በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እነሆ! አስደናቂ የሆነው ብርሃን!

እነሆ! አስደናቂ የሆነው ብርሃን!

እነሆ! አስደናቂ የሆነው ብርሃን!

በጨለማ ውስጥ በዳበሳ ሄደህ የምታውቅ ከሆነ ሁኔታው ምን ያህል አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትህም። ብርሃን ሲበራልህ ታላቅ እፎይታ ይሰማሃል! በተጨማሪም ጨለማ ውስጥ እንዳለህ ሆኖ የተሰማህ ጊዜ ይኖር ይሆናል። እንዲህ የተሰማህ ከገጠመህ ችግር ለመውጣት የሚያስችል መውጫ ቀዳዳ በጠፋብህ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ጭላንጭል ቀስ በቀስ ታየህ እንበል። እንደዚያ ከመሰለ ጨለማ ውስጥ ወጥቶ ብርሃን ማየት እጅግ አስደሳች ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ነበሩ። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የቀድሞ እምነታቸውን ትተው ክርስትናን ለተቀበሉት ሰዎች ሲጽፍ ‘[አምላክ] ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ ጠርቷችኋል’ ብሏቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይህ ለእነርሱ፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ደማቅ ብርሃን የመውጣት ያህል ነበር። በተጨማሪም ተስፋው የጨለመበት ብቸኛ ሰው ከመሆን ተላቅቆ አስተማማኝ ተስፋ የተዘረጋለት ቤተሰብ አባል ከመሆን ጋር ሊመሳሰል ይችላል።—ኤፌሶን 2:1, 12

“የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል”

የጥንት ክርስቲያኖች ‘እውነትን’ ማለትም እውነተኛውን የክርስትና እምነት አግኝተው ነበር። (ዮሐንስ 18:37) የእውነትን ድንቅ ብርሃን በማየታቸው ከመንፈሳዊ ጨለማ ተላቅቀው ወደ ደማቅ ብርሃን ወጥተዋል። ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ቅንዓት እየቀዘቀዘ ሄደ። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማገባደጃ አካባቢ በኤፌሶን ጉባኤ ውስጥ ከባድ ችግር ተከስቶ ነበር። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ችግሩ ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል። እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ አስብ፤ ንስሓ ገብተህ ቀድሞ ታደርገው የነበረውን ነገር አድርግ።” (ራእይ 2:4, 5) የኤፌሶን ክርስቲያኖች ለአምላክና ለእውነት ያላቸውን ፍቅር እንደገና ማቀጣጠል ነበረባቸው።

እኛስ? እኛም ብንሆን አስደናቂውን የአምላክን ቃል እውነት በማወቃችን ብርሃን ማየት ችለናል። ይህም እውነትን እንድንወድ አድርጎናል። ይሁን እንጂ በማንኛውም ሰው ላይ የሚደርሱ ችግሮች ለእውነት ያለንን ፍቅር ሊያቀዘቅዙብን ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ተለይቶ የሚታወቅባቸው ችግሮች ይደርሱብናል። የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ሲሆን በዓለማችን የሚገኙ ሰዎችም “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው” በመሆናቸው ይታወቃሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) እነዚህ ሰዎች የሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ቅንዓታችንንም ሆነ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ሊያቀዘቅዝብን ይችላል።

የመጀመሪያው ፍቅራችን ቀዝቅዞ ከሆነ ‘ከየት እንደ ወደቅን ማሰብና ንስሓ መግባት’ ይኖርብናል። ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ ሁኔታችን መመለስ አለብን። ከዚህም በላይ ለእውነት ያለን አድናቆት እንዲቀንስ መፍቀድ አይገባንም። ሁላችንም አዎንታዊ አመለካከትና ደስተኛ መንፈስ መያዛችን እንዲሁም ለአምላክም ሆነ ለእውነት ያለን ፍቅር እንዳይጠፋ መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

‘ነጻ ያወጣን እውነት’

ቅዱሳን መጻሕፍት የሚፈነጥቁት የእውነት ብርሃን እጅግ አስደናቂ ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሰዎችን ግራ ሲያጋቡ ለኖሩ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ‘የተፈጠርነው ለምንድን ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ክፋት ለምን ኖረ? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?’ የሚሉት ይገኙበታል። ይሖዋ አስደናቂ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውነቶች አሳውቆናል። ታዲያ ከልብ ልናመሰግን አይገባንም? የተማርነውን ነገር የማናደንቅ ምስጋና ቢሶች መሆን የለብንም!

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 8:32) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከኃጢአትና ከሞት ነጻ ያወጣል። በተጨማሪም ውድ የሆኑት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች፣ ባለማወቅና በጥርጣሬ ከተሞላው በጨለማ የተዋጠ ዓለም ነጻ አውጥተውናል። በተማርነው ነገር ላይ በአድናቆት ማሰላሰላችን ለይሖዋና ለቃሉ ያለን ፍቅር እንዲጠነክር ይረዳናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- ‘ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእናንተ በምታምኑት ዘንድ በእርግጥ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ አልተቀበላችሁትም።’ (1 ተሰሎንቄ 2:13) የተሰሎንቄ ሰዎች የአምላክን ቃል ሰምተው ‘በደስታ ተቀብለውታል።’ ከዚያ በኋላ “በጨለማ ውስጥ” ከመኖር ተላቅቀው “የብርሃን ልጆች” ለመሆን በቅተዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:4-7፤ 5:4, 5) እነዚህ ክርስቲያኖች ይሖዋ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ፣ ጥበበኛ፣ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ ተምረዋል። እንደ ሌሎቹ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እነርሱም ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአታቸው የሚደመሰስበት ዝግጅት እንዳደረገ ተገንዝበዋል።—የሐዋርያት ሥራ 3:19-21

የተሰሎንቄ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተሟላ እውቀት ነበራቸው ባይባልም እንዲህ ያለውን እውቀት ከየት ማግኘት እንደሚችሉ ተረድተዋል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ለአምላክ ያደረ ሰው “ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ” ይረዱታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በተሰሎንቄ የሚኖሩት ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ማጥናታቸውን በቀጠሉ መጠን ከአምላክ የሚገኘው ብርሃን እጅግ አስደናቂ እንደሆነ መገንዘብ ይችሉ ነበር። ስለዚህ ሁልጊዜ የሚደሰቱበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:16) የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው።

ለመንገዳችን ብርሃን

መዝሙራዊው የእውነት ብርሃን አስደናቂ የሆነው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:105) ከአምላክ ቃል የምናገኘው መለኮታዊ መመሪያ አቅጣጫችንን እንዳንስትና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል። አቅጣጫውን እንደሳተ መርከብ መሆን የለብንም። እውነትን ማወቅና በሥራ ላይ ማዋል “በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ . . . ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን” ከመሄድ ይጠብቀናል።—ኤፌሶን 4:14

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው።” (መዝሙር 146:3, 5) ከዚህም በላይ በይሖዋ መታመናችን ፍርሃትንና ጭንቀትን ለማሸነፍ ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በአምላክ ቃል ብርሃን መመራታችን በእርግጥም ይጠቅመናል።

በዓለም ሁሉ እንደ ከዋክብት የምታበሩ ሁኑ

የአምላክ ቃል የሚፈነጥቀው ብርሃን አስደናቂ የሆነበት ሌላው ምክንያት የሰው ልጆች እጅግ ክቡር በሆነ አንድ ሥራ ላይ እንዲካፈሉ መንገድ መክፈቱ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አዟቸዋል:- “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 28:18-20

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥራቹን ሲሰብኩም ይሁን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲያስተምሩ እገዛ እያደረገላቸው ያለው ማን እንደሆነ ልብ በል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። በእርግጥም ኢየሱስ በአገልግሎታቸውም ሆነ በሌሎች ‘መልካም ሥራዎቻቸው’ አማካኝነት ‘ብርሃናቸውን ሲያበሩ’ እርዳታና ድጋፍ አድርጎላቸዋል። (ማቴዎስ 5:14-16) መላእክትም በዚህ በወንጌላዊነት ሥራ ይሳተፋሉ። (ራእይ 14:6) ስለ ይሖዋ አምላክስ ምን ለማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው” ሲል ጽፏል። “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮንቶስ 3:6, 9

በተጨማሪም አምላክ የሰጠንን ሥራ ለማከናወን ያደረግነው ጥረት ምን ያህል እንደተባረከ አስብ። አምላክ ከሰጠን ‘በዓለም ሁሉ እንደ ከዋክብት የማብራት’ መብት ጋር የሚተካከል ምንም ነገር የለም። ከአምላክ ቃል ያገኘነውን ብርሃን በአነጋገራችንም ሆነ በተግባራችን በማንጸባረቅ ልበ ቅን ሰዎችን መርዳት እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 2:15) በተጨማሪም ‘አምላክ ሥራችንን እንዲሁም ስለ ስሙ ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ ስላልሆነ’ በቅንዓት መስበካችንና ማስተማራችን ደስታ ያስገኝልናል።—ዕብራውያን 6:10

‘ዐይንህን የምትኳለውን ኵል ግዛ’

ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሎዶቅያ ይገኝ ለነበረው ጉባኤ በላከው መልእክት ላይ እንዲህ ብሏል:- “ለማየትም እንድትችል ዐይንህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ እንድትገዛ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም።” (ራእይ 3:18, 19) ‘በኵል’ የተመሰለው የኢየሱስ ትምህርትና ተግሣጽ ለመንፈሳዊ መታወር ፍቱን መድኃኒት ነው። በመንፈሳዊ ጤናማ አመለካከት ይዘን ለመቀጠል ከፈለግን የክርስቶስን ምክር መቀበልና በተግባር ላይ ማዋል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም መመሪያዎች መታዘዝ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስን አስተሳሰብ መያዝና ምሳሌውን መኮረጅ ይገባናል። (ፊልጵስዩስ 2:5፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) ኩሉ እንዲሁ በነጻ የሚገኝ አይደለም። ኢየሱስ ‘ከእኔ ግዙ’ ብሏል። ኩሉን መግዛት ጊዜና ጥረት ይጠይቅብናል።

ከጨለማ ወጥተን ብርሃን ወዳለበት ክፍል ስንገባ ዓይናችን ብርሃኑን እስኪለምደው ድረስ ጥቂት ጊዜ ይወስድብናል። በተመሳሳይም የአምላክን ቃል ለማጥናትም ሆነ የእውነትን ብርሃን ለማየት ጊዜ ይጠይቃል። በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰልም ሆነ እውነት ምን ያህል ውድ መሆኑን በጥልቀት ማሰብ ጊዜ ይጠይቃል። ይሁንና የምናወጣው ወጪ ከባድ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ይህ ብርሃን እጅግ አስደናቂ ነው!

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ለማየትም እንድትችል ዐይንህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ግዛ’