በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ቶርኦ በኖሩበት ዘመንና እኛ በምንኖርበት ዘመን መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ። አንዱና ትልቁ ልዩነት በዛሬው ጊዜ ውስጣዊ ሰላም እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ምክር የሚሰጡ በርካታ ምንጮች መኖራቸው ነው። የስነ ልቦና ባለሞያዎችና የራስ አገዝ መጻሕፍት ደራሲያን ሌላው ቀርቶ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጆች እንኳን የየራሳቸውን ምክር ይለግሳሉ። የሚሰጡት ምክር ለጊዜው ይጠቅም ይሆናል፤ ሆኖም ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖር ከተፈለገ በጥልቅ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምክር ማግኘት አስፈላጊ ነው። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች የተገነዘቡትም ይህንኑ ነው።

አንቶንዮ፣ ማርኮስ፣ ጌርዞን፣ ቫኒ እና ማርሴሉ የተለያየ አስተዳደግና እውቀት ያላቸው ሲሆን ችግሮቻቸውም እንዲሁ ለየቅል ናቸው። ሆኖም ቢያንስ ሦስት ነገሮች አንድ ያደርጓቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ወቅት ‘በዚህ ዓለም ተስፋን አጥተውና ከአምላክ ተለይተው’ የኖሩበት ጊዜ ነበር። (ኤፌሶን 2:​12) በሁለተኛ ደረጃ የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ይመኙ ነበር። እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ሁሉም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመሩ በኋላ የፈለጉትን ውስጣዊ ሰላም አግኝተዋል። በጥናታቸው እየገፉ ሲሄዱ አምላክ እንደሚያስብላቸው ተገነዘቡ። በእርግጥም ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩ አቴናውያን እንደተናገረው አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሥራ 17:​27) ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት ይህንን ከልብ መገንዘብ ወሳኝ ነው።

ሰላም የጠፋው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ሰላም የጠፋበትን ማለትም ሰዎች ውስጣዊ ሰላምም ሆነ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሰላም ያጡበትን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይገልጻል። የመጀመሪያው በ⁠ኤርምያስ 10:​23 ላይ ተገልጿል:- “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” የሰው ልጅ ያለ ምንም እገዛ ራሱን በራሱ ለመግዛት የሚያስችል ጥበብም ሆነ አርቆ አስተዋይነት የሌለው ሲሆን ጠቃሚ የሆነ እርዳታ መስጠት የሚችለው ደግሞ አምላክ ብቻ ነው። የአምላክን መመሪያ አንከተልም የሚሉ ሰዎች ዘላቂ ሰላም ፈጽሞ አያገኙም። ሰላም የጠፋበት ሁለተኛው ምክንያት ሐዋርያው ዮሐንስ በተናገራቸው ቃላት ውስጥ ይገኛል:- ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ (1 ዮሐንስ 5:​19) ሰው መለኮታዊ መመሪያ ሳያገኝ ሰላም ለማግኘት የሚያደርገው መፍጨርጨር በማይታየው ነገር ግን ሕያውና በጣም ኃያል በሆነው “በክፉው” ማለትም በሰይጣን እንቅስቃሴ ይከሽፋል።

ብዙ ሰዎች የአምላክን መመሪያ ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጋቸውና ሰይጣን በዓለም ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ የሰው ዘር ባጠቃላይ በችግር ውስጥ እንዲዳክር አድርጎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን” ሲል ሁኔታውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (ሮሜ 8:​22) በዚህ አባባል የማይስማማ ማን ሊኖር ይችላል? በሃብታምም ሆነ በድኻ አገሮች የቤተሰብ ችግር፣ ወንጀል፣ አድሏዊነት፣ የባሕርይ አለመጣጣም፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የጎሣና የዘር ጥላቻ፣ ጭቆና፣ በሽታ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች የሰዎችን የአእምሮ ሰላም ይነሳሉ።

ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የሚቻልበት መንገድ

አንቶንዮ፣ ማርኮስ፣ ጌርዞን፣ ቫኒ እና ማርሴሉ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ሕይወታቸውን የሚለውጡ ነገሮችን ተማሩ። አንደኛ ነገር የዓለም ሁኔታ አንድ ቀን እንደሚለወጥ ተገነዘቡ። ይህ፣ አንድ ቀን ሁሉም ነገር መስተካከሉ አይቀርም የሚል እንዲያው የተድበሰበሰ ተስፋ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለሰው ልጆች ያወጣውን ዓላማ የሚያመለክት እውን የሆነና ጽኑ መሠረት ያለው እምነት ነው። የአምላክን ፈቃድ ካደረግን አሁንም እንኳን ከዚህ ዓላማ ተጠቃሚዎች መሆን እንችላለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረጋቸው ሁኔታዎች ተሻሽለውላቸዋል። ካሰቡት የበለጠ ደስታና ሰላም አግኝተዋል።

አንቶንዮ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሠራተኞች በሚያካሂዱት ተቃውሞና ዓመፅ መካፈሉን አቆመ። በዚህ መንገድ የሚመጣ ለውጥ ውስንና ጊዜያዊ ብቻ እንደሆነ ተገነዘበ። ቀድሞ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀ መንበር የነበረው ይህ ሰው ስለ አምላክ መንግሥት ተማረ። ይህ መንግሥት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጌታን ጸሎት (አባታችን ሆይ) ሲደግሙ አምላክን “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው የሚለምኑት መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:​10ሀ) አንቶንዮ የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር እውነተኛ ሰላም የሚያመጣ እውን ሰማያዊ መስተዳድር መሆኑን ተረዳ።

ማርኮስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ የሚሰጠውን ጥበብ ያለበት ምክር እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተማረ። በውጤቱም ቀድሞ ፖለቲከኛ የነበረው ይህ ሰው ከሚስቱ ጋር ታርቆ እንደገና አብሮ መኖር በመጀመሩ ደስተኛ ነው። እሱም እንደዚሁ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ስግብግብና ራስ ወዳድ የሆነውን ይህን ዓለም በሚሻል ሥርዓት የሚተካበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል። በጌታ ጸሎት ውስጥ የሚገኘው “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚለው ዓረፍተ ነገር ትርጉሙ ምን እንደሆነ ጥልቅ ማስተዋል አግኝቷል። (ማቴዎስ 6:​10ለ) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲሆን ሰዎች ከዚህ በፊት ያልታየ አስደሳች ሕይወት ያገኛሉ።

ስለ ጌርዞንስ ምን ለማለት ይቻላል? ከዚያ በኋላ ከከተማ ወደ ከተማ መዞሩንም ሆነ መስረቁን አቁሟል። ቀድሞ የጎዳና ተዳዳሪ የነበረው ይህ ልጅ አሁን ሕይወቱ ትርጉም ያለው ሆኖለታል፤ ምክንያቱም ጉልበቱን ሌሎች ሰዎች ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኙ ለመርዳት እየተጠቀመበት ነው። እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ያጠኑትን ተግባራዊ ማድረግ የአንድን ሰው ሕይወት በእጅጉ ሊለውጥና የተሻለ ሊያደርግ ይችላል።

ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት

በአምላክ ፈቃድ አፈጻጸም ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ስለ ኢየሱስ ብዙ ይማራሉ። ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት መላእክት እንዲህ ሲሉ በመዝሙር አምላክን አወድሰው ነበር:- “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።” (ሉቃስ 2:​14) ኢየሱስ ካደገ በኋላ የሰዎች ሕይወት ስለሚሻሻልበት ሁኔታ ያስብ ነበር። ስሜታቸውን ይረዳላቸውና በጣም የተጎዱ እንዲሁም የታመሙ ሰዎች ሲያገኝ የላቀ ርኅራኄ ያሳያቸው ነበር። እንዲሁም መላእክት ከዘመሩት ውዳሴ ጋር በሚስማማ መንገድ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም አስገኝቷል። በአገልግሎት ዘመኑ ፍጻሜ ላይ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው:- “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።”​—⁠ዮሐንስ 14:​27

ኢየሱስ እንዲሁ የበጎ አድራጎት ተግባር ብቻ የሚያከናውን ሰው አልነበረም። “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” ብሎ በተናገረ ጊዜ ራሱን ከእረኛ ጋር ያወዳደረ ሲሆን ቅን የሆኑ ተከታዮቹን ደግሞ ከበግ ጋር አመሳስሏቸዋል። (ዮሐንስ 10:​10, 11) አዎን፣ ከምንም ከማንም በላይ ለራሳቸው የሚያስቡ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ መሪዎች ከሚያደርጉት በተቃራኒ ኢየሱስ ለበጎቹ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል።

ኢየሱስ ካደረገው ከዚህ ነገር ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የሚሉትን ቃላት በሚገባ ያውቋቸዋል። (ዮሐንስ 3:​16) በኢየሱስ ለማመን ከሁሉ በፊት ስለ እሱና ስለ አባቱ ስለ ይሖዋ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነው እውቀት ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ወደ መመሥረት የሚመራን ሲሆን ይህም የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል።

ኢየሱስ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም አይጠፉም፣ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም” ብሏል። (ዮሐንስ 10:​27, 28) እንዴት ያለ አስደሳችና አጽናኝ አነጋገር ነው! እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከተናገረ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ዓመታት ቢሆናቸውም አሁንም በዚያ ወቅት የነበራቸው ኃይል አላቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በመግዛት ላይ የሚገኝ ንጉሥ ሲሆን አሁንም ሕያው እንደሆነና ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ፈጽሞ አትዘንጋ። ከብዙ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ሳለ እንዳደረገው ሁሉ የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ለሚፈልጉ ቅን ሰዎች ያስባል። በተጨማሪም አሁንም ለበጎቹ እረኛ ነው። ከተከተልነው ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን መርዳት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ዓመፅ፣ ጦርነትና ወንጀል ተወግዶ ፍጹም ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ ለማየት በሙሉ ልብ እንድንጠብቅ ያደርገናል።

ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት እንደሚረዳን ማወቅና ማመን ከፍተኛ ጥቅም አለው። ገና በልጅነቷ ከባድ ኃላፊነቶች የተጫነባትንና አምላክ ረስቶኛል ብላ ያሰበችውን ቫኒን አስታውስ። ቫኒ አሁን አምላክ እንዳልተዋት አውቃለች። እንዲህ ትላለች:- “አምላክ ተወዳጅ ባሕርያት ያሉት ሕያው አካል እንደሆነ ተምሬያለሁ። እኛ ሕይወት እንድናገኝ ሲል ልጁን ወደ ምድር ለመላክ የገፋፋው ፍቅሩ ነው። ይህን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።”

ማርሴሉ ከአምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት እውነተኛ እንደሆነ ይናገራል። ቀድሞ ጭፈራ ወዳድ የነበረው ይህ ሰው እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል:- “ወጣቶች ብዙ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስለማያውቁ በመጨረሻ በራሳቸው ላይ ጉዳት ያመጣሉ። አንዳንዶች እኔ ሳደርግ እንደነበረው አደገኛ ዕፆች ይወስዳሉ። ብዙዎች ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውቀት በመማር እንደ እኔ በረከት እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ቫኒ እና ማርሴሉ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በማጥናት በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ገንብተዋል እንዲሁም እሱ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲችሉ ለመርዳት ባለው ፈቃደኝነት ላይ ትምክኽት አዳብረዋል። እኛም መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠና እና ያጠናነውን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ እንደ እነርሱ ይህ ነው የማይባል ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ማበረታቻ በእርግጥ በእኛም ላይ ይሠራል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ሰላም ማግኘት

ኢየሱስ ክርስቶስ እውነትን የተራቡ ሰዎችን በምድራዊ ገነት ውስጥ ወደሚያገኙት የዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እየመራቸው ነው። ወደ አምላክ ንጹሕ አምልኮ ሲመራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው ጋር የሚመሳሰል ሰላም ያገኛሉ:- “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።” (ኢሳይያስ 32:​18) ይህ ደግሞ ወደፊት በደንብ ለሚያጣጥሙት ሰላም ቅምሻ ይሆንላቸዋል። እንዲህ እናነባለን:- “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”​—⁠መዝሙር 37:​11, 29

ስለዚህ ባሁኑ ጊዜ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን ማለት ነው? አዎን። ከዚህም በላይ አምላክ በቅርቡ ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያልታየ ሰላም በመስጠት ታዛዥ ሰዎችን እንደሚባርክ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ታዲያ ሰላም እንዲሰጥህ ለምን በጸሎት አትጠይቀውም? ሰላም የሚነሱህ ችግሮች ካሉብህ ንጉሥ ዳዊት በጸለየው መንገድ ጸሎት አቅርብ:- “የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። ድካሜንና መከራዬን እይ፣ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።” (መዝሙር 25:​17, 18) አምላክ እንደዚህ ያሉ ጸሎቶችን እንደሚሰማ እርግጠኛ ሁን። ሰላምን በቅን ልቦና ለሚሹ ሁሉ እጁን ዘርግቶ ሰላምን ይሰጣቸዋል። “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም” የሚል ፍቅራዊ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።​—⁠መዝሙር 145:​18, 19

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሰው ልጅ ያለ ምንም እገዛ ራሱን በራሱ ለመግዛት የሚያስችል ጥበብም ሆነ አርቆ አስተዋይነት የሌለው ሲሆን ጠቃሚ የሆነ እርዳታ ማግኘት የሚችለው ከአምላክ ብቻ ነው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምናገኘው እውቀት ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ወደ መመሥረት የሚመራን ሲሆን ይህም የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ሰላም የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን አስተዋጽዖ ያደርጋል