በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 19, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በዓለማችን የመጀመሪያው የተሟላ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ

በዓለማችን የመጀመሪያው የተሟላ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው የመጨረሻው የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ መውጣቱን የካቲት 15, 2020 አበሰረ። ይህ ትርጉም በዓለማችን የመጀመሪያው ሙሉ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ ታሪካዊ ማስታወቂያ የተነገረው በፎርት ሎደርዴል፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተገነባው አዲሱ የአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ የውሰና ፕሮግራም ላይ ነው። ፕሮግራሙ የተካሄደው በዌስት ፓልም ቢች ፍሎሪዳ በሚገኘው ክርስቺያን ኮንቬንሽን ሴንተር በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ ማዕከል ውስጥ ነው።

ከ2,500 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሲሆን በሄይቲ፣ በቤሊዝ፣ በትሪኒዳድ እና ቶቤጎ፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በሚገኙ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የተገኙ 15,635 ሰዎች ፕሮግራሙን በቀጥታ ሥርጭት ተከታትለዋል፤ በመሆኑም በፕሮግራሙ ላይ የተካፈሉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ከ18,000 በላይ ነበር።

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን በፕሮግራሙ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ

ከውሰና ንግግሩ በኋላ ወንድም ጃክሰን በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው የመጨረሻው መጽሐፍ መውጣቱን አበሰረ። ወንድም ጃክሰን ንግግሩን ሲደመድም “አንድ ልዩ ማስታወቂያ ልንነግራችሁ እንፈልጋለን” አለ። አክሎም እንዲህ አለ፦ “የቀረው የኢዮብ መጽሐፍ ብቻ ነበር፤ አሁን አዲስ ዓለም ትርጉም የተሟላ ሆኗል። እስካሁን ድረስ ድረስ ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ ያወጣ ሌላ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም። በመሆኑም በመላው ዓለም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የተሟላ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ነው።”

ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አሜሪካ ምልክት ቋንቋ ለመተርጎም 15 ዓመት ፈጅቷል፤ ለሕዝብ የተለቀቀው የመጨረሻ መጽሐፍ የኢዮብ መጽሐፍ ነው። የበላይ አካሉ አዲስ ዓለም ትርጉም ወደ አሜሪካ ምልክት ቋንቋ እንዲተረጎም ፈቃድ የሰጠው በ2004 ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ የማቴዎስ መጽሐፍ ወጣ፤ እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ ሌሎቹ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትም ወጡ። ባለፉት አሥር ዓመታት ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወጡ።

አዲስ ዓለም ትርጉም ደረጃ በደረጃ መውጣቱ መስማት በተሳናቸው ሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ተጽዕኖ አሳድሯል። ኢሳያስ ኢተን የተባለ በፕሮግራሙ ላይ የተገኘ አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “አዲስ ዓለም ትርጉምን ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ። መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ሳነብ ልቤ አልተነካም ነበር። የሚገርመው በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ማየት እንደጀመርኩ ወዲያው እንባዬ መጣ።”

ይህ ትርጉም በምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ በርካታ አስፋፊዎች የአገልግሎታቸውን ጥራት እንዲያሻሽሉ ረድቷል። በርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ የአሜሪካ ምልክት ቋንቋ ተርጓሚ የሆነው ዴቪድ ጎንዛሌዝ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ሙሉ በሙሉ መረዳት እንድችልና በአገልግሎት ደፋር እንድሆን ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስ በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ ከመውጣቱ በፊት በራስ የመተማመን ስሜት ስላልነበረኝ አገልግሎት ላይ የማነጋግራቸው ሰዎች ከባድ ጥያቄ እንዳይጠይቁኝ እመኝ ነበር። አሁን ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ስላለኝ ዝግጁ ሆኛለሁ። በራስ የመተማመን ስሜቴም ጨምሯል!”

ዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ባለው የትርጉም አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ የሚያስተባብረው ወንድም ኒኮላስ አላዲስ እንዲህ ብሏል፦ “የአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፕሮጀክት ለሌሎች የምልክት ቋንቋዎችም እንደ ሞዴል ሆኗል። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በ17 የምልክት ቋንቋዎች ወጥተዋል፤ በተጨማሪ የምልክት ቋንቋዎችም ሥራው እንደሚከናወን ይጠበቃል።”

በአሜሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች የአምላክን ቃል በራሳቸው ቋንቋ በማግኘታቸው ልባቸው እንዲነካና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።—የሐዋርያት ሥራ 2:6