በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለማይሊን አዲስ ፊት ተሠራላት

ለማይሊን አዲስ ፊት ተሠራላት

 ለማይሊን አዲስ ፊት ተሠራላት

የማይሊን እናት እንደተናገረችው

ተወዳጅዋ የ11 ዓመት ልጄ ማይሊን አዲስ ፊት ያስፈለጋት ለምን ነበር? ምን እንዳጋጠማት ልንገራችሁ።

ማይሊን ከሁለቱ ሴት ልጆቼ ትንሿ ናት። ነሐሴ 5, 1992 በኩባ በምትገኘው በኦልጊን ከተማ ስትወለድ እኔና አባቷ እንዲሁም ታላቅ እህቷ በጣም ተደስተን ነበር። ይሁን እንጂ ደስታችን ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ከተወለደች ከጥቂት ቀናት በኋላ ኩፍኝ ያዘኝ፤ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ በሽታው ወደ ማይሊን ተጋባ።

በመጀመሪያ ሁኔታዋ እምብዛም አሳሳቢ አይመስልም ነበር። እያደር ግን በሽታው እየባሰባት ስለሄደ ሆስፒታል መተኛት አስፈለጋት። ማይሊን ጥሩ የሕክምና ክትትል የተደረገላት ቢሆንም በሽታ የመከላከል ኃይሏ በጣም ተዳክሞ ስለነበር ኢንፌክሽን ሆነባት። ትንሹ አፍንጫዋ በአንድ ወገን ከወትሮው በተለየ መልኩ እንደቀላ ተመለከትኩ። ሐኪሞቹ ለዚህ መንስኤው እምብዛም የማያጋጥም ከፍተኛ የማጥቃት ኃይል ያለው የባክቴሪያ ዓይነት መሆኑን ገለጹልን።

ወዲያውኑ አንቲባዮቲክ መድኃኒት ቢሰጣትም በጥቂት ቀናት ውስጥ ባክቴሪያው ፊቷን ማበላሸት ጀመረ። ሐኪሞቹ ስርጭቱን እስኪያስቆሙት ድረስም ማይሊን አፍንጫዋንና ከናፍሯን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል እንዲሁም ከፊል ድዷንና አገጯን አጣች። በአንደኛው ዓይኗ በኩልም ቆዳዋ ሳስቶ ነበር።

ባለቤቴና እኔ ስናያት በጣም አለቀስን። ትንሿ ልጃችን እንዲህ ዓይነት ነገር እንዴት ሊደርስባት ቻለ? ማይሊን ለአያሌ ቀናት ልዩ የሕክምና ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ገብታ ስትታከም ቆይታ ስለነበር ሐኪሞቹ አትተርፍም ብለው አስበው ነበር። ባለቤቴም “እንግዲህ ለከፋው ነገር ተዘጋጂ” ይለኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሙቀት ወደምታገኝበት መሣሪያ እጄን አስገብቼ የማይሊንን ትንሽ እጅ ስነካ ጣቶቼን ጨምድዳ ያዘች። ሕይወቷ እንደሚተርፍ ስላወቅሁ ለባለቤቴ “ልጃችን አትሞትም ይሁን እንጂ እንዲህ ሆና ሕይወቷን እንዴት ልትገፋው ነው?” አልኩት። ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ይሄ ሁሉ አስፈሪ ቅዠት እንጂ እውን አይደለም ብለን እናስብ ነበር።

በሆስፒታል ሳለን በዚያን ጊዜ ስድስት ዓመት የሆናት ትልቋ ልጃችን ማይደሊስ ከወላጆቼ ጋር ነበረች። ትንሿ እህቷ ወደ ቤት እስክትመለስ በጉጉት ትጠባበቅ ነበር። ማይሊን ስትለያት ትልልቅ ሰማያዊ ዓይኖች ያሏት ውብ “አሻንጉሊት” ትመስል ነበር። ማይደሊስ ሕፃን እህቷ ማይሊን ከሆስፒታል ስትመለስ ባየቻት ጊዜ ግን የሚያስፈራ ገጽታ ነበራት።

ሕፃን ልጄ ይህን ያህል የምትሠቃየው ለምንድን ነው?’

ማይሊን በሆስፒታል አንድ ወር ተኩል ከቆየች በኋላ ወጣች። ማንም እንዲያያት ስላልፈለግን በከተማ ውስጥ ወዳለው ቤታችን አልተመለስንም። ከዚህ ይልቅ ገጠር ከወላጆቼ እርሻ አጠገብ ባለች ጎጆ ውስጥ ተገልለን መኖር ጀመርን።

መጀመሪያ ላይ ለማይሊን አፏ በነበረበት አካባቢ በሚገኝ ቀዳዳ በኩል የጡት ወተት ትንሽ ትንሽ እያደረግሁ ልሰጣት ችዬ ነበር። መጥባት አትችልም ነበር። ይሁን እንጂ ቁስሉ መዳን ሲጀምር ያ ቀዳዳም ሊዘጋ ተቃረበ። ልሰጣት የምችለው ነገር ፈሳሽ የሆነ ምግብ በጡጦ አድርጌ ነበር። ዕድሜዋ አንድ ዓመት ሲሞላ ወደ ኦልጊን ተመለስንና ሐኪሞቹ የአፏን ቀዳዳ ለማስፋት አራት ቀዶ ሕክምናዎች አደረጉላት።

‘ሕፃን ልጄ ይህን ያህል የምትሠቃየው ለምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። መልሱን ለማግኘት ወደ ጠንቋይ ቤት እሄድ የነበረ ሲሆን ወደ ሃይማኖታዊ  ምስሎቼም እጸልይ ነበር። ይሁን እንጂ የትኛውም ነገር ሊያጽናናኝ አልቻለም። አንዳንዶቹ ዘመዶቼና ጓደኞቼ የሚሰነዝሯቸው ደግነት የጎደላቸው አስተያየቶች ይበልጡን ግራ አጋቡኝ። አንዳንዶቹ “አምላክ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ለምን እንደሚፈቅድ የሚያውቀው ራሱ ነው” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “ይህ ከአምላክ የመጣ ቅጣት እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም” አሉኝ። እኔም ማይሊን ስታድግ ምን ብዬ እንደምነግራት በጣም እጨነቅ ነበር። አንድ ጊዜ ገና ትንሽ ልጅ ሳለች አባቷን “እኔ እንደ ሌላ ሰው አፍንጫ የሌለኝ ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው። አባቷም መልስ ሊሰጣት ስላልቻለ ወደ ውጭ ወጥቶ አለቀሰ። እኔ የሆነውን ነገር ላስረዳት ሞከርኩ። አንድ ትንሽ ትል አፏንና አፍንጫዋን እንደበላባት እነግራት እንደነበረ አሁንም ድረስ ታስታውሳለች።

ለተስፋ መሠረት የሚሆን ነገር

በጣም በተበሳጨሁበት ወቅት ጎረቤቴ የይሖዋ ምሥክር መሆኗን አስታወስኩ። አምላክ ትንሿ ልጄ ይህን ያህል እንድትሠቃይ የፈቀደበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንድታሳየኝ ጠየቅኳት። በተጨማሪም “ይህ ሕመም በእርግጥ እኔ ለሠራሁት ጥፋት ከአምላክ የመጣ ቅጣት ከሆነ ማይሊን የምትቀጣበት ምክንያት ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁ።

ጎረቤቴም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ * በሚለው መጽሐፍ ተጠቅማ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ጀመር። ቀስ በቀስም በማይሊን ላይ ለደረሰው ነገር ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነና እንዲያውም እሱ በእርግጥ እንደሚያስብልን መረዳት ጀመርኩ። (ያዕቆብ 1:13፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥቱ ግዛት ዘመን ሥቃይ ሁሉ እንደሚጠፋ የሚገልጸውን ግሩም ተስፋ ማድነቅ ጀመርኩ። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ እውቀት አጠነከረኝና የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ ገፋፋኝ። መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ አዲሱን መንፈሳዊ ፍላጎቴን አልወደደውም ነበር። ቢሆንም የደረሰብንን አሳዛኝ መከራ እንድቋቋም የሚረዳኝ እስከሆነ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን እንዳቆም አላስገደደኝም።

ከውጭ አገር የተገኘ እርዳታ

ማይሊን ሁለት ዓመት ሲሆናት በሜክሲኮ ያለ አንድ እውቅ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዶክተር ስለ ልጃችን ችግር ሰምቶ በነፃ ሊያክምልን ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸ። የመጀመሪያዎቹ ቀዶ ሕክምናዎች የተደረጉት በ1994 ነበር። እኔና ማይሊን አንድ ዓመት ለሚያህል ጊዜ በሜክሲኮ ቆየን። መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ስላላገኘን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አልቻልንም ነበር። ይህም መንፈሳዊነቴን አዳከመው። ከዚያም በአካባቢው ካሉ ምሥክሮች ከአንዷ ጋር ተገናኘንና እንደገና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በተቻለን መጠን አዘውትረን  መሰብሰብ ጀመርን። ወደ ኩባ ስመለስ ጥናቴን ቀጠልኩና በመንፈሳዊ አገገምኩ።

በዚህ ጊዜ ላይ ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ምንም ፍላጎት አልነበረውም። ፍላጎቱን ለማነሳሳት ስል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንድችል እንዲያነብልኝ እጠይቀው ጀመር። በመጨረሻም ወደ ሜክሲኮ የማደርገው ተደጋጋሚ ጉዞ የቤተሰባችንን ግንኙነት ሊያዳክመው ይችላል ብሎ ስለፈራ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ። በመንፈሳዊ አንድ መሆናችን ተለያይተን የምንቆይባቸውን ወቅቶች በተሻለ መንገድ ለመቋቋም እንደሚረዳን ተሰማው። በእርግጥም ደግሞ ረድቶናል። በ1997 ባለቤቴ፣ ትልቋ ልጄና እኔ ራሳችንን ወስነን በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

በሜክሲኮ በቆየንባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ማይሊን ትንሹ ትል ፊቷን ባይበላው ኖሮ ከአባቷና ከእህቷ ተለይተን መኖር እንደማያስፈልገን ትናገር ነበር። ይህን ለሚያህል ረዥም ጊዜ ቤተሰባችን መለያየቱ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ሜክሲኮ ሳለን ቤቴል ተብሎ የሚጠራውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መጎብኘታችን ምን ያህል እንዳበረታታን አይረሳኝም። ያገኘነውን የመንፈስ ብርታት አስታውሰዋለሁ። በቀዶ ሕክምናው ምክንያት የሚፈጠረው ቁስል በጣም የሚያሠቃይ ስለሆነ ማይሊን በዚህኛው ጉዟችን ወቅት ለአምስተኛ ጊዜ የሚደረግላትን ቀዶ ሕክምና አልፈልግም እያለች ስታስቸግረኝ ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሠሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ደፋር ሆና ሐኪሞቹ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉላት ብትስማማ ከሆስፒታል ስትወጣ ግብዣ እንደሚያዘጋጁላት ነገሯት። ስለዚህ ቀዶ ሕክምናው እንዲደረግላት ተስማማች።

ምን እንደተሰማት ማይሊን ራሷ ትንገራችሁ:- “በቤቴል ግብዣ እንደሚዘጋጅልኝ የቀረበልኝ ሐሳብ በጣም አስደሰተኝ። ስለዚህ በቀዶ ሕክምናው ወቅት አልፈራሁም። ብዙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች የተገኙበት ይህ ግብዣ በጣም የሚያስደስት ነበር። ብዙ ካርዶች የሰጡኝ ሲሆን እስካሁን ድረስ አስቀምጫቸዋለሁ። ያን ጊዜ ያገኘሁት ማበረታቻ ከዚያ በኋላ የተደረጉልኝ ቀዶ ሕክምናዎች ያስከተሉብኝን ሥቃይ መቋቋም እንድችል ጥንካሬ ሰጥቶኛል።”

እድገት ማድረግና ለመጽናት የሚያስችል እርዳታ ማግኘት

አሁን ማይሊን ዕድሜዋ 11 ዓመት ሲሆን ፊቷን እንደ አዲስ ለመሥራት 20 ቀዶ ሕክምናዎች አድርጋለች። ቀዶ ሕክምናዎቹ ብዙ የረዷት ቢሆንም አሁንም ቢሆን አፏን ሙሉ በሙሉ መክፈት አትችልም። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ደፋርና አዎንታዊ አመለካከት ያላት ልጅ ናት። መንፈሳዊ ነገሮችንም በጣም ታደንቃለች። ስድስት ዓመት ከሆናት ጀምሮ በጉባኤያችን በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግባ ክፍል ስትወስድ የቆየች ሲሆን ሚያዝያ 27, 2003 ተጠመቀች። ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የመራችበት ጊዜ አለ። በአንድ ወቅት ሜክሲኮ ሳለን አንድ ሰው አነጋገረችና ከእሷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። ማይሊን በክርስቶስ ሞት መታሰቢያና በሌሎችም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ጋበዘችው፤ በስብሰባዎቹ ላይ በመገኘቱ ተደስቷል።

ማይሊን ከቤት ወደ ቤት ስትሰብክ አንዳንድ ሰዎች ፊቷን ያዩና እንዲህ የሆነችው ተቃጥላ እንደሆነ ይጠይቃሉ። ማይሊንም አጋጣሚውን በመጠቀም ይሖዋ በመጪዋ ገነት አዲስ ፊት እንደሚሰጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋዋን ታካፍላቸዋለች።—ሉቃስ 23:43

ማይሊን በቀዶ ሕክምናው ምክንያት እንዲሁም ልጆች ስለሚያፌዙባት የደረሰባት ሥቃይ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ታዲያ ለመጽናት የረዳት ምንድን ነው? ማይሊን በሙሉ እምነት እንደሚከተለው በማለት መልስ ትሰጣለች:- “ይሖዋ ለእኔ በጣም እውን ነው። እንድጸና የሚያስችለኝን ጥንካሬና ብርታት እሱ ይሰጠኛል። ከአሁን ወዲያ ሐኪሞቹ ብዙም የሚረዱኝ ነገር ስለሌለ ተጨማሪ ቀዶ ሕክምና እንዲደረግልኝ አልፈልግም። ሐኪሞቹ ስወለድ የነበረኝን መልክ ሊመልሱልኝ ፈጽሞ አይችሉም። ይሖዋ ግን በአዲሱ ዓለም እንደገና የማምር እንድሆን አዲስ ፊት እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ይሖዋ በአዲሱ ዓለም አዲስ ፊት ይሰጠኛል’

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ቀስ በቀስም ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ መረዳት ጀመርኩ