በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ጀርመን ውስጥ ለሚገኙት የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች ምሥራቹን ማድረስ

ጀርመን ውስጥ ለሚገኙት የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች ምሥራቹን ማድረስ

ጀርመን ውስጥ በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች ይኖራሉ። * በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች የእነዚህ ሕዝቦች የአፍ መፍቻ ቋንቋ በሆነው በሮማኒ ቋንቋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትራክቶችን፣ ብሮሹሮችንና ቪዲዮዎችን አዘጋጅተዋል። *

በመስከረምና በጥቅምት 2016 በተደረገ ልዩ ዘመቻ የይሖዋ ምሥክሮች በበርሊን፣ በብሪመሃቨነ፣ በፋይበርግ፣ በሀምበርግ፣ በሄይደልበርግና በሌሎች የተለያዩ የጀርመን ከተሞች ለሚኖሩ የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች በሮማኒ ቋንቋ የተዘጋጀውን ይህን መልዕክት ለማካፈል ጥረት አድርገዋል። በተጨማሪም በስብሰባ አዳራሾቻቸው በሮማኒ ቋንቋ የሕዝብ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት አድርገው ነበር።

አስደናቂ ምላሽ

ብዙዎቹ የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች የይሖዋ ምሥክሮች ባካሄዱት በዚህ ዘመቻ በጣም ተገርመዋል እንዲሁም ተደስተዋል። “ሰዎቹ እነሱን ለማግኘት ልዩ ጥረት በማድረጋችን ተደስተዋል” በማለት በዘመቻው የተካፈሉት አንድሬና ኤስተር የሚባሉ ባልና ሚስት ተናግረዋል። ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሰሙና ሲያነቡ ልባቸው ተነክቷል። አንዲት ወጣት በሮማኒ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተሰኘውን ቪዲዮ ከተመለከተች በኋላ ዓይኗን ማመን አቅቷት “እንዴ! ይህ እኮ የእኔ ቋንቋ ነው!” በማለት ደጋግማ በአድናቆት ትናገር ነበር።

በሀምበርግ በተደረገው ዘመቻ የተካፈለ ማቲያስ የተባለ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ስምንት አባላት ባሉት ቡድን ውስጥ ሆነን 400 ገደማ የሚሆኑ የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች ወደሚኖሩበት ክልል ሄደን ነበር። ያነጋገርናቸው ሰዎች ሁሉ ጽሑፍ እንድንሰጣቸው ይጠይቁን ነበር።” በሀምበርግ በተካሄደው ዘመቻ የተካፈለችው ቤቲና “የይሖዋ ምሥክሮች በሮማኒ ቋንቋ ጽሑፍ እንዳዘጋጁ ሲያውቁ ያለቀሱም አሉ” በማለት ተናግራለች። ብዙዎቹ ወዲያውኑ ከጽሑፎቹ ላይ ጮክ ብለው ማንበብ የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ለጓደኞቻቸው የሚሰጡት ተጨማሪ ጽሑፍ ወስደዋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች በቋንቋቸው ወደተዘጋጁት የሕዝብ ስብሰባዎች እንዲመጡ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። ሀምበርግ ውስጥ በስብሰባው ላይ ከተገኙት 94 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው አያውቁም። በሄይደልበርግ አቅራቢያ በምትገኘው በራይሊንገን በተደረገው ስብሰባ ላይ 123 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ከዚያም የሮማኒ ቋንቋ የሚናገሩ አምስት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ጥያቄ አቅርበዋል።

በዘመቻው ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 3,000 የሚጠጉ ትራክቶችንና ብሮሹሮችን አሠራጭተዋል። የይሖዋ ምሥክሮቹ ከ360 ከሚበልጡ የሲንቲ እና የሮማ ሕዝቦች ውይይት ያደረጉ ሲሆን 19ኙ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ “አምላክ እጁን እየዘረጋልን መሆኑ በጣም ደስ ይላል” በማለት ተናግረዋል።

^ አን.2 ሲንቲ የሚባሉት ሕዝቦች የሚኖሩት በምዕራብና በማዕከላዊ አውሮፓ ሲሆን ሮማ የሚባሉት ሕዝቦች ደግሞ መነሻቸው ምሥራቅና ደቡባዊ ምሥራቅ አውሮፓ ነው፤ ሁለቱም ማኅበረሰቦች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።

^ አን.2 ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ኦንላይን እንደሚገልጸው የሮማኒ ቋንቋ “60 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ በጣም የተለያዩ ቀበሌኛዎችን” የያዘ ነው። ለአጻጻፍ እንዲያመች ይህ ርዕስ በጀርመን የሚኖሩ የሲንቲና የሮማ ሕዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋ ለማመልከት “ሮማኒ” የሚለውን ቃል ይጠቀማል።