በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ገነት

ገነት

ገነት ምንድን ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንድ ሰዎች ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ሳይሆን ተረት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ገነት ጥሩ ሰዎች ፍሬያማ ሥራዎችን እያከናወኑ ለዘላለም ተደስተው የሚኖሩበት የአትክልት ስፍራ እንደሆነ ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ገነት” የሚለው ቃል የሰው ልጆችን የመጀመሪያ መኖሪያ ይኸውም የኤደንን የአትክልት ስፍራ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዘፍጥረት 2:7-15) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የአትክልት ስፍራ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከበሽታና ከሞት ነፃ ሆነው ይኖሩበት የነበረ እውነተኛ ቦታ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:27, 28) እነዚህ ባልና ሚስት አምላክን ባለመታዘዛቸው በገነት የነበራቸውን መኖሪያ አጡ። ይሁንና የሰው ልጆች ወደፊት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ እንደሚኖሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይናገራሉ።

አንተን ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?

አምላክ አፍቃሪ ከሆነ ታማኝ አምላኪዎቹን በገነት ውስጥ ጥሩ ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ይባርካቸዋል ብለን ማሰባችን ምክንያታዊ ነው። በተጨማሪም ሰዎች የእሱን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያሳውቃቸዋል ብለን መደምደማችን ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ስለ አምላክ እውቀት በመቅሰምና እሱን በመታዘዝ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደምንችል ይናገራል።—ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 5:3

“አምላክ . . . በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው።”—ዘፍጥረት 2:8

 ገነት የሚገኘው የት ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንዶች ገነት የሚገኘው በሰማይ እንደሆነ ያምናሉ፤ ሌሎች ደግሞ ምድር ወደፊት ገነት እንደምትሆን ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የሰው ልጆች መኖሪያ የነበረው የመጀመሪያው ገነት የሚገኘው ምድር ላይ ነበር። አምላክ ምድርን የፈጠረው የሰው ልጆች ቋሚ መኖሪያ እንድትሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ምድርን ለዘላለም እንድትኖር አድርጎ እንደሠራት ይገልጻል። (መዝሙር 104:5) በተጨማሪም “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል።—መዝሙር 115:16

ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ገነት እንደምትሆን መናገሩ የሚያስገርም አይደለም። አምላክ ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ ሰዎችን የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርካቸዋል። በዚያ ሰላምና ጸጥታ ይሰፍናል። ሕመምና ሥቃይ አይኖርም። እንዲሁም የሰው ልጆች በምድር ላይ ያሉትን ድንቅ ነገሮች ሁሉ እያጣጣሙ ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 65:21-23

“የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው . . . ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:3, 4

በገነት ውስጥ የሚኖሩት እነማን ናቸው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሃይማኖቶች፣ በገነት ውስጥ የሚኖሩት ጥሩ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ያስተምራሉ። “ጥሩ” የሚባሉት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ግን የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። አንዳንድ ሰዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መካፈልና በዘልማድ የሚደረጉትን ጸሎቶች መድገም ብቻ በቂ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በገነት ውስጥ የሚኖሩት “ጻድቃን” እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና አምላክ እንደ ጻድቃን የሚቆጥረው እነማንን ነው? በሃይማኖታዊ ሥርዓት እየተካፈሉ የእሱን ፈቃድ ችላ የሚሉ ሰዎችን እንደ ጻድቃን እንደማይቆጥር ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት . . . ይበልጣል።” (1 ሳሙኤል 15:22) በአጭር አነጋገር በገነት ውስጥ ለዘላለም የሚኖሩት “ጻድቃን” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የአምላክ ሕጎች የሚታዘዙ ሰዎች ናቸው።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የአምላክን ሕጎች መታዘዝ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ከመካፈል ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናሳየው ምግባር አምላክን የሚያስደስት አሊያም የሚያሳዝን ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በመመርመር አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደምትችል መማር ትችላለህ። ደግሞም አምላክን ማስደሰት ከባድ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ትእዛዛቱ . . . ከባዶች አይደሉም” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:3) ታዛዥ ከሆንክ አምላክ፣ አንተን በገነት ውስጥ ለማኖር እንደሚናፍቅ እርግጠኛ ሁን።

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29