በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የእኔ ምግብ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነው’

‘የእኔ ምግብ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነው’

በጣም የሚያስደስትህ ነገር ምንድን ነው? ትዳር እንደ መመሥረት፣ ልጆች እንደ ማሳደግ ወይም ጥሩ ወዳጅነት እንደ መመሥረት ያሉት ነገሮች ናቸው? ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር አብሮ መመገብ ያስደስትህ ይሆናል። ይሁንና የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ማለትም ቃሉን ማጥናትና ምሥራቹን መስበክ ይበልጥ የሚክስ ነው ቢባል አትስማማም?

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” በማለት ፈጣሪውን በመዝሙር አወድሷል። (መዝ. 40:8) ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ መከራዎችና የሚያስጨንቁ ነገሮች ቢፈራረቁበትም መለኮታዊውን ፈቃድ መፈጸም ከልብ ያስደስተው ነበር። እርግጥ ነው፣ እውነተኛውን አምላክ በማገልገል ይደሰት የነበረው የይሖዋ አገልጋይ ዳዊት ብቻ አይደለም።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በመዝሙር 40:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በመሲሑ ማለትም በክርስቶስ ላይ እንደተፈጸመ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “[ኢየሱስ] ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፦ ‘“መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ። ሙሉ በሙሉ በሚቃጠል መባና ለኃጢአት በሚቀርብ መባ ደስ አልተሰኘህም።” በዚያን ጊዜ “እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ (ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል እንደተጻፈ) ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አልኩ።’”—ዕብ. 10:5-7

ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ተፈጥሮን በመመልከት፣ ከወዳጆቹ ጋር ጊዜ በማሳለፍና አብሮ በመብላት ይደሰት ነበር። (ማቴ. 6:26-29፤ ዮሐ. 2:1, 2፤ 12:1, 2) ሆኖም ዋነኛ ፍላጎቱ እንዲሁም ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝለት ነገር በሰማይ ያለውን የአባቱን ፈቃድ መፈጸም ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐ. 4:34፤ 6:38) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እውነተኛ ደስታ የሚገኝበትን ሚስጥር ከጌታቸው ተምረዋል። ለሌሎች የመንግሥቱን መልእክት በፈቃደኝነትና በጉጉት አካፍለዋል፤ ይህም ታላቅ ደስታ አስገኝቶላቸዋል።—ሉቃስ 10:1, 8, 9, 17

‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’

ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) ይህን ተልእኮ መፈጸም ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ሄዶ መስበክን፣ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግንና እንዲህ ላሉት ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት  መምራትን ያጠቃልላል። ይህን ሥራ ማከናወን ታላቅ ደስታ ያስገኛል።

ሰዎች ፍላጎት ባይኖራቸው እንኳ ፍቅር ለእነሱ መስበካችንን እንድንቀጥል ይገፋፋናል

ሰዎች ለመልእክታችን ፍላጎት ኖራቸውም አልኖራቸው፣ ከአገልግሎት ደስታ ማግኘታችን የተመካው እኛ ባለን አመለካከት ላይ ነው። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ግድ የለሾች ወይም ቸልተኞች ቢሆኑ እንኳ ምሥራቹን ማወጃችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው? ይህን የምናደርገው የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈላችን፣ ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር መገለጫ እንደሆነ ስለምንገነዘብ ነው። በእርግጥም የራሳችንም ሆነ የሌሎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው። (ሕዝ. 3:17-21፤ 1 ጢሞ. 4:16) ብዙ የእምነት አጋሮቻችን በአስቸጋሪ ክልሎች ውስጥ ሲሰብኩ ለአገልግሎት ያላቸውን ቅንዓት ይዘው እንዲቀጥሉ ወይም ቅንዓታቸው ይበልጥ እንዲቀጣጠል የረዷቸውን አንዳንድ ነጥቦች እስቲ እንመልከት።

በምታገኟቸው አጋጣሚዎች በሙሉ ተጠቀሙ

በአገልግሎታችን ላይ ተገቢ ጥያቄዎችን መጠቀማችን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። አንድ ቀን ጠዋት አማሊያ መናፈሻ ውስጥ አንድ ሰው ጋዜጣ ሲያነብ ተመለከተች። ከዚያም አማሊያ ወደ እሱ ቀርባ በጋዜጣው ላይ ጥሩ ዜና አንብቦ እንደሆነ ጠየቀችው። ሰውየው ምንም ጥሩ ዜና እንዳላነበበ ሲነግራት “እኔ ግን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ አንድ አስደሳች ዜና ይዤልህ መጥቻለሁ” አለችው። አማሊያ የተናገረችው ነገር የሰውየው ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ስላደረገ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። እንዲያውም አማሊያ በዚያ መናፈሻ ውስጥ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ችላለች።

ጃኒስ የሥራ ቦታዋን የአገልግሎት ክልሏ አድርጋዋለች። አንድ የጥበቃ ሠራተኛና አብራው የምትሠራ ሴት በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ትኩረታቸውን እንደሳበው ስትመለከት መጽሔቶቹን በቋሚነት ልታመጣላቸው እንደምትችል ነገረቻቸው። በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ በሚወጡት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለተማረከ አንድ ሌላ የሥራ ባልደረባዋም እንዲሁ አድርጋለች። ይህ ደግሞ ሌላ የሥራ ባልደረባዋ መጽሔቶቹን ለማግኘት እንድትጠይቅ አነሳስቷታል። ጃኒስ “ይህ ከይሖዋ ያገኘሁት ትልቅ በረከት ነው!” በማለት ተናግራለች። ከጊዜ በኋላ ጃኒስ፣ በሥራ ቦታዋ 11 የመጽሔት ደንበኞችን ማፍራት ችላለች።

አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ

አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች፣ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበት ወቅት ከቤቱ ባለቤት ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ሲጨርሱ ‘ሌላ ቀን እመጣለሁ’ ብለው ብቻ መሄድ እንደሌለባቸው ሐሳብ አቀረበላቸው። ከዚህ ይልቅ ግለሰቡን “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ላሳይዎት?” ወይም “ውይይታችንን ለመቀጠል መቼ ልምጣ? በስንት ሰዓት?” ብለው እንዲጠይቁት አበረታታቸው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ፣ እሱ በሚጎበኘው አንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይህን አቀራረብ በመጠቀም በአንድ ሳምንት ውስጥ 44 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር እንደቻሉ ሪፖርት አድርጓል።

ብዙ ሳይቆዩ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ይኸውም ግለሰቡን ባገኘነው በማግሥቱ ወይም ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመልሶ መሄድ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያውቁ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን ያሳያል። አንዲት ሴት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማችው  ለምን እንደሆነ ስትጠየቅ “ማጥናት የጀመርኩት ልባዊ አሳቢነትና ፍቅር ስላሳዩኝ ነው” ብላለች።

የቤቱን ባለቤት “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ላሳይዎት?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ

ማዳኢ በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ከተካፈለች ከጥቂት ጊዜ በኋላ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት የጀመረች ሲሆን ሌሎች 5 ጥናቶችን ደግሞ ለሌሎች አስፋፊዎች ሰጥታለች። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። ማዳኢ ይህን ያህል ብዙ ጥናቶችን እንድታስጀምር የረዳት ምንድን ነው? በመጀመሪያው ውይይት ላይ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በድጋሚ እስክታገኛቸው ድረስ ተመልሳ መሄዷ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትምህርት ቤቱ ስላስገነዘባት ነው። ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ የረዳች አንዲት ሌላ እህት ደግሞ “ይሖዋን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት ቁልፉ ሳይታክቱ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች።

ብዙ ሳንቆይ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጋችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ የሚሹ ግለሰቦችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን ያሳያል

ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ሳያሰልሱ ጥረት ማድረግን ይጠይቃሉ። ይሁን እንጂ ይህ ማድረግ ምንም ያህል ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። ራሳችንን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ካስጠመድን ሌሎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” መርዳት እንችላለን፤ ይህም ለሰዎች መዳን ያስገኝላቸዋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ለእኛ ደግሞ ወደር የሌለው እርካታና ደስታ ያስገኝልናል።