በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በብዙ አገሮች የሠርግ ስጦታ መስጠት የተለመደ ነው። እንደዚህ ዓይነት ስጦታዎች ስንሰጥ ወይም ስንቀበል የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልናስብባቸው ይገባል?

በትክክለኛ ዝንባሌና በተገቢው ወቅት እስከተደረገ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ መስጠትን አያወግዝም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ስጦታ በመስጠት ረገድ ለጋስ የሆነውን ይሖዋን እንዲመስሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታቸዋል። (ያዕቆብ 1:17) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” በማለት አሳስቧቸዋል። ከዚህ እንደምንረዳው ክርስቲያኖች ለጋስ እንዲሆኑ ተበረታትተዋል።​—⁠ዕብራውያን 13:16፤ ሉቃስ 6:38

በአንዳንድ አገሮች ተጋቢዎች ወደ አንድ ሱቅ በመሄድ በስጦታ ሊያገኟቸው የሚፈልጓቸውን ዕቃዎች ከመረጡ በኋላ ዝርዝሩ እንዲዘጋጅላቸው ይጠይቃሉ። ከዚያም ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ይህ የስጦታ ዝርዝር ወደሚገኝበት ሱቅ ሄደው እንዲገዙ ግብዣ ይቀርብላቸዋል። በአንድ በኩል ሲታይ እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ስጦታ የሚሰጠውን ሰው ተስማሚ ዕቃ ለመምረጥ ረጅም ሰዓት ከማባከን የሚገላግለው ከመሆኑም በላይ ስጦታው የሚሰጣቸው ሰዎችም የማይፈልጉትን ስጦታ ተቀብለው በኋላ ለሱቁ ለመመለስ ከመቸገር ያሳርፋቸዋል።

እንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አለማድረግ የተጋቢዎቹ ምርጫ ነው። ሆኖም አንድ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ነገር እንዳያደርግ ሊጠነቀቅ ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ ተጋቢዎቹ የመረጧቸው የስጦታ ዕቃዎች በሙሉ በጣም ውድ ቢሆኑስ? እንደዚህ ካደረጉ አቅማቸው ውስን የሆነ ሰዎች ስጦታ መስጠቱ ሊከብዳቸው ይችላል፤ ወይም ደግሞ ዋጋው ረከስ ያለ ስጦታ አምጥተው ከመሸማቀቅ ጭራሽ በሠርጉ ላይ ላለመገኘት ይመርጡ ይሆናል። አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የሠርግ ስጦታ መስጠት ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነው። በዚህ ረገድ ለጋስ ለመሆን ብፈልግም አሁን አሁን ግን ስጦታ መስጠት ደስታ እያሳጣኝ ነው።” የአንድ ሰው ሠርግ በሌሎች ላይ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚያሳድር መሆኑ እንዴት የሚያሳዝን ነው!

በእርግጥም ስጦታ የሚሰጡ ሰዎች ስጦታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ከአንድ የተወሰነ ሱቅ የተገዛ ወይም ውድ መሆን እንዳለበት ሊሰማቸው አይገባም። ደግሞም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው የሰጪውን የልብ ዝንባሌ እንጂ የስጦታውን ውድነት አለመሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 21:1-4) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ ለተቸገሩ ሰዎች በልግስና የሚደረጉ ስጦታዎችን በተመለከተ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ሲል ጽፏል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:7

አንድ ሰው ስጦታ በሚሰጥበት ጊዜ ማንነቱን የሚገልጽ ካርድ ከስጦታው ጋር አያይዞ ቢሰጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ምንም ስሕተት የለውም። ሆኖም በአንዳንድ ቦታዎች ስጦታውንና ሰጪውን ለተገኙት ሁሉ ማስተዋወቅ የተለመደ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው። ስጦታ የሚሰጡ ሰዎች አላስፈላጊ ትኩረት ላለመሳብ ሲሉ ስማቸው እንዳይነገር ይፈልጉ ይሆናል። እነዚህ ግለሰቦች ኢየሱስ በማቴዎስ 6:3 ላይ “አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዳደረጉ ያሳያል። ሌሎች ደግሞ ስጦታ መስጠት በሰጪውና በተቀባዩ መካከል መቅረት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ከዚህም በላይ አንድን ስጦታ ማን እንደሰጠ መናገሩ ስጦታዎችን በማወዳደር ‘የፉክክር መንፈስ እንዲፈጠር’ ሊያደርግ ይችላል። (ገላትያ 5:26 NW ) ክርስቲያኖች ስጦታ የሰጡትን ሰዎች ስም በተጋባዦቹ ፊት በመጥራት እንዲያፍሩ ወይም እንዲሸማቀቁ ማድረግ እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:8

በእርግጥም፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ስጦታ መስጠት ደስታ ያስገኛል።​—⁠ሥራ 20:35