በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ

ሚያዝያ 2010 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ በሚገኝ ነዳጅ ማውጫ ላይ አደጋ በመድረሱ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ዘይት ለሦስት ወራት ያህል ባሕሩ ውስጥ ፈሰሰ። አንድ የተመራማሪዎች ቡድን ባካሄደው ጥናት መሠረት አደጋው ከደረሰ ከሁለት ወር ተኩል በኋላ አንዳንዶቹ በካይ መርዞች እንደተወገዱ ተደርሶበታል፤ ተመራማሪዎቹ ሜቴይን የተባለውን ጋዝ የሚወዱ ባክቴሪያዎች እነዚህን መርዞች በልተዋቸው ሊሆን እንደሚችል ደምድመዋል። አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች ግን ይህ መሆኑን ይጠራጠራሉ። እነዚህ ተመራማሪዎች አብዛኛው የነዳጅ ዘይት ውቅያኖሱ ውስጥ እንደዘቀጠ ይሰማቸዋል።

ሩሲያ

ሩሲስካያ ጋዝዬታ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በሩሲያ ከ18 እስከ 35 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሰዎች መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት “በሕይወትህ ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ከፈለግህ ከምታምንባቸው የሥነ ምግባር ደንቦችና መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነገር ለማድረግ የምትገደድበት ጊዜ” እንደሚኖር ይሰማቸዋል።

ፔሩ

ብዙ ዘመን ያስቆጠሩ አንዳንድ ቆረቆንዳዎች (ከላይ እንደሚታየው ዓይነት) እንደሚጠቁሙት ቢያንስ ከ3,000 ዓመታት በፊት በሰሜናዊ ፔሩ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ፈንዲሻ ያፈኩ እንዲሁም የበቆሎ ዱቄት ይጠቀሙ ነበር።

ጣሊያን

ሉቾ ሶራቪቶ ደ ፍራንቼስኪ የተባሉት የአድሪኣ ሮቪጎ ጳጳስ፣ ሃይማኖታዊ መልእክት “ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ሊደርሳቸው” እንደሚገባ ያምናሉ። እኚህ የካቶሊክ ጳጳስ እንዲህ ብለዋል፦ “ለመንጎቻችን የምናደርገው እንክብካቤ የቤተ ክርስቲያን ደወል ከመደወል አልፎ የሰዎች ቤት ድረስ ሄዶ በማንኳኳት ግለሰቦችን መርዳትን የሚያካትት ሊሆን ይገባል።”

ደቡብ አፍሪካ

ለሕክምና አገልግሎት የሚውል አንድ ኪሎ የአውራሪስ ቀንድ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚሸጥበት ዋጋ 65,000 የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። በ2011 በደቡብ አፍሪካ ብቻ 448 አውራሪሶች በአዳኞች እንደተገደሉ ሪፖርት ተደርጓል። እነዚህን ቀንዶች የሚፈልጉ ወንበዴዎች በአውሮፓ የሚገኙ ሙዚየሞችንና የጨረታ ሽያጭ የሚካሄድባቸውን ቤቶች ሰብረው ገብተዋል። በአውሮፓ ባሉ መካነ አራዊት የሚገኙ አውራሪሶች እንኳ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ እየተነገረ ነው።