በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኦሎምፒክ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ

ኦሎምፒክ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ

ኦሎምፒክ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ

የኦሎምፒክ ውድድር ዳግም ልደት እንዲያገኝ ያስቻለው የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች አካፋና ዶማ ይዘው ያደረጉት ጥናት ነበር። ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደ ኩበርታ በግሪክ አገር በምትገኘው በጥንታዊቷ ኦሎምፒያ በተገኙት የመሬት ቁፋሮ ግኝቶች ተነሳስቶ ውድድሮቹ በዘመናችንም እንዲካሄዱ ጥረት አደረገ። በዚህም ምክንያት የመጀመሪያው የዘመናችን የኦሎምፒክ ውድድር በ1896 በአቴንስ ከተማ ተካሄደ።

አሁን ደግሞ ከ2004 በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታት ትላልቅ ዶዘሮችና ግሬደሮች ኦሎምፒክ ወደ ትውልድ አገሩ የሚመለስበትን መንገድ መጥረግ ጀመሩ። የግሪክ ዋና ከተማ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የምታደርገው ዝግጅት መላዋን ከተማ የግንባታ ቀጣና አስመስሏታል።

የ2004ቱ ሃያ ስምንተኛ ኦሎምፒያድ ሊደረግ የታቀደው ከነሐሴ 13 እስከ 29 በአቴንስ ነው። ከ201 አገሮች የተውጣጡ 10,000 አትሌቶች በ28 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ። ውድድሮቹ የሚካሄዱት በ38 ቦታዎች ሲሆን ከውድድሮቹ በኋላም ከ300 በላይ የሜዳልያ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ። 21,500 ከሚያክሉ የመገናኛ ብዙኃን አባላት በተጨማሪ በትጋት የሚሠሩ 55,000 የሚያክሉ የፀጥታ ጥበቃ ሠራተኞች ይኖራሉ።

የመሰናክል ሩጫ

አቴንስ ኦሎምፒክን ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ከጀመረች ቆይታለች። የዘመናችን ኦሎምፒክ መቶኛ ዓመት የተከበረው በ1996 ስለነበረ ኦሎምፒክን ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ ከዚህ የተሻለ ዓመት አይኖርም ተብሎ ታስቦ ነበር።

ይሁን እንጂ አቴንስ የ1996ቱን ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አጣ። ከተማይቱ ጨዋታው በሚደረግባቸው ሁለት ሳምንታት የሚኖረውን ሽር ጉድ ለማስተናገድ የሚያስችል መዋቅር የላትም ተባለ።

ግሪክና ዋና ከተማዋ አቴንስ ወገባቸውን ታጥቀው ለሥራ እንዲነሳሱ ያደረጋቸው ይህ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱ ነበር። አቴንስ ሁኔታውን አስተካክላለሁ ብላ ተገዘተች። ከተማይቱ ይህን በጎ ተነሳሽነትና ተጨባጭ የሆኑ ጥቂት ዕቅዶች ይዛ ታጥቃ በመነሳት በ1997 የ2004ን ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረበች። በዚህ ጊዜ ጥያቄዋ ተቀባይነት አገኘ።

አቴንስ ሥር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ታጥቃ ተነሳች። ውድድሮቹን ለማስተናገድ የነበረው ፍላጎት ከዚህ በፊት ታይቶ ለማያውቅ እንቅስቃሴና ልማት መጀመር ምክንያት ሆነ። በያለበት መንገዶችንና የውድድር ሥፍራዎችን ለመገንባትና ያሉትንም ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጧጧፈ። ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርባቸው የበጋ ቅዳሜና እሁድ ቀናት ሳይቀር ላባቸውን እያንጠፈጠፉ የሚሠሩ ሠራተኞችና የግንባታ መሣሪያዎች ማየት የተለመደ ነገር ሆነ።

በመጋቢት 2001 የመጀመሪያው አውሮፕላን በዓለም የአንደኛነት ደረጃ ከያዙት የአውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ ለመሆን በበቃው በአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ አረፈ። በተጨማሪም፣ በድምሩ 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው አዳዲስ መንገዶች ሲሠሩ 90 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላላቸው ሌሎች ነባር መንገዶች ደግሞ ደረጃቸውን ከፍ የማድረግ ሥራ ተካሂዷል። በአዳዲሶቹ መንገዶች ላይ የመኪና ጭንቅንቅ እንዳይፈጠር የመኪና እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ የሚረዱ 40 የሚያክሉ የመሬት በላይ ድልድዮች ተሠርተዋል። አዳዲስ የመሬት ውስጥ የባቡር መስመሮች የተዘረጉ ከመሆኑም ሌላ ለከተማ ባቡር የሚሆን ተጨማሪ 24 ኪሎ ሜትር መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል። በከተማው ዙሪያ ወደሚገኙ የመኖሪያ መንደሮች በሚያደርስ 32 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የባቡር ሐዲድ መስመርና በየቦታው በተዘጋጁ ዘመናዊ ባቡር ጣቢያዎች አማካኝነት የትራፊኩን ጭንቅንቅና የአየሩን ብክለት ለመቀነስ ታስቧል።

በአጭሩ አቴንስ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ራሷን ለውጣ አዲስ ከተማ ለመሆን ጥረት አድርጋለች። አዳዲስ የመናፈሻ ቦታዎች፣ ንጽሕናቸው የተጠበቀ አካባቢዎችና አዳዲስ የመጓጓዣ አውታሮች ተገንብተዋል። የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዣክ ሮኸ “ከውድድሩ በፊት አቴንስን ያውቁ የነበሩ ሰዎች ከውድድሩ በኋላ ቢመለከቷት አያውቋትም” ብለዋል።

እልህ አስጨራሽ ዝግጅቶች

የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቀን እየቀረበ ሲመጣ የሥራው ጥድፊያም እየጨመረ መጥቷል። የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዣክ ሮኸ የግንባታውንና የዝግጅቱን ሂደት የግሪክ ባሕላዊ ጭፈራ ከሆነው ከሰርታኪ ጋር አመሳስለውታል። ቀልድ በታከለበት አነጋገር “እንደ ሰርታኪ ካለው ሙዚቃ ጋር ይመሳሰላል። ሙዚቃው በጣም ቀስ ብሎ ይጀምርና አለማቋረጥ ፍጥነቱን እየጨመረ ሄዶ መጨረሻ ላይ ምቱ ለመከታተል አዳጋች የሚሆንበት ደረጃ ላይ ይደርሳል” ብለዋል።

እውነትም እርሳቸው እንዳሉት “የመላው ኦሎምፒክ ዝግጅት እምብርት” የሆነው የኦሎምፒክ መንደር ምንም ነገር ባልነበረበት የአቴንስ ሰሜናዊ ገጠር አካባቢ ጎላ ብሎ ይታያል። በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወቅት 16,000 ለሚያክሉ አትሌቶችና የቡድን ኃላፊዎች መኖሪያ ይሆናል ተብሎ የታሰበው ይህ ፕሮጀክት በግሪክ አገር ከተደረጉት የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ሁሉ በጣም ትልቁ ፕሮጀክት ነው። ውድድሩ ካለቀ በኋላ 10,000 ለሚያክሉ የከተማው ሰዎች መኖሪያ ይሆናል።

የውድድሩ አዘጋጆች በጥንታዊው ታሪክና በዘመናዊው ውድድር መካከል ያለውን የታሪክ ትስስርም አልዘነጉም። አንዳንድ ሥነ ሥርዓቶች የሚካሄዱት በጥንቷ ኦሎምፒያ ይሆናል። ውድድሮቹ በሚከናወኑባቸው ቀናት የሚቀርቡ ባሕላዊ ትርዒቶችም በሌሎች ታላላቅ አርኪዎሎጂያዊ ሥፍራዎች እንዲካሄዱ ይደረጋል። ዝነኛው የማራቶን ጦርነት በተደረገበት ቦታ አጠገብ የጀልባ ቀዘፋ ውድድር የሚደረግበት አዲስ ማዕከል ተሠርቷል። የማራቶን ሯጮችም የመጀመሪያው የማራቶን ሩጫ በተደረገበት መሬት ላይ ሮጠናል ለማለት ይችላሉ። የውድድሩ አዘጋጆች ለመወዳደሪያነት ያዘጋጁት አቴናዊው ወታደር ፋርሳውያን ድል መነሳታቸውን ለማብሰር በ490 ከክርስቶስ ልደት በፊት የሮጠበትን የ42 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው።

የዝግጅቶቹ ሁሉ ቁንጮ

የውድድሩን መከፈት የሚያበስሩት ርችቶች ሲተኮሱ የሰው ሁሉ ዓይን የሚያርፈው 75,000 ሰዎችን በሚይዘው በኦሎምፒክ ስታድየም ላይ ይሆናል። ብዙዎች የአቴንስ ኦሎምፒክ ዝግጅቶች ሁሉ ቁንጮ ይህ በአዲስ መልክ የተሠራው ስታድየም ነው ብለው ያስባሉ። ይህን ስታድየም ልዩ የሚያደርገው በዝነኛው የስፓኝ አርክቴክት በሳንትያጎ ካላትራቫ የተነደፈው ጣሪያው ነው።

ጣሪያው በጣም የሚያስደንቅ የምሕንድስና ጥበብ የታየበት ሲሆን የተሠራው ጠቅላላ ክብደቱ 16,000 ቶን ከሚመዝን መስታወት ነው። አሥር ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ይሸፍናል ተብሎ ይታሰባል። ጣሪያው የሚያርፈው እያንዳንዳቸው የ304 ሜትር ርዝመት ባላቸው ሁለት ግዙፍ ቅስቶች ላይ ሲሆን 80 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል። የአውስትራሊያውን የሲድኒ ሐርበር ድልድይ ሁለት ሦስተኛ መጠን ይኖረዋል ማለት ነው። ቅስቶቹ የተሠሩባቸው የብረት ቱቦዎች ከ9,000 እስከ 10,000 ቶን የሚመዝን ክብደት ሲኖራቸው “በውስጣቸው አውቶቡስ ማሳለፍ ይችላሉ” ሲሉ አንድ የግንባታ ባለሞያ ተናግረዋል። የጣሪያው ጠቅላላ ክብደት በፓሪስ የሚገኘውን የአይፍል ታወርን ሁለት እጥፍ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ይህን የሚያክል ግዙፍ ጣሪያ ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚያነድደው የአቴንስ የነሐሴ ፀሐይ ምን ያህል እንደሚሞቅ አስብ! በጣሪያው ላይ የተገጠሙት መስታወቶች 60 በመቶ የሚሆነውን የፀሐይ ጨረር አንጸባርቆ የመመለስ ችሎታ ያለው ልዩ ሽፋን ተደርጎላቸዋል። ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። የጣሪያው አሠራር ለውድድሩ ልዩ ማስታወሻ እንዲሆንም ታስቧል። የቀድሞው የግሪክ የባሕል ሚኒስቴር ኢቫንጀሎስ ቬናይዜሎስ እንዳሉት “ትልቁ ዓይን የሚስብ ሕንጻ ሲሆን ለአቴንስ ኦሎምፒክ አርማ ይሆናል።”

ለውድድሩ ዝግጅት የተከናወነው ከፍተኛ የግንባታ ሥራ የውድድሩ የፍጻሜ ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ እንዲህ ያለውን ታላቅ ውድድር ለማዘጋጀት ለተደረገው ድካምና ልፋት ማስታወሻ ይሆናል። አቴናውያን ለኦሎምፒክ ተብለው የተዘጋጁት ግንባታዎች በሙሉ በከተማው ያለው የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል የሚያደርጉ እንደሚሆኑ ተስፋ ያደርጋሉ። እንደማንኛውም ጊዜ ሁሉ፣ የኑሮ ውጣ ውረዶችን በሰርታኪ ጭፈራ ላይ እንደሚያደርጉት በእርጋታና በትዕግሥት መጋፈጥ ይቀጥላሉ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ፈተና ላይ የወደቁ የኦሎምፒክ ዓላማዎች

የኦሎምፒክ አዘጋጆች ውድድሮቹ የተመሠረቱባቸው “ጨዋነት የሚንጸባረቅበት የፉክክር፣ የስፖርት፣ የሰላም፣ የባሕልና የትምህርት” ዓላማዎች ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ፖለቲካ፣ ብሔራዊ ስሜት፣ ንግድና ሙስና ሌላው የኦሎምፒክ ውድድር ገጽታዎች ናቸው።

ከዚህ በፊት እንደታየው ኦሎምፒክ ከፍተኛ የቴሌቪዥን ታዳሚዎችና ብዙ ገንዘብ የሚታፈስበት የማስታወቂያ ውሎች የሚያስገኝ በመሆኑ ውድድሮቹን በቴሌቪዥን ለማሰራጨት የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ከፍተኛ የማሻሻጫ ሥራ ሆኗል። ሙሬ ፊሊፕስ የተባሉት አውስትራሊያዊ ተመራማሪ “ባሁኑ ጊዜ ኦሎምፒክ ትልቅ ንግድ ሆኗል። ብዙዎቹ ውሳኔዎች የሚደረጉትም ለንግድ እንዲያመቹ ተብለው ነው” ብለዋል።

ሌሎችን በጣም የሚያሳዝናቸው ደግሞ በውድድሮቹ ላይ የሚታየው ቅጥ ያጣ ብሔራዊ ስሜት ነው። የኦሎምፒክ ውድድር በሚካሄድበት ሰሞን እርቅ እንዲሰፍን፣ ጥላቻና ጦርነት እንዲቆም ጥረት ይደረጋል። ይሁን እንጂ ለግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ካልተወገዱ እንዲህ ያለው ጥረት የይስሙላ ከመሆን በስተቀር የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም። ብራያን ማርትን የተባሉት የሳይንስ ፕሮፌሰር “ውድድሮቹ የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት ፉክክር የሚካሄድባቸው መድረኮች ሆነዋል” ብለዋል። በማከልም “በኦሎምፒክ ላይ በአትሌቶች መካከል የሚደረገው ውድድር መልኩን ለውጦ በአገሮች መካከል የሚደረግ ውድድር ተደርጎ ይታያል። አትሌቶች አገሮቻቸው ተካፋዮች ካልሆኑ እነርሱም በውድድሮቹ ተካፋይ አይሆኑም። ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያገኙት ድል በባንዲራዎችና በብሔራዊ መዝሙሮች ታጅቦ የአገር ድል ተደርጎ ይቆጠራል . . . [ኦሎምፒክ] ተወዳዳሪዎች የጠብ አምሮታቸውን፣ አገሮች ደግሞ የሥልጣንና የክብር ደረጃቸውን የማስጠበቅ ትግላቸውን የሚወጡበት መድረክ ሆኗል። . . . የኦሎምፒክ እንቅስቃሴ ሰላም የሚመጣበትን ሁኔታ የማመቻቸት ቀዳሚ ዓላማውን እውን የሚያደርግበት አቅም የለውም።”

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአቴንስ ኦሎምፒክ የስፖርት መወዳደሪያ ሕንጻ

የ2004 ሜዳልያ ዲዛይን

[ምንጮች]

Aerial photo: AP Photo/Thanassis Stavrakis; medal design: © ATHOC

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአቴንስ የመሬት ውስጥ ባቡር

አቴንስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ

[ምንጭ]

© ATHOC

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በመገንባት ላይ ያለ የኦሎምፒክ መንደር

አጊዮስ ኮስማስ ጀልባ ቀዘፋ ማዕከል

[ምንጭ]

© ATHOC/Photo: K. Vergas

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኦሎምፒክ ስታድየም ጣሪያ በግንባታ ላይ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያለቀው ጣሪያ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሞዴል

[ምንጭ]

© ATHOC

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© ATHOC