በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዛፍ ቅርፊት እስከ ጠርሙስ መክደኛነት​—የቡሽ ታሪክ

ከዛፍ ቅርፊት እስከ ጠርሙስ መክደኛነት​—የቡሽ ታሪክ

ከዛፍ ቅርፊት እስከ ጠርሙስ መክደኛነት​—የቡሽ ታሪክ

በሞተር፣ በክሪኬት መጫወቻ ኳስ፣ በቤዝቦል እና በሻምፓኝ አሠራር ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት የዛፍ ቅርፊት ይኖራል ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ይህን የዛፍ ቅርፊት ዓሣ አጥማጆችና የተዋቡ ወይዛዝርት በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጠቀሙበት ሲሆን ከጠፈር ጥናት ጋር በተያያዘም አገልግሎት ላይ ውሏል። ይበልጥ የሚያስደንቀው ደግሞ ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቅርፊት ይህን የመሰለ አገልግሎት የሚሰጠው ዛፉ ሳይቆረጥ መሆኑ ነው!

ቡሽ የሚገኘው ከቡሽ ዛፍ (ኮርክ ኦክ) ግንድ ውጨኛ ቅርፊት ነው። ይሁን እንጂ ይህ የተለመደው ዓይነት ቅርፊት አይደለም። ክብደቱ ቀላል ከመሆኑም ሌላ እሳት የማይደፍረውና የመለጠጥ ችሎታ ያለው ነው።

የቡሽ ዛፍ ለበርካታ ዓመታት ጠንካራ የሆነው ቅርፊቱን በብዛት ይሰጣል። ቅርፊቱ ካልተቀረፈ ውፍረቱ እስከ 25 ሴንቲ ሜትር ሊደርስ የሚችል ሲሆን ዛፉን ከሙቀት፣ ከቅዝቃዜና ከሰደድ እሳት የሚከላከል ሽፋን ሆኖ ያገለግላል። ሰዎች ቅርፊቱን ቀርፈው ከወሰዱ በኋላ ዛፉ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ቅርፊቱን ቀስ በቀስ መልሶ ይተካል።

በመላው ዓለም ከሚመረተው የቡሽ ምርት 55 በመቶ የሚሆነውን የምታመርተው ፖርቱጋል ስትሆን ስፔይን 30 በመቶ፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ (አልጀሪያን፣ ፈረንሳይን፣ ጣልያንን፣ ሞሮኮንና ቱኒዝያን ጨምሮ) የቀረውን 15 በመቶ ያመርታሉ። *

ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት

ሮማውያንና ግሪኮች ቡሽ ለዓሣ ማጥመጃ መረብ ማንሳፈፊያነትና ለጫማ ሶል በጣም አመቺ እንደሆነ ደርሰውበት ነበር። በተጨማሪም የማሰሮ መክደኛ አድርገው ተጠቅመውበታል። ቡሽ ከፍተኛ በሆነ ሙቀት እንኳን የመለጠጥና የመሳሳብ ችሎታውን ስለማያጣ የመኪና ሞተር ጋስኬት ይሠራበታል። በአንዳንድ የጠፈር መንኮራኩሮች ላይም ሙቀት አምቀው ማስቀረት የሚችሉ ክፍሎችን ለመሥራት ይውላል።

ቤት የሚሠሩ ብዙ ሰዎች የቡሽን መልክና ሙቀት አምቆ የማቆየት ችሎታ ስለሚወዱት የቤታቸው ግድግዳና ወለል በቡሽ ንጣፍ እንዲሸፈን ያደርጋሉ። የስፖርት ዕቃ አምራቾችም የቤዝቦል ኳስን ውስጠኛ ክፍልና የዓሣ ማጥመጃ መንጠቆ እጀታዎችን ለመሥራት ይጠቀሙበታል። ቡሽ ከሁሉ በላይ የሚታወቀው ለወይን ጠጅና ለሻምፓኝ ጠርሙስ መክደኛ በመሆን በሚሰጠው አገልግሎት ሳይሆን አይቀርም።—“እጅግ አስተማማኝ የሆነ መክደኛ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አካባቢ አይበክልም

በጥሩ ሁኔታ የተጠበቀ የቡሽ ዛፍ ደን፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ሳይጎዳ በተፈጥሮ ውጤቶች ሊጠቀም እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ የቡሽ ዛፎች ገጠራማ አካባቢዎችን ያስውባሉ እንዲሁም ከቅርንጫፎቻቸው ሥር ሆነው ሣር ለሚግጡ ከብቶች ጥላና ምግብ ያስገኛሉ፤ በተጨማሪም የበጋውን ትኩሳት በረድ ያደርጋሉ።

ኢምፔሪያል በመባል የሚታወቀው የንሥር ዝርያን፣ ጥቁር ጥንብ አንሳንና ጥቁር ራዛን ጨምሮ በርካታ ሊጠፉ የተቃረቡ የአእዋፍ ዝርያዎች ጎጆአቸውን ሠርተው የሚኖሩት በትላልቅ የቡሽ ዛፎች ላይ ነው። አይቤሪያ ሊኒክስ የተባለው ሊጠፋ የተቃረበ የድመት ዝርያ የሚገኘው በእነዚህ የቡሽ ዛፍ ደኖች ውስጥ ብቻ ነው። ወርልድ ዋይልድ ላይፍ ፈንድ የተባለው ድርጅት የዚህ የሊኒክስ ዝርያ ሕልውና የተመካው በስፔይንና በፖርቱጋል በሚገኘው የቡሽ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ላይ እንደሆነ በቅርቡ ገልጿል።

ስለዚህ የወይን ጠጅ ለመክፈት ቡሹን በምታወጣበት ጊዜ የዚህን ዛፍ ጠቀሜታ ቆም ብለህ አስብ። በእጅህ የያዝከው ቡሽ ከተፈጥሮ የተገኘ፣ በራሱ በስብሶ ወደ አፈር የሚመለስና በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ምርት ነው። እንዲያውም በዚህ ምርት መጠቀም ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ታዲያ ከአንድ ዛፍ ከዚህ የበለጠ ምን ጥቅም ማግኘት ትፈልጋለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 የቡሽ ዛፍ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚያድግ ቢሆንም ለንግድ የሚውለው ቡሽ በዋነኛነት የሚገኘው ዛፉ በተፈጥሮ ከሚበቅልበት በሜድትራንያን አካባቢ ካሉ አገሮች ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

“እጅግ አስተማማኝ የሆነ መክደኛ”

ተቀማጭነቱ በኤክስትሬማዱራ፣ ስፔይን የሆነው የቡሽ፣ የእንጨትና የከሰል ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ሚጋል ኤሌና ቡሽ በጠርሙስ መክደኛነት ስለሚሰጠው አገልግሎት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቡሽ በጠርሙስ መክደኛነቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ከአንድ መቶ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያለው የቡሽ መክደኛ ሲከፈት አይቻለሁ፤ የወይን ጠጁም ሳይበላሽ ቆይቷል! ቡሽ እጅግ አስተማማኝ የሆነ መክደኛ ነው።

ከቡሽ ዛፍ ላይ መክደኛ የሚሠራበት ቅርፊት ለመውሰድ ዛፉ ምን ያህል ዕድሜ ሊኖረው ይገባል?

የዛፉ ዘር ከተተከለ ከ25 ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን ምርት ማግኘት ቢቻልም ከፍተኛ ጥራት ያለው መክደኛ ለማግኘት የቡሽ ዛፉ ቢያንስ 50 ዓመት የሞላው መሆን አለበት። እርግጥ 50 ዓመት ቆይቶ ገንዘብ ለሚያስገኝ ተክል ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። እንዲያውም ትርፍ ለማስገኘት ይህን ያህል ዓመት መቆየት የሚኖርበት ሌላ ኢንዱስትሪ ይኖራል ብዬ አላስብም።

የቡሽ ዛፍ ምን ያህል ዕድሜ ይኖራል?

የቡሽ ዛፍ ዕድሜ እስከ 200 ዓመት ሊደርስ የሚችል ሲሆን አንዳንዶቹ ዛፎች ደግሞ ከዚያ በላይ ይኖራሉ። የቡሽ ምርት በየዘጠኝ ዓመቱ ይሰበሰባል።

የቡሽ ምርት ቀጣይ እንዲሆን ምን በመደረግ ላይ ነው?

የአውሮፓ ሕብረትና የአገራችን መንግሥት፣ ሰዎች የቡሽ ዛፍ እንዲተክሉ ለማበረታታት ድጎማ ይሰጣሉ። በመሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ነባር ለሆኑት የቡሽ ደኖች የተሻለ እንክብካቤ እያደረግን ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ ሄክታር የሚሸፍኑ አዳዲስ ዛፎችን ተክለናል።

ቡሽ ከማምረት ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት አዳዲስ እድገቶች ታይተዋል?

ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በጣም ጥሩ የሆኑትን ዘሮች ለመለየት ብዙ ምርምር አድርገናል። ምርቱንም ለማሻሻል ከሌሎች ቡሽ አምራች የሆኑ አገሮች ጋር ተቀራርበን በመሥራት ላይ እንገኛለን። የቡሽ ቅርፊት የሚሰበስቡ ሰዎች ለዘመናት ሲያደርጉ እንደቆዩት በመጥረቢያ መጠቀም ትተው በቀላሉ መቅረፍ የሚችሉበት ትንሽ የእጅ መጋዝ ሠርተንላቸዋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅርፊቱ ከተቀረፈ በኋላ እንደገና ማደግ ይጀምራል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ቅርፊቱን በጥንቃቄ ይልጣሉ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅርፊቶቹ ለቀጣዩ ሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ይደረደራሉ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜም ቢሆን፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡሽ የሚቆራረጠው በእጅ ነው

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቃቅን ቁርጥራጮችና ፍርፋሪዎች አንድ ላይ ተጣብቀው ቡሽና ሌሎች ነገሮች ይሠሩባቸዋል