቼን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ እንደቻልኩ ይሰማኛል። አልፎ አልፎ ድሮ ከሠራኋቸው ነገሮች የተነሳ ልቤ የሚኮንነኝ ቢሆንም ይሖዋ ልቤን ያውቀዋል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት ጋር ተስማምቶ መኖር ከጉዳት እንደጠበቀኝና ውስጣዊ ሰላም እንዳስገኘልኝ ምንም ጥርጥር የለውም።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ጄልሰን ኮሬየ ዲ ኦሊቬራ

ዕድሜ፦ 33

አገር፦ ብራዚል

የኋላ ታሪክ፦ የመጠጥና የዕፅ ሱሰኛ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በብራዚልና በኡራጓይ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው 100,000 ገደማ ነዋሪዎች ባሏት ባዤ በምትባል የብራዚል ከተማ ውስጥ ነው። እርሻና ከብት እርባታ ዋነኞቹ መተዳደሪያዎች ናቸው። ያደግኩት ዱርዬዎች ዓመጽ በሚያስፋፉበትና ድሆች በሚበዙበት ሰፈር ሲሆን የአካባቢው ወጣቶችም ጠጪዎችና የዕፅ ሱሰኞች ነበሩ።

ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ መጠጣት፣ ማሪዋና ማጨስና ሄቪ ሜታል ሙዚቃ ማዳመጥ ጀመርኩ። በአምላክ መኖር አላምንም ነበር። በዓለም ላይ የሚታየው መከራና ሁከት አምላክ እንደሌለ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።

ጊታር እጫወትና የዘፈን ግጥሞችን እጽፍ የነበረ ሲሆን የምጽፈው ሐሳብ እንዲመጣልኝ ስል ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይ መጽሐፍ አነብ ነበር። ያቋቋምኩት የሙዚቃ ባንድ የጠበቅኩትን ያህል ስኬታማ ሳይሆን በመቅረቱ የባሰ የኃይለኛ ዕፆች ሱሰኛ መሆን ጀመርኩ። ከልክ በላይ ዕፅ በመውሰዴ ብሞት እንኳ ግድ አይሰጠኝም ነበር። አመልካቸው የነበሩት አብዛኞቹ ዘፋኞች ሕይወታቸውን ያጡት በዚህ መንገድ ነው።

የዕፅ ሱሴን ለማርካት የሚያስችለኝን ገንዘብ የማገኘው ካሳደገችኝ አያቴ በመበደር ነበር። ገንዘቡን ምን ላይ እንደማውለው ስትጠይቀኝ እዋሻት ነበር። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በመናፍስታዊ ሥራዎች ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩ። ሙዚቃ የማቀናበር ችሎታዬን ያሳድግልኛል ብዬ በማሰብ ከዲያብሎስ ጋር ግንኙነት ባለው የአስማት ሥራ ለመካፈል ጉጉት አደረብኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መገኘት ከጀመርኩ በኋላ አስተሳሰቤ እየተለወጠ ሄደ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ በሕይወት የመቀጠልና እውነተኛ ደስታ የማግኘት ፍላጎት አደረብኝ። የያዝኩት ይህ አዲስ አመለካከት ረጅሙን ጸጉሬን ለመቁረጥ እንድወስን አነሳሳኝ። ጸጉሬን አሳድጌ የነበረው ደስተኛ አለመሆኔንና የዓመጸኝነት ዝንባሌ እንዳለኝ ለማሳየት ነበር። ከዚያም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት አልኮል ከልክ በላይ መጠጣት፣ ዕፅ መውሰድና ማጨስ ማቆም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። በተጨማሪም የሙዚቃ ምርጫዬን መለወጥ እንዳለብኝ ተረዳሁ።

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ወቅት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ። ጥቅሱ ምሳሌ 3:5, 6 ሲሆን ሐሳቡ እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” በዚህ ጥቅስ ላይ ሳስብ፣ እኔ ፈቃደኛ ከሆንኩ ይሖዋ ሕይወቴን እንዳስተካክል እንደሚረዳኝ የእርግጠኝነት ስሜት አደረብኝ።

ያም ሆኖ ለብዙ ጊዜ ስከተለው የነበረውን አኗኗር መለወጥና ከነበሩብኝ የአልኮልም ሆነ የዕፅ ሱሶች መላቀቅ የገዛ እጄን ቆርጦ የመጣል ያህል ከባድ ሆኖብኝ ነበር። (ማቴዎስ 18:8, 9) እነዚህን ለውጦች ደረጃ በደረጃ ማድረግ የማይሆን ነገር መስሎ ታየኝ። በዚህ መንገድ ሊሳካልኝ እንደማይችል ገብቶኝ ነበር። በመሆኑም የነበሩኝን መጥፎ ልማዶች በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርጌ ተውኩ። በተጨማሪም ወደ ድሮ ጎጂ አኗኗሬ ሊመልሱኝ ከሚችሉ ቦታዎችም ሆነ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ራቅሁ።

አልፎ አልፎ በሚሰማኝ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በየቀኑ ባገኘሁት ስኬት ላይ በማተኮር ለራሴ ጥሩ ግምት እንዲኖረኝ ማድረግ ቻልኩ። በይሖዋ ፊት በአካል፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ ሆኖ መገኘት የሚያስከብር እንደሆነ ተሰማኝ። ስለ ቀድሞ አኗኗሬ ከማሰብ ይልቅ የወደፊቱን መመልከት እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ የጸለይኩ ከመሆኑም ሌላ የእሱን እርዳታ አግኝቻለሁ። አንዳንዴ መጥፎ ልማዶቼ ያገረሹብኝ ነበር። ሆኖም አስጠኚዬ በፕሮግራሙ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናኝ ግድ እለው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ገና የስካር መንፈስ ላይ እያለሁም እንኳ አጠና ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውነት ይኸውም ለእኛ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን፣ የሐሰት ሃይማኖትን እንደሚያጠፋ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ያለውን የስብከት ሥራ እንደሚደግፍ ማወቄ ውስጣዊ እርካታ አስገኘልኝ። (ማቴዎስ 7:21-23፤ 24:14፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በእነዚህ እውነታዎች መካከል ያለውን ዝምድና መረዳቴ የተሟላ ግንዛቤ እንዳገኝ አስቻለኝ። በመጨረሻም ሕይወቴን ለአምላክ ለመወሰን ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። አምላክ ላደረገልኝ ነገር ሁሉ አመስጋኝ መሆኔን ማሳየት ፈልጌ ነበር።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በአሁኑ ጊዜ ሕይወቴ ዓላማና ትርጉም እንዳለው ይሰማኛል። (መክብብ 12:13) ሁልጊዜ ከቤተሰቤ ተቀባይ ከመሆን ይልቅ ለእነሱ መስጠት የምችለው ነገር አገኘሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን ጥሩ ነገሮች ለአያቴ ነገርኳት፤ በአሁኑ ጊዜ እሷም ራሷን ለይሖዋ ወስናለች። በርካታ የቤተሰቤ አባላትና ቀደም ሲል አቋቁሜው በነበረው የሙዚቃ ባንድ ውስጥ የነበረ አንድ ሰው ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።

በአሁኑ ጊዜ ባለትዳር ስሆን እኔና ባለቤቴ በአብዛኛው ጊዜያችንን የምናሳልፈው ሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ በመርዳት ነው። ‘በፍጹም ልቤ በይሖዋ መታመንን’ ስለተማርኩ የተትረፈረፈ በረከት እንዳገኘሁ ይሰማኛል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ በሕይወት የመቀጠልና እውነተኛ ደስታ የማግኘት ፍላጎት አደረብኝ”