በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?

መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?

መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?

የዚህን ጥያቄ መልስ እንደሚያውቁ የሚናገሩ ቀሳውስት አብዛኛውን ጊዜ መከራ ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንደሆነ ያስተምራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሄይቲ በርዕደ መሬት ከተመታች ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በዋናው ከተማ የሚኖሩ አንድ ቄስ አደጋው ከአምላክ የመጣ መልእክት እንደሆነ ለምዕመኖቻቸው ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ብለው በቀጥታ አያስተምሩም። የሃይማኖት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ አሜሪካዊ ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አመለካከት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “አምላክ እንዲህ ያሉ አደጋዎችን የሚያመጣበት ምክንያት ሚስጥር ከመሆኑም ሌላ እኛ ይህን የመጠየቅ መብት የለንም። የእኛ ድርሻ እምነት ማሳደር ብቻ ነው።”

በሰው ልጆች ላይ መከራ ‘የሚያመጣው’ በእርግጥ አምላክ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መከራ የሚያመጣው አምላክ እንዳልሆነ አበክሮ ይገልጻል! በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የይሖዋ አምላክ ዓላማ አልነበረም። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በአምላክ አገዛዝ ላይ በማመፅ መልካምና ክፉ የሆነውን በተመለከተ የራሳቸውን መሥፈርት አወጡ። ለአምላክ ጀርባቸውን መስጠታቸው ያስከተለባቸውንም መዘዝ ለመቀበል ተገደዱ። እነሱ ባደረጉት መጥፎ ውሳኔ የተነሳ ዛሬም በእኛ ላይ መከራ እየደረሰብን ይገኛል። ሆኖም በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤው በጭራሽ አምላክ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ማንም ሰው ፈተና በሚደርስበት ጊዜ ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። ምክንያቱም አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) በአምላክ ዘንድ ሞገስ ያገኙ ሰዎችን ጨምሮ መከራ በማንም ሰው ላይ ሊደርስ ይችላል። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት፦

● ነቢዩ ኤልሳዕ ለሞት በሚዳርግ በሽታ ተይዞ ነበር።​—2 ነገሥት 13:14

● ሐዋርያው ጳውሎስ “እየተራብንና እየተጠማን፣ እየተራቆትን፣ እየተመታን፣ ቤት አጥተን እየተንከራተትን [እንገኛለን]” ሲል የደረሰበትን ሁኔታ ጽፏል።​—1 ቆሮንቶስ 4:11

● ክርስቲያኑ አፍሮዲጡ ታሞና ‘ትካዜ’ ላይ ወድቆ ነበር።​—ፊልጵስዩስ 2:25, 26

አምላክ እነዚህን ሦስት ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት እየቀጣቸው እንደነበር የሚገልጽ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አምላክ አለመሆኑን በመግለጽ ብቻ አይወሰንም። ይልቁንም ብዙውን ጊዜ ለመከራ መንስኤ የሚሆኑ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ይገልጻል።

ሰዎች የሚያደርጉት ምርጫ

“አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” (ገላትያ 6:7) ሲጋራ የሚያጨስ፣ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ የሚያሽከረክር ወይም ገንዘቡን የሚያባክን ሰው ውሳኔው ለሚያስከትልበት ማንኛውም መከራ በተወሰ መጠንም ቢሆን ተጠያቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች በሚያደርጉት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ምርጫ የተነሳ ለመከራ ልንዳረግ እንችላለን። በእርግጥም የሰው ልጆች የናዚ አገዛዝ ከፈጸማቸው ዘግናኝ ድርጊቶች አንስቶ በልጆች ላይ ግፍ እስከመፈጸም ያሉ እጅግ ሰቅጣጭ የሆኑ የጭካኔ ተግባራትን ፈጽመዋል። አንዳንዶች ነፃ ምርጫ የማድረግ መብታቸውን አላግባብ ስለሚጠቀሙ በሌሎች ላይ መከራ ያመጣሉ።

ያልተጠበቁ ክስተቶች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም ውስጥ አንድ ትልቅ ግንብ በመደርመሱ ሳቢያ 18 ሰዎች ለሞት ተዳርገው ነበር። ኢየሱስ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር “በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች የነበሩ ይመስላችኋል? እላችኋለሁ፣ በፍጹም አይደለም” ብሏል። (ሉቃስ 13:4, 5) ኢየሱስ በሰዎቹ ላይ የደረሰው አደጋ ከአምላክ ዘንድ የመጣ ቅጣት አለመሆኑን ተገንዝቦ ነበር። እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ አስቀድሞ የተጻፈውን “ሁሉም [ሰዎች] መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል” የሚለውን ሐሳብ ያውቃል። (መክብብ 9:11 NW) ብዙ አሳዛኝ ሁኔታዎች የሚከሰቱት ሰዎች በአጉል ጊዜ አጉል ቦታ ላይ በመገኘታቸው ወይም በሚፈጽሙት ስህተት የተነሳ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሰዎች ማስጠንቀቂያዎችን ችላ በማለታቸው እንዲሁም ሕንፃዎች መጥፎ የአየር ንብረትን ወይም ርዕደ መሬትን መቋቋም እንዲችሉ ተደርገው ባለመገንባታቸው በሰው ልጆች ላይ በርካታ መከራዎች ደርሰዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ያልተጠበቁ ክስተቶች በብዙ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ መከራም ያስከትላሉ።

“የዚህ ዓለም ገዥ”

መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም ግን በክፉው ኃይል ሥር ነው” ይላል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) እዚህ ላይ “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን ይህ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር “የአየሩ ሥልጣን ገዥ” እንደሆነ ተገልጿል። ሰይጣን “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ [ያለውን] መንፈስ” ያስፋፋል። (ኤፌሶን 2:2) ዘር እንደማጥፋት እና በልጆች ላይ ግፍ እንደመፈጸም ያሉ አንዳንድ ወንጀሎች እጅግ አሠቃቂ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙዎች፣ የሰው ልጅ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጽማል ብሎ ማመን ይከብዳቸዋል።

ይሁንና አምላክ ለሚደርስብን መከራ ግድ አይሰጠውም ማለት ነው? መከራን ማስወገድ ይችላል? ደግሞስ እንዲህ ያደርግ ይሆን?