በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው?

 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ይሁንና የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሚገኝባቸው ቋንቋዎች ሁሉ ይህን ትርጉም መጠቀም ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም ይህ ትርጉም የአምላክን ስም የሚጠቀም ከመሆኑም ሌላ ትክክለኛና ግልጽ ነው።

  •   የአምላክን ስም መጠቀም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጆች የመጽሐፉን ባለቤት በስም ሳይጠቅሱ በመቅረታቸው የሚገባውን ክብር ነፍገውታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ መጽሐፉን በማዘጋጀቱ ሥራ አስተዋጽኦ ያደረጉ ከ70 የሚበልጡ ሰዎች ስም ተጠቅሷል። ያም ቢሆን ይህ ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን አምላክ ስም ይኸውም ይሖዋ የሚለውን ስም አንድም ቦታ ላይ አይጠቅስም!

     በአንጻሩ ግን አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊው ስም መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ በነበረባቸው ቦታዎች ሁሉ ማለትም በሺህዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ እንዲመለስ አድርጓል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ትርጉም ያዘጋጀው ኮሚቴ አባላት ስም አልተጠቀሰም።

  •   ትክክለኛ ትርጉም። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ቋንቋ የያዘውን መልእክት በትክክል የሚያስተላልፉት ሁሉም ትርጉሞች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ትርጉም ማቴዎስ 7:13ን ያስቀመጠው በዚህ መንገድ ነው፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ገሃነም የሚወስደው በር ሰፊ ነው፤ በዚያ መሄድም ቀላል ነው።” ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ እዚህ ጥቅስ ላይ የገባው ቃል ትርጉም “ጥፋት” እንጂ “ገሃነም” አይደለም። ምናልባት ተርጓሚዎቹ ይህን ቃል የተጠቀሙት ክፉዎች ለዘላለም በገሃነመ እሳት እንደሚሠቃዩ ስለሚያምኑ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን ሐሳብ አይደግፍም። በመሆኑም አዲስ ዓለም ትርጉም ጥቅሱን እንደሚከተለው በማለት በትክክል ተርጉሞታል፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅና ሰፊ ነው።”

  •   ለመረዳት ቀላል የሆነ። አንድ ጥሩ ትርጉም፣ ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን ግልጽና በቀላሉ የሚገባ መሆን ይኖርበታል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በሮም 12:11 ላይ ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ቃል በቃል ሲተረጎም “መንፈሳችሁ ይፍላ” የሚል ትርጉም ያለው አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህ አገላለጽ በአሁኑ ጊዜ ትርጉም የማይሰጥ በመሆኑ በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ጥቅሱ በቀላሉ በሚገባ መንገድ ተተርጉሟል። ጥቅሱ ክርስቲያኖችን “በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ” ብሏቸዋል።

 አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም የሚጠቀም፣ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም ከመሆኑ በተጨማሪ ሌላም ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ፤ ይህ ትርጉም የሚሰራጨው በነፃ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት አቅማቸው የማይፈቅድ ሰዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ቃል በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብ ችለዋል።