በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ራስ ወዳድ በሆነ ዓለም ውስጥ ጨዋ ልጆች ማሳደግ

ራስ ወዳድ በሆነ ዓለም ውስጥ ጨዋ ልጆች ማሳደግ

በየቀኑ ለሌሎች መልካም ነገር ማድረግ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ይሁንና በየዕለቱ እንደሚታየው ብዙዎች የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ይመስላል። የትም ብትሄድ ሰዎች ዓይን ያወጣ ማጭበርበር ሲፈጽሙ፣ ሥርዓት በጎደለው መንገድ መኪና ሲያሽከረክሩ እንዲሁም አስጸያፊ ነገር ሲናገሩና በቁጣ ሲደነፉ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

በብዙ ቤተሰቦች ውስጥም እንዲህ ያለው የራስ ወዳድነት መንፈስ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ባለትዳሮች የትዳር ጓደኛቸው እንደማይመጥናቸውና ሌላ “የተሻለ ሰው” ማግባት እንደሚችሉ ስለሚሰማቸው ትዳራቸውን ያፈርሳሉ። አንዳንድ ወላጆችም እንኳ ሳይታወቃቸው ልጆቻቸው የራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲያድርባቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዴት? ልጃቸው እንዳሻው እንዲሆን በመፍቀድ የሚያቀብጡት ከመሆኑም ሌላ ልጁን ከመቅጣት ወደኋላ ይላሉ።

በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች ብዙ ወላጆች፣ ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ እንዲሰጡ ልጆቻቸውን እያሠለጠኗቸው ሲሆን ይህም ብዙ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ለሌሎች አሳቢነት የሚያሳዩ ልጆች፣ ጓደኞች ማፍራትና ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት አስቸጋሪ አይሆንባቸውም። በተጨማሪም እንደዚህ ያሉት ወጣቶች በሕይወታቸው እርካታ ይኖራቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ ለሌሎች አሳቢነት የሚያሳዩና ጨዋ እንዲሆኑ በመርዳት እንዲሁም በዓለም ላይ የተስፋፋው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዳያበላሻቸው በመከላከል ጠቃሚ ሥልጠና ልትሰጣቸው የምትችለው እንዴት ነው? በልጆችህ ውስጥ የራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርጉ ሦስት ችግሮችንና እነዚህን ችግሮች መፍታት የምትችልበትን መንገድ እስቲ እንመልከት።

 1 ከልክ በላይ ማሞገስ

ችግሩ፦ ተመራማሪዎች፣ አሳሳቢ የሆነ አዝማሚያ በብዙዎች ዘንድ እየተስፋፋ እንደሆነ ገልጸዋል፤ ይኸውም ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡ ብዙ ወጣቶች ለራሳቸው የተጋነነ ግምት አላቸው፤ በሌላ አባባል ያከናወኑት ነገር ያን ያህል ትልቅ የሚባል ባይሆንም ወይም ምንም ያከናወኑት ነገር ባይኖርም እንኳ ስኬት ማግኘት ይፈልጋሉ። አንዳንዶች ሙያቸውን እንኳ ጠንቅቀው ሳያውቁ በፍጥነት እድገት ለማግኘት ይጠብቃሉ። ሌሎች ደግሞ ልዩ ቦታ እና ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም ሌሎች ሰዎች የእነሱን አመለካከት እንደማይጋሩ ሲገነዘቡ በጣም ይከፋቸዋል።

መንስኤው ምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለራሳቸው የተጋነነ ግምት እንዲኖራቸው የሚያደርገው አስተዳደጋቸው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የተስፋፋውና በራስ የመተማመን መንፈስን ለማጎልበት እንደሚረዳ የሚታሰበው አመለካከት በአንዳንድ ወላጆች ላይ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። ይህ አመለካከት ከላይ ከላይ ሲታይ ትክክለኛ ይመስላል፤ ልጆችን በመጠኑ ማሞገስ ጥሩ ከሆነ የበለጠ ማሞገሱ ደግሞ የተሻለ ጥቅም እንደሚኖረው ይገለጻል። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች በልጆቻቸው እንዳልተደሰቱ መግለጻቸው ልጆቹን ተስፋ ከማስቆረጥ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይነገራል። እንዲሁም ልጆች ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጥበት ዓለም ውስጥ ልጆቻቸውን በዚህ መንገድ የማያሳድጉ ወላጆች ኃላፊነታቸው በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ ተደርገው ይታያሉ። ልጆች እንዳጠፉ እንዲሰማቸው ማድረግ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልሆነ ይገለጻል።

በመሆኑም ብዙ አባቶችና እናቶች ልጆቻቸው አድናቆት የሚገባው ነገር ባያከናውኑም እንኳ ከመጠን በላይ ያሞካሿቸዋል። ልጆቹ ያከናወኑት ትንሹ ነገር እንኳ ተጋንኖ ይነገራል፤ በሌላ በኩል ግን ልጆቹ የቱንም ያህል ትልቅ ስህተት ቢፈጽሙ በቸልታ ይታለፋል። እነዚህ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ለመርዳት ከተፈለገ ስህተታቸውን አይቶ እንዳላዩ ማለፍና የሠሩትን ማንኛውንም ነገር ማሞገስ እንደሚገባ ያስባሉ። ልጆች አንድ ጥሩ ሥራ ሠርተው በሥራቸው እንዲደሰቱ ከማበረታታት ይልቅ ምንም ሳያከናውኑ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍ እንዲል ማድረጉ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ለሌሎች አድናቆት መቸር አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። (ማቴዎስ 25:19-21) ይሁን እንጂ ልጆችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ብቻ ብሎ ማሞገስ ስለ ራሳቸው የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከትበት ምንም ነገር ሳይኖረው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ገላትያ 6:3) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ለልጆችህ እርማት ከመስጠት ወደኋላ አትበል፤ ጥብቅ ብትሆንባቸው አይሞቱም” ማለቱ ተገቢ ነው። *ምሳሌ 23:13 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን

ምን ማድረግ ትችላላችሁ? አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለልጆቻችሁ እርማት ስጡ፤ እንዲሁም አድናቆት የሚገባው ነገር ሲያከናውኑ አመስግኗቸው። ልጆቻችሁ ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ስትሉ ብቻ አታሞካሿቸው። እንዲህ ማድረጉ ምንም አይጠቅማቸውም። ጀነሬሽን ሚ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በራስ የመተማመን ስሜትን ተገቢ በሆነ መንገድ ማዳበር የምትችለው ችሎታህን ስታሻሽልና አዳዲስ ነገሮችን ስትማር እንጂ ምንም ሳታከናውን ጎበዝ ስትባል አይደለም።”

“እያንዳንዳችሁ . . . በትሕትና አስቡ እንጂ ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ።”—ሮም 12:3 የ1980 ትርጉም

 2 ከልክ ያለፈ እንክብካቤ

ችግሩ፦ ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡ ብዙ ወጣቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመወጣት ዝግጁ አይደሉም። አንዳንዶቹ ትንሽ ነቀፌታ ሲሰነዘርባቸው በጣም ይደነግጣሉ። ሌሎች ደግሞ በቀላሉ የማይደሰቱ ከመሆናቸውም ሌላ መሥራት የሚፈልጉት ደስ የሚላቸውን ሥራ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት ለሥራ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት “የሥራው ጠባይ አንዳንድ ጊዜ አሰልቺ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል፤ እኔ ደግሞ የሚያሰለች ሥራ አልፈልግም” እንዳለ ዶክተር ጆሴፍ አለን ስኬፒንግ ዚ ኢንድለስ አዶለሰንስ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል። ዶክተር አለን “ይህ ወጣት ማንኛውም ሥራ የሚያሰለች ነገር ሊኖረው እንደሚችል የገባው አይመስልም። አንድ የሃያ ሦስት ዓመት ሰው በዚህ ዕድሜው እንዴት ይህን ማወቅ ይከብደዋል?” በማለት ጽፈዋል።

መንስኤው ምንድን ነው? ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳያጋጥማቸው መከላከል እንደሚገባቸው እየተሰማቸው መጥቷል። ልጃቸው ፈተና ብትወድቅ አስተማሪዋን ማነጋገርና ውጤቷን ከፍ እንዲያደርግላት መጠየቅ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ልጃቸው ክፍሉን ቢያዝረከርክ እነሱ ያስተካክሉለታል። ልጃቸው ከጓደኛው ጋር ቢጣላ ጥፋቱን በጓደኛው ላይ ማላከክ ይቀናቸዋል።

ልጆቻችሁ ችግር እንዳያጋጥማቸው ለመከላከል መፈለጋችሁ ያለ ነገር ቢሆንም ከልክ ያለፈ እንክብካቤ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርጋቸው ይኸውም ለድርጊታቸው ኃላፊነት መውሰድ እንደማያስፈልጋቸው እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ፖዘቲቭ ዲሲፕሊን ፎር ቲንኤጀርስ የሚለው መጽሐፍ በዚህ መንገድ ስለሚያድጉ ልጆች ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ልጆች የሚያሳዝኑ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው ችሎ ማለፍን ከመማር እንዲሁም ከእነዚህ ተሞክሮዎች ትምህርት ከመቅሰም ይልቅ ከመጠን በላይ ራስ ወዳድና ወላጆቻቸውም ሆኑ ሌሎች ሰዎች እነሱ የሚፈልጉትን ነገር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው የሚሰማቸው ይሆናሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ማጋጠማቸው የማይቀር ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ነገሮች በሁሉም ሰው ላይ ይደርሳሉ” ይላል። (መክብብ 9:11 ኢዚ ቱ ሪድ ቨርሽን) ይህም ሲባል ጥሩ ሰዎችም ጭምር ክፉ ነገር ይደርስባቸዋል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ ብዙ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጠሙት ሲሆን እነዚህንም በጽናት ተቋቁሟል። ሆኖም ያጋጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ታግሎ መወጣቱ ጠቅሞታል! እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬያለሁ። . . . ጠግቦም ሆነ ተርቦ፣ ብዙ አግኝቶም ሆነ ተቸግሮ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬያለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:11, 12

ምን ማድረግ ትችላላችሁ? “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለመከተል ጥረት አድርጉ፤ በእርግጥ ይህን ስታደርጉ የልጆቻችሁን የብስለት ደረጃ ከግምት ማስገባት ይኖርባችኋል። (ገላትያ 6:5) ልጃችሁ ክፍሉን ቢያዝረከርክ ራሱ እንዲያስተካክል ማድረጉ የተሻለ ነው። ልጃችሁ ፈተና ብትወድቅ ይህ ለሚቀጥለው ፈተና የተሻለ ዝግጅት እንድታደርግ ትምህርት ሊሆናት ይገባል። እንዲሁም ልጃችሁ ከጓደኛው ጋር ቢጣላ አጽናኑት፤ ሆኖም አመቺ የሆነ ጊዜ መርጣችሁ፣ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆን እሱ የፈጸመው ስህተት ይኖር እንደሆነ መለስ ብሎ እንዲያስብ አበረታቱት። አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ማለፍ የለመዱ ልጆች የመንፈስ ጥንካሬንና በራስ መተማመንን ያዳብራሉ፤ ችግር በገጠማቸው ቁጥር ሰው የሚደርስላቸው ከሆነ ግን እነዚህን ባሕርያት ሳያዳብሩ ይቀራሉ።

“እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም . . . የሚመካበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

 3 ከልክ በላይ መስጠት

ችግሩ፦ በወጣቶች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ 81 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ‘ሀብታም መሆን’ እንደሆነ ተናግረዋል፤ ይህም እነዚህ ወጣቶች ሌሎችን ከመርዳት የበለጠ ለሀብት ቦታ እንደሚሰጡ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ባለጠጋ ለመሆን መጣጣር እርካታ አያስገኝም። እንዲያውም ቁሳዊ ሀብትን የሚያሳድዱ ሰዎች ደስታቸው እንደሚቀንስና በጭንቀት እንደሚዋጡ ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም እንደዚህ ያሉት ሰዎች ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ችግሮች የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው።

መንስኤው ምንድን ነው? አንዳንድ ልጆች የሚያድጉት ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ቦታ በሚሰጥ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ “ወላጆች ልጆቻቸውን ማስደሰት የሚፈልጉ ሲሆን ልጆች ደግሞ ብዙ ነገር እንዲገዛላቸው ይፈልጋሉ” በማለት ይናገራል። “በመሆኑም ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ይገዙላቸዋል። ልጆቹም ለጊዜው ደስ ቢላቸውም ተጨማሪ ነገር እንዲገዛላቸው መጠየቃቸው አይቀርም።”

እርግጥ ነው፣ የማስታወቂያው ኢንዱስትሪ በቃኝ ማለት የማያውቁትን ሸማቾች ለመበዝበዝ ፍላጎታቸውን በሚቀሰቅሱ ማስታወቂያዎች ይጠቀማል። ምርጥ የሆኑ ነገሮችን ማግኘት እንደሚገባን የሚገልጽ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ማስታወቂያዎች ይቀርባሉ። ብዙ ወጣቶች ማስታወቂያዎቹ የሚያስተላልፉት መልእክት ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ከአቅማቸው በላይ በዱቤ በመግዛታቸው በዕዳ ተዘፍቀዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል። (መክብብ 7:12) ያም ቢሆን ግን “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። አክሎም “አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው . . . ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ ቁሳዊ ሀብትን ከማሳደድ ይልቅ ለኑሮ አስፈላጊ በሆኑት መሠረታዊ ነገሮች ረክተን እንድንኖር ያበረታታናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8

“ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም . . . ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9

ምን ማድረግ ትችላላችሁ? እናንት ወላጆች፣ ለገንዘብና ገንዘብ ሊገዛቸው ለሚችላቸው ነገሮች ያላችሁን አመለካከት መርምሩ። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን በማስቀደም ልጆቻችሁም እንዲሁ እንዲያደርጉ እርዷቸው። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተሰኘው ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ወላጆችና ልጆች በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ ይችላሉ፦ ‘የማጣሪያ ሽያጭ በሚኖርበት ጊዜ ብንገዛ ያዋጣናል? የሚወደድብን መቼ ስንገዛ ነው?’ ‘በዱቤ ብንገዛ ወለዱ ምን ያህል ነው?’ ‘አንድን ነገር ሌላ ሰው ስለገፋፋህ ብቻ ገዝተህ ታውቃለህ?’”

በቤተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ተወያይቶ ከመፍታት ይልቅ ብዙ ቁሳዊ ነገሮችን በማቅረብ ችግሩን ለመሸፋፈን አትሞክሩ። ዘ ፕራይስ ኦቭ ፕሪቭሌጅ የተሰኘው መጽሐፍ “ቁሳዊ ነገሮችን በማቅረብ ችግሮችን ለመሸፋፈን መሞከር አያዋጣም” በማለት ይናገራል። “ለችግሮች መፍትሔ የሚገኘው በጉዳዩ ላይ በማሰብ፣ አስተዋይ በመሆንና ራስን በሌሎች ቦታ በማስቀመጥ እንጂ ጫማና ቦርሳ በመግዛት አይደለም።”

^ စာပိုဒ်၊ 11 መጽሐፍ ቅዱስ በልጆች ላይ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ በደል ማድረስን አይደግፍም። (ኤፌሶን 4:29, 31፤ 6:4) ወላጆች ለልጆቻቸው እርማት የሚሰጡት ልጆቹን ለማሠልጠን እንጂ ንዴታቸውን ለመወጣት መሆን የለበትም።