መዝሙር 64:1-10

  • ስውር ከሆኑ ጥቃቶች ጥበቃ ማግኘት

    • “አምላክ ይመታቸዋል” (7)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት ማህሌት። 64  አምላክ ሆይ፣ የማቀርበውን ልመና ስማ።+ ጠላት ከሚሰነዝርብኝ አስፈሪ ጥቃት ሕይወቴን ታደግ።   ከክፉ ሰዎች ስውር ሴራ፣ከክፉ አድራጊዎች ሸንጎ ጠብቀኝ፤+   እነሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤መርዘኛ ቃላቸውን እንደ ቀስት ያነጣጥራሉ፤   ይህን የሚያደርጉት ከተደበቁበት ቦታ ሆነው ንጹሑን ሰው ለመምታት ነው፤ያላንዳች ፍርሃት በድንገት ይመቱታል።   ክፉ ዓላማቸውን ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፤*በስውር እንዴት ወጥመድ እንደሚዘረጉ ይነጋገራሉ። “ማን ያየዋል?” ይላሉ።+   ክፉ ነገር ለመሥራት አዳዲስ መንገዶች ይቀይሳሉ፤የረቀቀ ሴራቸውን በስውር ይሸርባሉ፤+በእያንዳንዳቸው ልብ ውስጥ ያለው ሐሳብ አይደረስበትም።   ሆኖም አምላክ ይመታቸዋል፤+እነሱም በድንገት በቀስት ይቆስላሉ።   የገዛ ምላሳቸው ለውድቀት ይዳርጋቸዋል፤+ይህን የሚመለከቱ ሁሉ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።   በዚህ ጊዜ ሰዎች ሁሉ ይፈራሉ፤አምላክ ያደረገውንም ነገር ያውጃሉ፤ሥራውንም በሚገባ ያስተውላሉ።+ 10  ጻድቅ ሰው በይሖዋ ሐሴት ያደርጋል፤ እሱንም መጠጊያው ያደርጋል፤+ቀና ልብ ያላቸውም ሁሉ ይደሰታሉ።*

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ክፉ ነገር ለማድረግ አንዳቸው ሌላውን ያበረታታሉ።”
ወይም “ይኮራሉ።”