የሕይወት ታሪክ
በመላው ሕይወታችን ከታላቁ አስተማሪያችን ያገኘናቸው ትምህርቶች
በታጠቁ ወታደሮች የሚጠበቁ ኬላዎች፣ በሚቃጠል ጎማ የተዘጉ መንገዶች፣ አውሎ ነፋሶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲሁም ሽሽት። እነዚህ እኔና ባለቤቴ በአቅኚነትና በሚስዮናዊነት አገልግሎታችን ካጋጠሙን ፈተናዎች አንዳንዶቹ ናቸው። ያም ቢሆን፣ ሌላ ዕድል ቢሰጠን እንኳ ሕይወታችንን መምራት የምንፈልገው በዚሁ መንገድ ነው። ባጋጠመን ውጣ ውረድ ሁሉ የይሖዋ ድጋፍና በረከት አልተለየንም። ታላቅ አስተማሪያችን እንደመሆኑ መጠን ጠቃሚ ትምህርቶችንም አስተምሮናል።—ኢዮብ 36:22፤ ኢሳ. 30:20
ወላጆቼ የተዉልኝ ምሳሌ
በ1950ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ወላጆቼ ከጣሊያን ወደ ካናዳ ተጉዘው ሳስካችዋን ውስጥ በምትገኘው በኪንደርስሊ መኖር ጀመሩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እውነትን ሰሙ። ከዚያ በኋላ ሕይወታችን በእውነት ዙሪያ ያጠነጠነ ሆነ። ትዝ ይለኛል፣ ልጅ እያለሁ ከቤተሰቤ ጋር ሙሉ ቀን የምናገለግልባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲያውም “ረዳት አቅኚ” ሆኜ ማገልገል የጀመርኩት በ8 ዓመቴ ነው እያልኩ እቀልዳለሁ።
ከቤተሰቤ ጋር፣ በ1966 ገደማ
ወላጆቼ ድሆች ቢሆኑም ለይሖዋ መሥዋዕት በመክፈል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልኛል። ለምሳሌ በ1963 በፓሰዲና፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ አብዛኛውን ንብረታቸውን ሸጠው ነበር። በ1972 በጣሊያንኛ መስክ ለማገልገል ስንል 1,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘን ካናዳ ውስጥ በብሪትሽ ኮሎምቢያ ወደሚገኘው ወደ ትሬይል ተዛወርን። አባቴ የሚሠራው በጽዳት ሠራተኛነት ነበር። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማተኮር ሲል የሥራ እድገት ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም።
ወላጆቼ ለእኔ፣ ለወንድሜና ለሁለት እህቶቼ ለተዉልን ግሩም ምሳሌ አመስጋኝ ነኝ። በሕይወቴ ያገኘሁት ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና የጀመረው በዚህ መንገድ ነው፤ በመላው ሕይወቴ የማልረሳው ትምህርት አግኝቻለሁ፦ መንግሥቱን ካስቀደምኩ ይሖዋ ይንከባከበኛል።—ማቴ. 6:33
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ
በ1980 ግልጽ የሆኑ መንፈሳዊ ግቦች ካሏት ዴቢ የተባለች ውብ እህት ጋር ትዳር መሠረትኩ። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት እንፈልግ ስለነበር ዴቢ ከተጋባን ከሦስት ወር በኋላ አቅኚ ሆነች። በትዳር ዓለም አንድ ዓመት ከቆየን በኋላ እገዛ ወደሚያስፈልግበት ትንሽ ጉባኤ ተዛወርን። እዚያ ሳለን እኔም በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ።
በሠርጋችን ቀን፣ 1980
ከጊዜ በኋላ ተስፋ ስለቆረጥን ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ወሰንን። በመጀመሪያ ግን የወረዳ የበላይ ተመልካቹን አነጋገርነው። እሱም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲህ የሚል ግልጽ ምክር ሰጠን፦ “እናንተ ራሳችሁ የችግሩ ክፍል መዝ. 141:5) ምክሩን ወዲያውኑ በሥራ ላይ አዋልነው። በዚህ ጊዜ በርካታ አዎንታዊ ነገሮች እንዳሉ ማስተዋል ቻልን። ወጣቶችንና የማያምን የትዳር አጋር ያላቸውን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ፍላጎት ነበራቸው። ይህ ለእኛ ወሳኝ ትምህርት ነው። የነገሮችን አዎንታዊ ገጽታ ማየትን እንዲሁም ተፈታታኝ ነገሮችን ይሖዋ እስኪያስተካክል ድረስ መታገሥን ተምረናል። (ሚክ. 7:7) ደስታችንን መልሰን አገኘን፤ ሁኔታውም መሻሻል ጀመረ።
ናችሁ። ያላችሁበት ሁኔታ ባለው አሉታዊ ገጽታ ላይ እያተኮራችሁ ነው። አዎንታዊ ነገሮችን ማግኘት ከፈለጋችሁ ግን ማግኘታችሁ አይቀርም።” ይህ ምክር በጣም ያስፈልገን ነበር። (በአቅኚነት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ስንካፈል የተመደቡልን አስተማሪዎች ቀደም ሲል በሌሎች አገራት ያገለግሉ ነበር። አስተማሪዎቹ ፎቶግራፍ እያሳዩ ስላጋጠማቸው ተፈታታኝ ሁኔታና ስላገኙት በረከት ሲነግሩን ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት አደረብን። በመሆኑም በዚህ አገልግሎት ለመካፈል ወሰንን።
በብሪትሽ ኮሎምቢያ ባለ የስብሰባ አዳራሽ፣ 1983
እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ስንል በ1984 ፈረንሳይኛ ወደሚነገርበት ወደ ኩዊቤክ ተዛወርን፤ ይህ አካባቢ ከብሪትሽ ኮሎምቢያ 4,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ለውጥ አዲስ ባሕልና ቋንቋ መማር ጠይቆብናል። ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ ደግሞ ብዙ ጊዜ ገንዘብ ያልቅብን ነበር። በአንድ ወቅት፣ የምንበላውን ምግብ የምናገኘው በአንድ ገበሬ እርሻ ላይ ያለውን የወዳደቀ ድንች በመቃረም ነበር። ዴቢ በድንች የተለያዩ ዓይነት ምግቦችን በማብሰል ተካነች። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በደስታ ለመጽናት ጥረት እናደርግ ነበር። ከዚህም በላይ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ማየት ችለናል።—መዝ. 64:10
አንድ ቀን ያልጠበቅነው ስልክ ተደወለልን። በካናዳ ቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን። ቀደም ሲል በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል አመልክተን ስለነበር ቤቴል ለማገልገል ስንጋበዝ የተቀላቀለ ስሜት ተሰምቶን ነበር። ሆኖም ግብዣውን ተቀበልን። እዚያ ከደረስን በኋላ በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለውን ወንድም ኬነዝ ሊትልን “የጊልያድ ማመልከቻችንስ እንዴት ሊሆን ነው?” ብለን ጠየቅነው። እሱም “ወንዙ ጋ ስንደርስ ድልድዩን እንሻገራለን” ብሎ መለሰልን።
የሚገርመው ከአንድ ሳምንት በኋላ ወንዙ ጋ ደረስን። እኔና ዴቢ በጊልያድ እንድንማር ተጋበዝን። ስለዚህ ውሳኔ ማድረግ ነበረብን። ወንድም ሊትል እንዲህ አለን፦ “የትኛውንም ብትመርጡ ‘ምናለ ያኛውን በመረጥኩ’ ብላችሁ
የምታስቡበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሁለቱም በእኩል መጠን ጥሩ ምርጫዎች ናቸው። ይሖዋ የትኛውንም ምርጫ ሊባርክ ይችላል።” በመሆኑም ጊልያድ ለመሄድ ወሰንን። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የወንድም ሊትል ምክር በጣም ትክክል እንደሆነ ማየት ችለናል። ከሁለት የአገልግሎት ምድቦች አንዱን መምረጥ ላስፈለጋቸው ክርስቲያኖች የእሱን ምክር እንነግራቸዋለን።የሚስዮናዊነት ሕይወት
(በስተ ግራ) ዩሊሴዝ ግላስ
(በስተ ቀኝ) ጃክ ሬድፎርድ
ሚያዝያ 1987 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በተካሄደው የጊልያድ ትምህርት ቤት 83ኛ ክፍል ላይ ከሚማሩት 24 ተማሪዎች መካከል በመሆናችን በጣም ተደሰትን። ዋነኞቹ አስተማሪዎቻችን ወንድም ዩሊሴዝ ግላስ እና ወንድም ጃክ ሬድፎርድ ነበሩ። አምስቱ ወራት ወዲያውኑ አለቁና መስከረም 6, 1987 ተመረቅን። ከጆን ጉድ እና ከማሪ ጉድ ጋር ሆነን በሄይቲ እንድናገለግል ተመደብን።
ሄይቲ ውስጥ፣ 1988
በ1962 የመጨረሻዎቹ ሚስዮናውያን ከተባረሩ ወዲህ ከጊልያድ የተመረቁ ሚስዮናውያን ወደ ሄይቲ ተልከው አያውቁም። ከተመረቅን ከሦስት ሳምንታት በኋላ በሄይቲ ማገልገል ጀመርን። የተመደብንበት ጉባኤ 35 አስፋፊዎች ያሉት ተራራማ አካባቢ ላይ ያለ ትንሽ ጉባኤ ነው። ወጣቶች ነበርን፤ ተሞክሮም አልነበረንም። የምንኖረው በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ለብቻችን ነበር። ሰዎቹ በጣም ድሆች ነበሩ፤ ደግሞም አብዛኞቹ ማንበብ አይችሉም። እዚያ በኖርንበት ጊዜ ሕዝባዊ ዓመፅ፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲሁም አውሎ ነፋሶች አጋጥመውናል።
በሄይቲ ከነበሩት መንፈሰ ጠንካራና ደስተኛ ወንድሞችና እህቶች ብዙ ትምህርት አግኝተናል። ብዙዎቹ ሕይወታቸው በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋንና አገልግሎትን ይወዱ
ነበር። ለምሳሌ አንዲት አረጋዊት እህት ማንበብ ባትችልም 150 ገደማ ጥቅሶችን በቃሏ ታውቅ ነበር። በየቀኑ የምናየው ነገር፣ ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ ስለሚሰጠው ስለ አምላክ መንግሥት መስበካችንን እንድንቀጥል ቁርጠኝነታችንን አጠናክሮታል። ከመጀመሪያዎቹ ጥናቶቻችን አንዳንዶቹ የዘወትር አቅኚ፣ ልዩ አቅኚ እንዲሁም የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው ሲያገለግሉ ማየት በጣም የሚያስደስት ነው።ሄይቲ ሳለሁ የሞርሞን እምነት ሚስዮናዊ ከሆነ ትሬቨር የተባለ ወጣት ጋር ተገናኝቼ ነበር። ከእሱ ጋር በተደጋጋሚ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተወያይተናል። ከዓመታት በኋላ ከትሬቨር ያልተጠበቀ ደብዳቤ ደረሰኝ። እንዲህ ሲል ጻፈልኝ፦ “በቀጣዩ ትልቅ ስብሰባ ላይ እጠመቃለሁ። ወደ ሄይቲ ተመልሼ የሞርሞን ሚስዮናዊ በነበርኩበት በዚያው አካባቢ ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል እፈልጋለሁ።” ትሬቨር ከሚስቱ ጋር ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ይህንኑ አድርጓል።
አውሮፓ—ቀጥሎም አፍሪካ
በስሎቬንያ ስሠራ፣ 1994
በአንዳንድ የአውሮፓ ክፍሎች በመንግሥቱ ሥራ ላይ የተጣለው እገዳ እየላላ ነበር፤ እኛም እዚያ እንድናገለግል ተመደብን። በ1992 ሉብሊያና፣ ስሎቬንያ ደረስን። ወላጆቼ ወደ ጣሊያን ከመሄዳቸው በፊት ያደጉት በዚያ አቅራቢያ ነው። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሥር ባሉ አካባቢዎች ጦርነቱ ገና አላበቃም ነበር። በቪየና፣ ኦስትሪያ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲሁም በዛግሬብ፣ ክሮኤሺያ እና በቤልግሬድ፣ ሰርቢያ ያሉት ቢሮዎች በአካባቢው ያለውን ሥራ በበላይነት ይከታተሉ ነበር። አሁን እያንዳንዱ ራስ ገዝ ሪፑብሊክ የራሱ ቤቴል እንዲኖረው ተወሰነ።
በመሆኑም አዲስ ቋንቋና ባሕል መልመድ ነበረብን። የአካባቢው ሰዎች “ዬዢክ ዬ ቴዢክ” ይሉ ነበር፤ ይህም “ቋንቋው ከባድ ነው” ማለት ነው። ደግሞም እውነታቸውን ነው! በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተደረጉትን ለውጦች ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል በፈቃደኝነትና በታማኝነት እንደተቀበሉ ስናይ ለእነሱ አድናቆት አደረብን፤ ይሖዋ እንዴት እንደባረካቸውም አስተዋልን። ይሖዋ ምንጊዜም ነገሮችን በፍቅር እንደሚያስተካክል በድጋሚ ተመለከትን፤ ደግሞም ይህን የሚያደርገው በትክክለኛው ጊዜ ላይ ነው። በስሎቬንያ ባሳለፍናቸው ዓመታት፣ ቀደም ሲል ያገኘናቸው ብዙ ትምህርቶች ተጠናክረውልናል፤ አዳዲስ ትምህርቶችንም አግኝተናል።
ሆኖም ከዚያ በኋላም ብዙ ለውጦች አጋጥመውናል። በ2000 በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በኮት ዲቩዋር እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያም ኅዳር 2002 በእርስ በርስ ጦርነቱ የተነሳ ወደ ሴራ ሊዮን ተወሰድን። በወቅቱ በሴራ ሊዮን የነበረው ለ11 ዓመት የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃቱ ነበር። ድንገት ተነስቶ ከኮት ዲቩዋር መውጣት ቀላል አልነበረም። ሆኖም ያገኘናቸው ትምህርቶች ደስታችንን መጠበቅ እንድንችል ረድተውናል።
ፍሬያማ በነበረው ክልልና ለዓመታት ጦርነትን በጽናት በተቋቋሙት አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች ላይ አተኮርን። ድሆች ቢሆኑም ያላቸውን ለማካፈል ፈቃደኞች ነበሩ። አንዲት እህት ለዴቢ ልብሶች ሰጠቻት። ዴቢ ልብሱን ለመቀበል ስታቅማማ እህታችን እንዲህ አለቻት፦ “በጦርነቱ ወቅት በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞቻችን ሲደግፉን ነበር። አሁን ደግሞ የእኛ ተራ ነው።” እኛም የእነሱን ምሳሌ ለመከተል ግብ አወጣን።
ቆየት ብለን ወደ ኮት ዲቩዋር ተመለስን። ሆኖም በዚያ የነበረው ዓመፅ በድጋሚ አገረሸ። ስለዚህ ኅዳር 2004 በሄሊኮፕተር ከአገሪቱ ወጣን። ሁለታችንም የያዝነው 10 ኪሎ ግራም የሚመዝን አንድ አንድ ሻንጣ ብቻ ነበር። በፈረንሳይ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ መሬት ላይ ተኝተን አደርን። ከዚያም በማግስቱ በአውሮፕላን ወደ ስዊዘርላንድ ተወሰድን። እኩለ ሌሊት ገደማ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ስንደርስ የቅርንጫፍ ኮሚቴው አባላትና የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መምህራን ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው ሞቅ ባለ መንገድ ተቀበሉን። እቅፍ አደረጉን፤ ትኩስ ምግብ አቀረቡልን፤ እንዲሁም ብዙ የስዊዘርላንድ ቸኮሌት ሰጡን። ልባችን በጥልቅ ተነካ።
በኮት ዲቩዋር ለስደተኞች ንግግር ሳቀርብ፣ 2005
ከዚያም ለአጭር ጊዜ ያህል በጋና ተመደብን፤ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተረጋጋ በኋላ ደግሞ ወደ ኮት ዲቩዋር ተመለስን። ወንድሞቻችን ያሳዩን ደግነት፣ ድንገት ተነስተን ከአገር በምንወጣበት ወቅትና በጊዜያዊ ምድቦቻችን ላይ በእጅጉ ጠቅሞናል። እኔና ዴቢ እንዲህ ያለው የወንድማማች ፍቅር የይሖዋ ድርጅት መለያ ቢሆንም ይህን ፍቅር መቼም ቢሆን አቅልለን ላለመመልከት ወሰንን። እንዲያውም ከዚያ የመከራ ጊዜ በጣም ጠቃሚ ሥልጠና አግኝተናል።
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄድን
በመካከለኛው ምሥራቅ፣ 2007
በ2006 በመካከለኛው ምሥራቅ አዲስ ምድብ እንደተሰጠን የሚገልጽ ደብዳቤ ከዋናው መሥሪያ ቤት ደረሰን። አሁንም አዲስ ሕይወት፣ አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ አዳዲስ ቋንቋዎችና አዳዲስ ባሕሎችን ማስተናገድ ነበረብን። በፖለቲካና በሃይማኖት በተከፋፈለው በዚህ አካባቢ ብዙ ትምህርት አግኝተናል። በጉባኤዎቹ ውስጥ ያሉትን የተለያየ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ወንድሞች ማየት አስደሳች ነው። እንዲሁም ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን መከተል አንድነት እንደሚያስገኝ ተመልክተናል። አብዛኞቹ ወንድሞች ከቤተሰባቸው አባላት፣ አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው የሚደርስባቸውን ተቃውሞ በድፍረት ይቋቋሙ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በጣም እናደንቃቸዋለን።
በ2012 በቴል አቪቭ፣ እስራኤል በተካሄደው ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ተገኝተን ነበር። በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች በዚያ አካባቢ እንዲህ በብዛት የተሰበሰቡት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ፈጽሞ የማይረሳ ስብሰባ ነበር!
በዚያ ወቅት፣ በሥራችን ላይ ገደብ በተጣለበት አንድ አገር ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንን እንድንጎበኝ ተላክን። የተወሰነ ጽሑፍ ይዘን ሄድን፤ አብረናቸው አገለገልን፤ እንዲሁም
ትናንሽ የወረዳ ስብሰባዎችን አደረግን። በየቦታው ብዙ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮችና ኬላዎች ነበሩ። ሆኖም በቦታው ከነበሩት ጥቂት አስፋፊዎች ጋር በጥንቃቄ ስንንቀሳቀስ እምብዛም ስጋት አላደረብንም።ወደ አፍሪካ ተመለስን
በኪንሻሳ፣ ኮንጎ ንግግር ስዘጋጅ፣ 2014
በ2013 ለየት ያለ የአገልግሎት ምድብ ተሰጠን፤ በኪንሻሳ በሚገኘው የኮንጎ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ኮንጎ ውብ ተፈጥሮ ያላት ሰፊ አገር ብትሆንም በከባድ ድህነትና በዓመፅ ስትታመስ ቆይታለች። መጀመሪያ ላይ “አፍሪካን በደንብ እናውቃታለን፤ ዝግጁ ነን” ብለን አስበን ነበር። ሆኖም ገና መማር ያለብን ብዙ ነገር ነበር። በተለይ መሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች መጓዝ ለእኛ አዲስ ነበር። ሆኖም ልናተኩርበት የምንችል ብዙ መልካም ነገር አግኝተናል። ለምሳሌ ወንድሞችና እህቶች በከባድ ድህነት ውስጥ እየኖሩም የነበራቸው ደስታና ጽናት፣ ለአገልግሎት ያላቸው ፍቅር እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የሚከፍሉት መሥዋዕትነት አስደናቂ ነው። የመንግሥቱ ሥራ ፍሬ ያፈራው በይሖዋ ድጋፍና በረከት ብቻ እንደሆነ በገዛ ዓይናችን አይተናል። ኮንጎ ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍናቸው ዓመታት የማይረሳ ትዝታ ጥለውብናል፤ መንፈሳዊ ቤተሰባችንም በጣም ሰፍቷል።
በደቡብ አፍሪካ ስንሰብክ፣ 2023
በ2017 መጨረሻ ላይ በደቡብ አፍሪካ አዲስ ምድብ ተሰጠን። እስካሁን ካገለገልንባቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎች ትልቁ ይሄ ነው። በቤቴል የተሰጠን የሥራ ምድብም ለእኛ አዲስ ነበር። ያኔም መማር ያለብን ብዙ ነገር ነበር፤ ግን ቀደም ሲል ያገኘናቸው ትምህርቶች በጣም ጠቅመውናል። ለአሥርተ ዓመታት የጸኑትን በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከልብ እንወዳቸዋለን። ከተለያየ ዘርና ባሕል የተውጣጡ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በአንድነት ሲሠሩ ማየትም በጣም አስደናቂ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች አዲሱን ስብዕና ሲለብሱና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ሲያውሉ ይሖዋ ሰላም በመስጠት እንደባረካቸው በግልጽ ማየት ችለናል።
እኔና ዴቢ ባለፉት በርካታ ዓመታት ደስ የሚሉ የአገልግሎት ምድቦችን ተቀብለናል፤ ከአዳዲስ ባሕሎች ጋር ተላምደናል፤ እንዲሁም አዳዲስ ቋንቋዎችን ተምረናል። ያሳለፍናቸው አንዳንዶቹ ነገሮች ተፈታታኝ ቢሆኑም በድርጅቱና በወንድማማች ማኅበራችን አማካኝነት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ሁልጊዜም አጣጥመናል። (መዝ. 144:2) ከሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያገኘነው ሥልጠና የተሻልን የይሖዋ አገልጋዮች እንዳደረገን እናምናለን።
ከወላጆቼ ያገኘሁትን ሥልጠና፣ ከውዷ ባለቤቴ ከዴቢ ያገኘሁትን ድጋፍ እንዲሁም በዓለም አቀፉ መንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ ያገኘኋቸውን ግሩም ምሳሌዎች ከፍ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ። ወደፊትም ቢሆን ከታላቁ አስተማሪያችን መማራችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።