በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ፓውላ ኪዮሲ

የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች?

የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች?

 

ዶክተር ፓውላ ኪዮሲ ጣሊያን በሚገኘው ፈራራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሞለኪውል ባዮሎጂ ባለሙያ ሆና ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ሠርታለች። ንቁ! መጽሔት ስለ ሙያዋና ስለ እምነቷ አነጋግሯታል።

እስቲ ስለ አስተዳደግሽ ንገሪን።

አባቴ ጫማ ሠሪ ሲሆን እናቴ ደግሞ ገበሬ ነበረች። እኔ ግን የሳይንስ ሊቅ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። በቤታችን አካባቢ የነበሩት የሚያማምሩ አበቦች፣ ወፎችና ሌሎች ነፍሳት በጣም ያስደንቁኝ ነበር። እነዚህ ነገሮች ከሰው በላይ የሆነ ከፍተኛ ጥበብ ያለው አካል የእጅ ሥራዎች እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር።

ከድሮም ጀምሮ በፈጣሪ ታምኚ ነበር ማለት ነው?

አላምንም ነበር። እንዲያውም አምላክ መኖሩን መጠራጠር የጀመርኩት ገና ልጅ እያለሁ ነው። አባቴ በልብ ሕመም የተነሳ በድንገት ሞተ፤ በዚህም ምክንያት ‘እነዚህን ሁሉ ውብ ነገሮች የፈጠረው አካል መከራና ሞት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ።

በሳይንስ መስክ ያደረግሽው ጥናት ለዚህ ጥያቄ መልስ እንድታገኚ ረዳሽ?

መጀመሪያ ላይ አልረዳኝም። የሞለኪውል ባዮሎጂ ባለሙያ ከሆንኩ በኋላ ስለ ሴሎች ሞት ማጥናት ጀመርኩ። ጥናቴን የማካሂደው አካላችን የተገነባባቸው ሴሎች ተፈጥሯዊ ሂደታቸውን ጠብቀው ስለሚሞቱበት ሁኔታ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ የሴሎች ሞት፣ ሕብረ ሕዋሶች በቂ ኦክስጅን ወይም ደም ባለማግኘታቸው ምክንያት ከሚከሰተውና ለቁስል ማመርቀዝ ብሎም ለጋንግሪን መንስኤ ከሚሆነው የሴሎች ሞት የተለየ ነው። ይህ ሂደት ለጤንነታችን በጣም አስፈላጊ ቢሆንም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር።

ይህ ሂደት አስፈላጊ የሆነው በምን መንገድ ነው?

አካላችን የተገነባው በትሪሊዮን በሚቆጠሩ በዓይን የማይታዩ ሴሎች ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል መሞታቸውና በሌላ ሴል መተካታቸው የግድ ነው። የእያንዳንዱ ዓይነት ሴል ዕድሜ የተለያየ ነው፤ አንዳንዶቹ በየሳምንቱ የሚተኩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በየጥቂት ዓመታት ይተካሉ። ሴሎች የሚሞቱበትና አዳዲስ ሴሎች የሚፈጠሩበት ውስብስብ የሆነ ሂደት ሁልጊዜ በትክክል መሥራት አለበት።

 ከዚህ ሂደት ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ስህተት ሊፈጠር ይችላል?

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴሎች መሞት በሚገባቸው ጊዜ ሳይሞቱ ሲቀሩ እንደ ሩማቶይድ አርትራይተስ ወይም ካንሰር የመሰሉ የጤና እክሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሴሎች መሞት ከሚገባቸው ጊዜ ቀድመው ሲሞቱ እንደ ፓርኪንሰንስ እና አልዛይመርስ የመሰሉት በሽታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። እኔ ምርምር የማደርገው እነዚህን በሽታዎች ማከም ስለሚቻልበት መንገድ ነው።

ስለ ሴሎች አሟሟት ያደረግሽው ጥናት የነካሽ እንዴት ነው?

እውነቱን ለመናገር በጥናቴ የደረስኩበት ነገር ግራ አጋብቶኝ ነበር። ይህ አስደናቂ የሆነ ሂደት ጤነኛ ሆነን እንድንኖር በሚፈልግ አንድ አካል የተቀናበረ እንደሆነ ግልጽ ነው። ‘ይህ ከሆነ ታዲያ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው እና የሚሞቱት ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ መመላለሱ አልቀረም። ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት አልቻልኩም።

ሴሎች ተፈጥሯዊ ሂደታቸውን ጠብቀው የሚሞቱበት መንገድ ንድፍ አውጪ እንዳለ እንድታምኚ አድርጎሻል?

ሁሉም ሴሎቻችን ማለት ይቻላል በየጊዜው ስለሚተኩ ለዘላለም መኖር የሚቻል ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው

አዎ። አጠቃላይ ሂደቱ የሚከናወንበት መንገድ እጅግ ውስብስብ በመሆኑ አእምሯችን ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው፤ ሆኖም አሠራሩ የተዋቀረበት መንገድ አስደናቂ ጥበብ የተንጸባረቀበት እንደሆነ ግልጽ ነው። የዚህ ጥበብ ምንጭ አምላክ እንደሆነ አምናለሁ። ይህን ሂደት የሚቆጣጠሩትን ውስብስብ አሠራሮች ለማጥናት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው አጉሊ መነጽሮችን እጠቀማለሁ። አንዳንዶቹ አሠራሮች፣ አስፈላጊ ከሆነ በሴኮንዶች በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ ሴሎች እንዲጠፉ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሴሎቹም ራሳቸውን በማጥፋት በዚህ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና አለ። መላው ሂደት አስገራሚ በሆነ መንገድ የተቀነባበረ በመሆኑ እጅግ በጣም ያስደንቃል።

ስለ አምላክ እና ስለ መከራ ለነበረሽ ጥያቄ መልስ ያገኘሽው እንዴት ነው?

በ1991 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ ሲመጡ የምንሞተው ለምን እንደሆነ ጠየቅኳቸው። እነሱም “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” የሚለውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማውጣት መልስ ሰጡኝ። (ሮም 5:12) የመጀመሪያው ሰው የአምላክን ትእዛዝ ባይጥስ ኖሮ ለዘላለም መኖር ይችል ነበር። ይህ ሐሳብ በጥናቴ ካስተዋልኩት ነገር ጋር እንደሚስማማ ወዲያውኑ ተገነዘብኩ። አምላክ ሰዎች እንዲሞቱ ዓላማው እንዳልነበረ ማወቅ ችዬ ነበር። ሁሉም ሴሎቻችን ማለት ይቻላል በየጊዜው ስለሚተኩ ለዘላለም መኖር የሚቻል ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያሳመነሽ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 139:16 (NW) ላይ ስለ አምላክ ሲናገር “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ” እንደሚል አወቅሁ። የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን በሴሎቻችን ውስጥ ተመዝግቦ ስለሚገኘው መረጃ አጥንቻለሁ። መዝሙራዊው ግን እንዲህ ስላለው በሴሎቻችን ውስጥ የተመዘገበ መረጃ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እየጨመረ በሄደ መጠን በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ስለመሆኑ ያለኝ እምነት እየጠነከረ መጣ።

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት መረዳት እንድትችዪ ምን እገዛ ተደርጎልሻል?

አንድ የይሖዋ ምሥክር አብሬው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ሐሳብ አቀረበልኝ። አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት በመጨረሻ አወቅኩ። በተጨማሪም አምላክ ወደፊት ‘ሞትን ለዘላለም እንደሚውጥ’ ተማርኩ። (ኢሳይያስ 25:8) በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወኑት አስደናቂ ሂደቶች ፍጹም በሆነ መንገድ እንዲሠሩ በማድረግ ለዘላለም ለመኖር የሚያስችለንን ሁኔታ ማዘጋጀት ለፈጣሪ ከባድ ነገር አይሆንበትም።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሽውን እውቀት ሌሎችን ለመርዳት የተጠቀምሽበት እንዴት ነው?

በ1995 የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን ነገሮች ለሌሎች እያካፈልኩ ነው። ለምሳሌ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ወንድሟ ሕይወቱን በማጥፋቱ በጣም አዝና ነበር። አምላክ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎችን ፈጽሞ ይቅር እንደማይል በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ተምራለች። እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የትንሣኤ ተስፋ እንደሚሰጥ ነገርኳት። (ዮሐንስ 5:28, 29) ፈጣሪ እንደሚያስብልን ማወቋ በእጅጉ አጽናናት። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ስመለከት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ማካፈል ስለ ሳይንስ ከመናገር የበለጠ እርካታ እንደሚያስገኝልኝ ይሰማኛል!