በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የከተማው አስተዳደር አምባገነን መሆን የለበትም’

‘የከተማው አስተዳደር አምባገነን መሆን የለበትም’

 ‘የከተማው አስተዳደር አምባገነን መሆን የለበትም’

ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የካናዳ የዜጎች መብትና ነፃነት ቻርተር የሁሉንም ካናዳውያን መብት ያስከብራል። የመናገር፣ የመጻፍና የአምልኮ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉና የሕግ ከለላ የሚደረግላቸው መብቶች ናቸው።

በመሆኑም ከሞንትሪያል በስተ ሰሜን ምሥራቅ የሚገኘው የብሌይንቪል ከተማ አስተዳደር በከተማው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ማሻሻያ አድርጎ አለፈቃድ ‘ለሃይማኖታዊ ዓላማ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሰዎችን ማነጋገርን’ የሚከለክል ሕግ ሲያወጣ የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታውን ዝም ብለው ማየት አልቻሉም። ይህ ሕግ ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉትን አገልግሎት በቀጥታ ይቃወማል። (የሐዋርያት ሥራ 20:20, 21) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሕግ ማውጣት ለምን አስፈለገ? የከተማው ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሰዎችን ማነጋገራቸውን የሚቃወሙ በርካታ አቤቱታዎች ስለደረሷቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የፖሊስ ቢሮ መዛግብት እንደሚያሳዩት ባለፉት አምስት ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በሚመለከት አንድም አቤቱታ አልቀረበም!

ቢሆንም ማሻሻያው በ1996 ሕግ ሆኖ ወጣ። በብሌይንቪል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ነገረ ፈጆች፣ ሃይማኖታዊ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ መብት በመሆኑ የከተማው አስተዳደር በዚህ ሕግ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ የሚያግድ ከሆነ ድርጊቱ ሕገ ወጥ እንደሚሆንበት ለአስተዳደሩ አስታወቁ። የከተማው ባለ ሥልጣናት ይህን አቤቱታ ከቁብ ሳይቆጥሩ 17 የሚያክሉ የክስ መጥሪያዎች ላኩ። የምሥክሮቹ ነገረ ፈጆች የብሌይንቪል አስተዳደር የሁሉም ካናዳውያን መብት የሆነውን የአምልኮና የመናገር ነፃነት እንዳያግድ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት አቀረቡ።

ጉዳዩ በኩቤክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 3 እና 4, 2000 ለክቡር ዳኛ ዣን ክሬፖ ቀረበ። ዳኛው ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመሩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፍ ብይን ሰጡ። ዳኛ ክሬፖ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “አቤት ባዮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ የሥነ ምግባርና የመንፈሳዊነት አቋም እንዲኖራቸው ሲያበረታቱ የመጀመሪያውን ክርስቲያን ጉባኤ ፈለግ መከተላቸው ነው። . . . ሰዎችን ቤታቸው ሄዶ ማነጋገር ለኅብረተሰቡ ክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚሰጥበት አንዱ መንገድ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የብሌይንቪል ነዋሪዎችን በአማካይ በየአራት ወሩ አንድ ጊዜ እየሄዱ ጠቃሚና  የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ግብዣ ያቀርቡላቸዋል።” ዳኛ ክሬፖ በብይናቸው ላይ “[ፍርድ ቤቱ] የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማከናወን ፈቃድ የማውጣት ግዳጅ እንደሌለባቸው በግልጽ ያሳውቃል” ብለዋል።

የብሌይንቪል አስተዳደር የዳኛ ክሬፖን ውሳኔ በመቃወም ለኩቤክ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረበ። የይግባኝ አቤቱታው ሰኔ 17, 2003 ከተደመጠ በኋላ ነሐሴ 27, 2003 የተሰጠው ውሳኔ የመጀመሪያው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን አጽድቋል። ፍርድ ቤቱ ከሃይማኖታዊ ነፃነት በተጨማሪ በማስተማርና መረጃዎችን በማሰራጨት ሃይማኖታዊ እምነቶችን የመግለጽ መብት የሚያስከብረውን የካናዳ የዜጎች መብትና ነፃነት ቻርተር ጠቅሶ የሚከተለውን መግለጫ አወጣ:- “አቤቱታ የቀረበበት ሕግ የይሖዋ ምሥክሮችን የሃይማኖት ነፃነት እንዲሁም የብሌይንቪል ነዋሪዎችን የሐሳብ፣ የእምነት፣ የመምረጥና የመናገር ነፃነት በእጅጉ ይገድባል። . . . ማስረጃው እንደሚያመለክተው የብሌይንቪል ነዋሪዎች ሰላም ነስተውናል የሚል ቅሬታ ያሰሙት በሸቀጣ ሸቀጥ አዟሪዎችና ቸርቻሪዎች ላይ እንጂ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አይደለም። ለሃይማኖታዊ ዓላማ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሰዎችን ማነጋገርን የሚቆጣጠር ደንብ ማውጣት የሚያስፈልግበት አንዳች ምክንያት የለም። በተጨማሪም ተሻሽሎ የወጣው ሕግ በቂ ውይይት ሳይደረግበት በችኮላና በግድየለሽነት የተረቀቀ ከመሆኑም በላይ ዓላማው የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ ለማስጠበቅ እንደሆነ ቢገለጽም ያልታሰበበት ከባድ መዘዝ የሚያስከትል ነው። . . . ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ አንድ የከተማ አስተዳደር የከተማው ነዋሪዎች በምሽቶች ወይም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት እነማንን ቤታቸው መቀበል እንደሚገባቸውና እንደማይገባቸው በመወሰን የአምባገነንነት ባሕርይ ማሳየት የለበትም። የመጀመሪያው ፍርድ ቤት አቤቱታ የቀረበበት ደንብ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ምንም ዓይነት ኃይልና ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም ብሎ መወሰኑ ትክክል ነው።”

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የኩቤክ ፍርድ ቤቶች የዜጎች መብት ቻርተርን ተንተርሰው የኩቤክ ነዋሪዎችን ሃይማኖታዊ ነፃነት ከጭፍን ጭቆና በመጠበቃቸው በጣም ተደስተዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ካናዳ

ብሌይንቪል

ሞንትሪያል

ዩናይትድ ስቴትስ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካናዳ የዜጎች መብትና ነፃነት ቻርተር የሁሉንም ካናዳውያን ነፃነት ያስከብራል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በብሌይንቪል በነፃነት ማገልገል ችለዋል። ተደራቢው ፎቶ:- በመንግሥት አዳራሻቸው ለአምልኮ ይሰበሰባሉ