በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ

ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ

የሕይወት ታሪክ

ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ

ሌኦፖልት ኤንግላይትነር እንደተናገረው

የኤስ ኤስ መኮንኑ ሽጉጡን መዝዞ ራሴ ላይ ደገነና “ለመሞት ዝግጁ ነህ?” ሲል ጠየቀኝ። ከዚያም “አንተ ልትለወጥ የማትችል ሰው ስለሆንክ ልገድልህ ነው” አለኝ። ድምፄ እንዳይንቀጠቀጥ እየተጠነቀቅሁ “ዝግጁ ነኝ” በማለት መለስኩለት። ከዚያም ዓይኔን በመጨፈን ራሴን አረጋግቼ ቃታውን እስኪስበው መጠባበቅ ጀመርኩ፤ ሆኖም መኮንኑ አልተኮሰም። “ለመሞትም የማትረባ ነህ!” ብሎ ከጮኸብኝ በኋላ ሽጉጡን ከራሴ ላይ አነሳው። እንደዚህ ባለ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልገኝ የቻልኩት እንዴት ነው?

ሐምሌ 23, 1905 በኦስትሪያ ተራሮች ላይ በምትገኘው አይገን ፎግልሁብ በምትባል ከተማ ተወለድኩ። ለወላጆቼ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። አባቴ የሚሠራው በእንጨት መሰንጠቂያ ውስጥ ሲሆን እናቴ ደግሞ የአንድ ገበሬ ልጅ ነበረች። ወላጆቼ ድሆች ቢሆኑም ጠንካራ ሠራተኞች ነበሩ። የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በሳልዝበርግ አቅራቢያ በሚገኘው በባት ኢሽል ከተማ ሲሆን በአካባቢው ውብ የሆኑ ሐይቆችና ደስ የሚሉ ተራሮች ነበሩ።

ከወላጆቼ ድህነት በተጨማሪ ስወለድ ጀምሮ የነበረብኝ የጀርባ አጥንት ሕመም ያሠቃየኝ ስለነበር ልጅ እያለሁ በሕይወት ውስጥ የሚታየው የፍትሕ መጓደል ያሳስበኝ ነበር። በዚህ ሕመም ሳቢያ ቀጥ ብዬ መቆም ያስቸግረኛል። በትምህርት ቤት በሚደረገው የሰውነት እንቅስቃሴ ላይ እንድካፈል አይፈቀድልኝም ነበር፤ በዚህም ምክንያት በክፍል አብረውኝ የሚማሩት ልጆች መሳለቂያ ሆንኩ።

አንደኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ አካባቢ 14 ዓመት ሊሆነኝ ትንሽ ሲቀረኝ ከድህነት ለመሸሽ ስል ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። በረሃብ አለንጋ መገረፍ የሁልጊዜ ገጠመኝ ነበር፤ በዚህ ላይ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው የኅዳር በሽታ ያስከተለብኝ ኃይለኛ ትኩሳት ይባሱኑ ሰውነቴን ደቆሰው። አብዛኞቹ ገበሬዎች ለሥራ እንዲቀጥሩኝ ስጠይቃቸው “እንደ አንተ ላለ አቅመ ደካማ የሚሆን ሥራ የለንም” የሚል መልስ ይሰጡኝ የነበረ ቢሆንም አንድ ደግ ገበሬ ግን ቀጠረኝ።

ስለ አምላክ ፍቅር መማር

እናቴ አጥባቂ ካቶሊክ ብትሆንም አባቴ ለሃይማኖት ግድየለሽ ስለነበር እምብዛም ቤተ ክርስቲያን አልሄድም ነበር። ያም ቢሆን ግን በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው የምስል አምልኮ ይረብሸኝ ነበር።

በጥቅምት ወር 1931 አንድ ወዳጄ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ወደተዘጋጀ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ከእርሱ ጋር እንድሄድ ጠየቀኝ። የምስል አምልኮ አምላክን ያስደስተዋል? (ዘፀአት 20:4, 5) እሳታማ ሲኦል አለ? (መክብብ 9:5) ሙታንስ ይነሳሉ? (ዮሐንስ 5:28, 29) የሚሉትን ጨምሮ ለዋና ዋና ጥያቄዎቼ በዚሁ ስብሰባ ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አገኘሁ።

ከሁሉ ያስደነቀኝ ነገር ምንም እንኳን በአምላክ ስም ጦርነቶች ቢካሄዱም እርሱ እነዚህን ጭካኔ የሚንጸባረቅባቸው ውጊያዎች እንደማይደግፍ ማወቄ ነበር። ‘አምላክ ፍቅር እንደሆነ’ እንዲሁም ይሖዋ የተባለ ከሁሉ የላቀ ስም እንዳለው አወቅሁ። (1 ዮሐንስ 4:8፤ መዝሙር 83:18 NW) በይሖዋ መንግሥት ሥር መላዋ ምድር ገነት ሆና የሰው ልጆች ለዘላለም በደስታ እንደሚኖሩባት ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ። እንዲሁም አምላክ በሰማይ ባቋቋመው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ድንቅ መብት የተዘረጋላቸው ፍጹም ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉም ተማርኩ። ለዚህ መንግሥት ምንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነበርኩ። ስለዚህ በግንቦት ወር 1932 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በዚያን ጊዜ ኦስትሪያ አጥባቂ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ስለነበረች ይህ እርምጃ ድፍረት ጠይቆብኛል።

ጥላቻና ተቃውሞ አጋጠመኝ

ወላጆቼ ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቄ ስወጣ በጣም ተበሳጩ፤ ቄሱም ከመስበኪያ ሰገነቱ ላይ ሆኖ ወሬውን በፍጥነት አዳረሰው። የአካባቢው ነዋሪዎች ጥላቻቸውን ለመግለጽ ፊት ለፊቴ ምራቃቸውን ይተፉ ነበር። እንደዛም ሆኖ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ፤ ከዚያም በጥር 1934 በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ።

የናዚ ፓርቲ እኛ በምንኖርበት ግዛት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ በመምጣቱ የፖለቲካው ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት አስቸጋሪ ሆነ። በስቲሪያ በሚገኘው በኤንስ ሸለቆ በአቅኚነት በማገለግልበት ወቅት ፖሊሶች ሁልጊዜ ያሳድዱኝ ስለነበረ ‘እንደ እባብ ብልህ’ መሆን ነበረብኝ። (ማቴዎስ 10:16) ከ1934 እስከ 1938 ባለው ጊዜ ውስጥ ስደት የዕለት ተዕለት ሕይወቴ ክፍል ሆኖ ነበር። ሥራ እንደሌለኝ እየታወቀ የሥራ አጥ ድጎማዬን ተነፈግሁ፤ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ምክንያት በተደጋጋሚ አጠር ላለ ጊዜ፣ በአራት አጋጣሚዎች ደግሞ ረጅም እስራት ተፈርዶብኛል።

የሂትለር ወታደሮች ኦስትሪያን ተቆጣጠሯት

መጋቢት 1938 የሂትለር ወታደሮች ኦስትሪያ ገቡ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ90,000 የሚበልጡ ሰዎች (አዋቂ ከሆነው የኅብረተሰቡ ክፍል 2 በመቶ የሚሆኑት) የናዚን አገዛዝ ተቃውማችኋል በሚል ተወንጅለው ወደ ወኅኒ ቤቶችና ማጎሪያ ካምፖች ተጋዙ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህ እንደሚመጣ ስለተረዱ ተዘጋጅተው ነበር። በ1937 የበጋ ወቅት፣ እኔ የነበርኩበት ጉባኤ አባላት የሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ለመካፈል ሲሉ በብስክሌት 350 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ፕራግ ሄዱ። በዚያም በጀርመን በሚገኙ ወንድሞቻችን ላይ ስለተፈጸመባቸው ግፍ ሰምተው ነበር። አሁን ተራው የእኛ እንደሆነ ግልጽ ነበር።

የሂትለር ወታደሮች ኦስትሪያ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉት ስብሰባና የስብከቱ ሥራ በድብቅ መከናወን ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በስዊስ ጠረፍ በኩል ይገቡ የነበረ ቢሆንም ጽሑፎቹ ለሁሉም ወንድሞች አይዳረሱም ነበር። ስለዚህ በቪየና ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችን በድብቅ ጽሑፎች ያትሙ ነበር። እኔም ብዙውን ጊዜ ጽሑፎችን ለወንድሞች አደርስ ነበር።

ወደ ማጎሪያ ካምፕ ተላክሁ

ሚያዝያ 4, 1939 እኔና ሦስት የእምነት ባልደረቦቼ በባት ኢሽል የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እያከበርን ሳለ ጌስታፖዎች መጥተው ያዙን። ሁላችንንም በሊንዝ ወደሚገኘው የፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በመኪና ወሰዱን። በመኪና ስሄድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ቢሆንም በጉዞው ከመደሰት ይልቅ ጨንቆኝ ነበር። ሊንዝ ከደረስኩ በኋላ በተከታታይ የሚያሠቃይ ምርመራ ቢደረግብኝም እምነቴን አልካድኩም። ከአምስት ወራት በኋላ በላይኛው ኦስትሪያ ግዛት ዳኛ ፊት ቀረብኩ። በዚያም የወንጀል ምርመራው ሂደት ሳይታሰብ ተቋረጠ፤ ሆኖም ይህ የመከራዬ መጨረሻ አልነበረም። በዚህ መሃል፣ ሦስቱን የእምነት ባልደረቦቼን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ያጋዟቸው ሲሆን እስከ መጨረሻው በታማኝነት ጸንተው እዚያው ሞቱ።

እኔ ለጊዜው በማረፊያ ቤት እንድቆይ ተደረገ፤ ከዚያም ጥቅምት 5, 1939 ጀርመን ወደሚገኘው ቡከንዋልድ ማጎሪያ ካምፕ እንደምወሰድ ተነገረኝ። አንድ ልዩ ባቡር በሊንዝ ባቡር ጣቢያ እስረኞችን ለመውሰድ ይጠባበቅ ነበር። ባቡሩ ሁለት ሰዎችን ብቻ የሚይዙ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእኔ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ የተመደቡት የቀድሞው የላይኛው ኦስትሪያ አገረ ገዢ ዶክተር ሃይንሪች ግላይስነር ነበሩ።

ከዶክተር ግላይስነር ጋር ጥሩ ውይይት ጀመርን። በሁኔታዬ ከልብ አዘኑ፤ እንዲሁም አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜም ቢሆን በግዛታቸው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ሕጋዊ ችግሮች እንደደረሱባቸው ሲያውቁ በጣም ደነገጡ። በሁኔታው መጸጸታቸውን በሚገልጽ መንገድ እንዲህ አሉኝ:- “ሚስተር ኤንግላይትነር፣ ያለፈውን ማስተካከል ባልችልም ይቅርታ መጠየቅ ግን እፈልጋለሁ። መንግሥታችን ፍትሓዊ አገዛዝ እንዲኖር ባለማድረጉ ጥፋተኛ ነው። ከአሁን በኋላ እርዳታ ካስፈለገህ እኔ ልረዳህ የምችለውን ማንኛውም ነገር ላደርግልህ ፈቃደኛ ነኝ።” ከጦርነቱ በኋላ እንደገና የተገናኘን ሲሆን በናዚ አገዛዝ ጭቆና ለደረሰባቸው ሰዎች መንግሥት የሚሰጠውን የጡረታ አበል እንዳገኝ ረድተውኛል።

ልገድልህ ነው

ጥቅምት 9, 1939 ቡከንዋልድ ማጎሪያ ካምፕ ደረስኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የእስር ቤቱ ጠባቂ ከሚመጡት እስረኞች መካከል የይሖዋ ምሥክር እንዳለ ተነግሮት ስለነበር ትኩረቱን በሙሉ በእኔ ላይ በማድረግ በጭካኔ ደበደበኝ። ከዚያም እምነቴን ሊያስክደኝ እንደማይችል ሲገነዘብ እንዲህ አለኝ:- “ኤንግላይትነር ልገድልህ ነው። ከዚያ በፊት ግን ለወላጆችህ የመሰናበቻ ቃላትህን በካርድ ላይ እንድታሰፍር ፈቅጄልሃለሁ።” ለወላጆቼ አጽናኝ የሆኑ ቃላትን ለመጻፍ አስቤ እስክሪብቶውን ባነሳሁ ቁጥር ቀኝ እጄን ይመታኝ ስለነበረ ወረቀት ላይ የማሰፍረው እንዲሁ የተሞነጫጨረ ነገር ነበር። በፌዝ እየሣቀ “ምን የማይረባ ሰው ነው! ሁለት መስመር እንኳን አስተካክሎ መጻፍ አይችልም። እንደዚህም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡን አይተውም” ይለኝ ነበር።

ከዚያም በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት ጠባቂው ሽጉጡን አውጥቶ አናቴ ላይ በመደገን እንደሚተኩስብኝ ነገረኝ። ከዚያም አንዲት በሰው የታጨቀች ትንሽ ክፍል ውስጥ ገፍቶ አስገባኝ። ሌሊቱን ሙሉ ቆሜ ማደር ነበረብኝ። ለነገሩ ለመተኛት የተመቻቸ አጋጣሚ ባገኝ እንኳን መላ ሰውነቴን በጣም አምሞኝ ስለነበር መተኛት አልችልም ነበር። አብረውኝ ካሉት ሰዎች የምሰማው “ማጽናኛ” ቢኖር “ለአንድ የማይረባ ሃይማኖት ብሎ መሞት ሕይወትን ማባከን ነው!” የሚል ነበር። ዶክተር ግላይስነር ከእኔ አጠገብ ባለው ክፍል ውስጥ ነበሩ። የተከሰተውን ነገር ሲሰሙ በአዘኔታ “በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት አስከፊ ገጽታ እንደገና እየታየ ነው!” በማለት ተናገሩ።

ምንም እንኳን በአብዛኛው እሁድ ዕለት የማንሠራ ቢሆንም በ1940 የበጋ ወቅት ሁሉም እስረኞች እሁድ ዕለት የድንጋይ መፍለጫው ቦታ እንድንገኝ ትእዛዝ ወጣ። ይህም አንዳንድ እስረኞች “ለሠሩት አነስተኛ ወንጀል” አጸፋ ለመመለስ ተብሎ የተደረገ ነበር። በጣም ትላልቅ ድንጋዮችን ከድንጋይ መፍለጫው ቦታ ወደ ካምፑ እንድንወስድ ታዘዝን። ሁለት እስረኞች አንድ ትልቅ ድንጋይ ጀርባዬ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ከክብደቱ የተነሳ ራሴን ስቼ ልወድቅ ትንሽ ቀርቶኝ ነበር። ሆኖም አርተር ሩድል የተባለው የሚፈራ ላገፉኸር (የካምፑ ዋና ኃላፊ) ሳይታሰብ መጥቶ አዳነኝ። ድንጋዩን ለመሸከም የማደርገውን ሥቃይ የተሞላበት ጥረት ሲመለከት “ይሄንን ድንጋይ ጀርባህ ላይ ተሸክመህ ካምፑ ድረስ መውሰድ አትችልም! አሁኑኑ አውርደው!” አለኝ። የተባልኩትን በማድረግ እፎይታ አገኘሁ። ቀጥሎም ሩድል ከዚያ በጣም የሚያንስ ድንጋይ እያመለከተ “ያኛው ለመሸከም ቀላል ነው፤ አንስተህ ወደ ካምፑ ውሰደው” አለኝ። ከዚያም ወደ ተቆጣጣሪያችን ዞሮ “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ሠፈራቸው ይመለሱ። ለአንድ ቀን የሚሆን በቂ ሥራ ሠርተዋል!” የሚል ትእዛዝ ሰጠው።

በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ ከመንፈሳዊ ቤተሰቦቼ ጋር መገናኘት ስለምችል ሁልጊዜ እደሰት ነበር። መንፈሳዊ ምግቦችን ለማሰራጨት ዝግጅት አደረግን። አንድ ወንድም በቁራጭ ወረቀት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይጽፍና ለሌሎቹ ያስተላልፍ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስም በድብቅ ወደ ካምፑ ገብቶ ስለነበር ገንጥለን በየመጽሐፎቹ ከፋፈልነው። የኢዮብ መጽሐፍ ለሦስት ወር ያህል እኔ ጋር የነበረ ሲሆን ካልሲዬ ውስጥ እደብቀው ነበር። የኢዮብ መጽሐፍ ጸንቼ እንድቆም ረድቶኛል።

በመጨረሻም መጋቢት 7, 1941 ወደ ኒደሃገን ማጎሪያ ካምፕ ከተዛወሩ በርካታ ሰዎች ጋር ተቀላቅዬ ተወሰድኩ። ከቀን ወደ ቀን ሁኔታዬ እያሽቆለቆለ ሄደ። በአንድ ወቅት እኔና ሁለት ወንድሞች የሥራ ቁሳቁሶችን በሣጥኖች ውስጥ እንድናሽግ ታዘዝን። ከዚያም ከሌሎች እስረኞች ጋር አብረን ወደ ሠፈር እንድንሄድ ተደረገ። አንድ የኤስ ኤስ ወታደር ወደኋላ እንደቀረሁ ሲመለከት በጣም ከመናደዱ የተነሳ ሳላስበው በጭካኔ ጀርባዬን በእርግጫ መታኝ፤ ይህም ከባድ ጉዳት አደረሰብኝ። ሕመሙ በጣም የሚያሠቃይ ነበር፤ እንደዛም እየታመምኩ በነጋታው ሥራ ሄድኩ።

ሳይታሰብ ተፈታሁ

በሚያዝያ ወር 1943 ከኒደሃገን ካምፕ ለቀን እንድንወጣ ተደረግን። ከዚያ በመቀጠል በራቨንስብሩክ ወደሚገኘው የሞት ካምፕ ተዛወርኩ። ከዚያም በሰኔ 1943 ሳይታሰብ ከማጎሪያ ካምፑ የመለቀቅ አጋጣሚ ቀረበልኝ። በዚህ ጊዜ ግን ከካምፑ እንድወጣ ሲፈቀድልኝ እምነቴን እንድክድ አልተጠየቅሁም። ቀሪ ሕይወቴን በእርሻ ቦታ የጉልበት ሥራ ለመሥራት መስማማት ብቻ ነበር የሚጠበቅብኝ። ከአሰቃቂው የካምፕ ሕይወት ለማምለጥ ስል ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበርኩ። ለመጨረሻ የጤንነት ምርመራ ወደ ካምፑ ዶክተር ሄድኩ። ዶክተሩ እኔን በማየቱ ተደነቀ። “ይገርማል፣ እስካሁን የይሖዋ ምሥክር ነህ!” አለኝ። “ልክ ነህ ዶክተር” በማለት መለስኩለት። “ነገሩ እንደዛ ከሆነ ለምን እንደምንለቅህ አይገባኝም። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አንተ ካለ የማይረባ ፍጡር መገላገል ለእኛ ትልቅ እፎይታ ነው” አለኝ።

ይህን ሲል ማጋነኑ አልነበረም። በእውነትም ጤንነቴ አስጊ ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር። ከፊሉ ቆዳዬ በቅማል ተበልቷል፣ ከብዙ ድብደባ የተነሳ አንዱ ጆሮዬ መስማት አይችልም፤ እንዲሁም መላ ሰውነቴ ቆስሎ መግል ይዞ ነበር። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከማጣት፣ መቋጫ ከሌለው ረሃብ እና ከከባድ ሥራ የተነሳ ከ46 ወራት በኋላ 28 ኪሎ ግራም ብቻ እመዝን ነበር። በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ሐምሌ 15, 1943 ከራቨንስብሩክ ካምፕ እንድወጣ ተፈቀደልኝ።

ወደ መኖሪያ ከተማዬ እንድሄድ ያለ ጠባቂ በባቡር ተላክሁ፤ ከዚያም በሊንዝ ወደሚገኘው የጌስታፖ ዋና መሥሪያ ቤት ሄጄ ሪፖርት አደረግሁ። የጌስታፖው መኮንን ከካምፑ እንደተለቀቅሁ የሚገልጹ ወረቀቶቼን ከሰጠኝ በኋላ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀኝ:- “ስንለቅህ የድብቅ ሥራህን ለመቀጠል አስበህ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል! ስትሰብክ ካገኘንህ ግን አምላክ ይርዳህ።”

በመጨረሻ ወደ ቤቴ ተመለስኩ! እናቴ ከመኝታ ክፍሌ ውስጥ ምንም ነገር አልነካችም፤ ሚያዝያ 4, 1939 ተይዤ ስሄድ እንደነበረው እንደዛው ቆየኝ። ሌላው ቀርቶ ከአልጋዬ አጠገብ ባለው ጠረጴዛ ላይ መጽሐፍ ቅዱሴ እንደተከፈተ ነበር። በጉልበቴ ተንበርክኬ ከልብ የመነጨ የምስጋና ጸሎት አቀረብኩ።

ወዲያው በተራራማው ቦታ በሚገኝ እርሻ ላይ እንድሠራ ተመደብኩ። የልጅነት ወዳጄ የነበረው የእርሻው ባለቤት የመክፈል ግዴታ ባይኖርበትም ትንሽ ደሞዝ ይከፍለኝ ነበር። ከጦርነቱ በፊት ይህ ወዳጄ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በግቢው ውስጥ እንድደብቅ ፈቅዶልኝ ነበር። በእነዚያ ጽሑፎች በሚገባ ተጠቅሜ በመንፈሳዊ መጠንከር በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። በዚህ ቦታ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ተሟላልኝ፤ ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ በእርሻው ቦታ ላይ ሆኜ ለመጠበቅ ቆርጬ ነበር።

በተራራማ አካባቢዎች መደበቅ

ሆኖም እነዚያ የተረጋጉ የነፃነት ቀኖች ለረጅም ጊዜ አልቆዩም። በነሐሴ 1943 አጋማሽ ላይ የጤንነት ምርመራ ለማድረግ የጦር ሠራዊት ዶክተር ጋር እንድሄድ ታዘዝኩ። በመጀመሪያ ጤነኛ ባልሆነው ጀርባዬ ምክንያት አሁን ላለው አገልግሎት ብቁ እንዳልሆንኩ ነገረኝ። ይሁን እንጂ ከሳምንት በኋላ ያው ዶክተር የምርመራ ውጤቱን አሻሽሎ “ጤነኛ በመሆኑ በጦር ግንባር ላይ ተሰልፎ ሊዋጋ ይችላል” ብሎ ጻፈ። ለተወሰነ ጊዜ የጦር ሠራዊቱ ሊያገኘኝ አልቻለም፤ ሆኖም በሚያዝያ 17, 1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ ከትንሽ ጊዜ በፊት ያዙኝና በውጊያው ግንባር እንድሰለፍ መለመሉኝ።

ጥቂት ልብሶች፣ ምግብና መጽሐፍ ቅዱስ በመያዝ በአቅራቢያችን በሚገኙት ተራሮች መደበቂያ ቦታ መፈላለግ ጀመርኩ። መጀመሪያ አካባቢ እደጅ መተኛት ችዬ ነበር፤ ሆኖም አየሩ እየከበደ ከመምጣቱም በላይ ግማሽ ሜትር ያህል ከፍታ ያለው በረዶ ጣለ። ከዚህም የተነሳ ሰውነቴ እንዳለ ራሰ። ከዚያም ከባህር ወለል በላይ 1,200 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኝ ተራራ ላይ ወዳለች አንዲት ጎጆ ለመድረስ ቻልኩ። በብርድ እንቀጠቀጥ ስለነበር ወዲያው እሳት አቀጣጥዬ ልብሴን አደራረቅሁና ራሴም መሞቅ ጀመርኩ። በጣም ደክሞኝ ስለነበር ከእሳቱ ፊት ለፊት ባለው አግዳሚ ወንበር ላይ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ኃይለኛ የሆነ ሕመም ተሰማኝና በድንገት ከእንቅልፌ ነቃሁ። የለበስኩት ልብስ በእሳት ተያይዞ ነበር። መሬቱ ላይ እየተንከባለልኩ እሳቱን አጠፋሁት። ጀርባዬ እንዳለ ውኃ ቋጠረ።

ልያዝ እንደምችል ባውቅም ገና ጎህ ሳይቀድ ቀደም ሲል ወደነበርኩበት በተራራው ላይ ወደሚገኘው የእርሻ ቦታ ሹልክ ብዬ ተመለስኩ። ሆኖም የገበሬው ሚስት በጣም ስለፈራች እኔን የሚፈልጉ ሰዎች መጥተው እንደነበር ገልጻ አባረረችኝ። ስለዚህ ወደ ወላጆቼ ሄድኩ። መጀመሪያ ላይ ወላጆቼም እንኳ እኔን ወደ ቤት ለማስገባት አቅማምተው ነበር። በኋላ ግን አስገቡኝና ሣር መከመሪያ ቆጥ ላይ እንድተኛ አደረጉኝ፤ እናቴም ቁስሌን ማከም ጀመረች። ከሁለት ቀናት በኋላ ግን ወላጆቼ በጣም ስለተሳቀቁ እንደገና ወደ ተራራማው አካባቢ ሄጄ ብደበቅ እንደሚሻለኝ ወሰንኩ።

ግንቦት 5, 1945 አንድ ኃይለኛ ድምፅ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። የኅብረ ብሔራቱ ኃይሎች አውሮፕላኖች ዝቅ ብለው ሲበርሩ አየሁ። በዛች ቅጽበት የሂትለር አገዛዝ እንደተገለበጠ አወቅኩ። የይሖዋ መንፈስ ለማመን የሚያዳግት መከራ ቢደርስብኝም እንድጸና አበርትቶኛል። የመዝሙር 55:22 ቃላት እውነት መሆናቸውን ከራሴ ተሞክሮ ለማየት ችያለሁ፤ ይህ ጥቅስ በመከራዬ መጀመሪያ ላይ እጅግ አጽናንቶኛል። ‘የከበደኝን ነገር በይሖዋ ላይ ጥያለሁ፤’ በአካል ደካማ ብሆንም “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ” በሄድኩበት ጊዜ ያለማቋረጥ ደግፎኛል።—መዝሙር 23:4

የይሖዋ ኃይል ‘ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነው

ከጦርነቱ በኋላ ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ መመለስ ጀመረ። በመጀመሪያ በተራራማው አካባቢ በሚገኘው ጓደኛዬ እርሻ ላይ እንደ ቀን ሠራተኛ ተቀጥሬ እሠራ ነበር። ሆኖም ዕድሜ ልኬን በግብርና መስክ የጉልበት ሥራ እንድሠራ ከተጣለብኝ ግዳጅ ነፃ የወጣሁት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሚያዝያ 1946 ጣልቃ ከገባ በኋላ ነበር።

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በባት ኢሽል እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙት ክርስቲያን ወንድሞች አዘውትረው መሰብሰብ ቻሉ። እንዲሁም በከፍተኛ ቅንዓት ምሥራቹን መስበክ ጀመሩ። እኔም በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የሌሊት ጥበቃ ሥራ ስላገኘሁ አቅኚነቴን ለመቀጠል ቻልኩ። በመጨረሻም በዛንክት ቮልፍጋንግ ከተማ መኖር ጀመርኩ። በ1949 ከቀድሞ ትዳሯ አንድ ልጅ ያላትን ቴሬዝያ ኩርተስን አገባሁ። በትዳር 32 ዓመታት አሳልፈናል። ውዷ ባለቤቴ ከሰባት ዓመታት በላይ ካስታመምኳት በኋላ በ1981 አረፈች።

ቴሬዝያ ከሞተች በኋላ የአቅኚነት አገልግሎቴን ቀጠልኩ፤ ይህም እሷን በማጣቴ የተሰማኝን ከፍተኛ ሐዘን ለመቋቋም አስችሎኛል። በአሁኑ ጊዜ በባት ኢሽል የጉባኤ ሽማግሌና አቅኚ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። አሁን ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ ስለማልችል በባት ኢሽል መናፈሻና ከቤቴ ፊት ለፊት ሆኜ ለሰዎች ስለ መንግሥቱ ተስፋ እናገራለሁ እንዲሁም ጽሑፎችን አበረክታለሁ። ከሰዎች ጋር ያደረግኳቸው ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶች ትልቅ የደስታ ምንጭ ሆነውልኛል።

ወደኋላ መለስ ብዬ ስላለፈው ሕይወቴ ሳስብ የደረሱብኝ አሰቃቂ መከራዎች እንድመረር እንዳላደረጉኝ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ በሚደርሱብኝ ፈተናዎች ሳቢያ እጨነቅ ነበር። ሆኖም ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትኩት የጠበቀ ዝምድና አስቸጋሪ ጊዜያትን ለመቋቋም አስችሎኛል። ጌታ ለጳውሎስ “ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” በማለት የሰጠው ምክር በሕይወት ዘመኔ እውነት ሲሆን ለማየት ችያለሁ። አሁን 100 ዓመት ሊሞላኝ የተቃረበ ሲሆን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” ለማለት እችላለሁ።—2 ቆሮንቶስ 12:9, 10

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚያዝያ 1939 በጌስታፖዎች ተይዘን ተወሰድን

ግንቦት 1939፣ ጌስታፖዎች በእኔ ላይ ያቀረቡትን ክስ የሚያሳይ ሰነድ

[ምንጭ]

Both images: Privatarchiv; B. Rammerstorfer

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአቅራቢያችን በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች እደበቅ ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Foto Hofer, Bad Ischl, Austria