በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጽሑፍ በሌለው ቋንቋ መተርጎም

ጽሑፍ በሌለው ቋንቋ መተርጎም

የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን ከእንግሊዝኛ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ይተረጉማሉ፤ በአሁኑ ወቅት የሕትመት ውጤቶቻቸው ከ900 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በእንግሊዝኛ የተጻፈውን ነገር ወደ ሌላ የጽሑፍ ቋንቋ መተርጎም በራሱ ከባድ ነገር ነው። ጽሑፉን ወደ ምልክት ቋንቋ መተርጎም ደግሞ ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል። መስማት የተሳናቸው ብዙዎቹ ሰዎች የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉት እጃቸውንና የፊታቸውን ገጽታ በመጠቀም ነው፤ በመሆኑም የምልክት ቋንቋ ተርጓሚዎች ጽሑፉን የሚተረጉሙት ወደ ቪዲዮ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የሕትመት ውጤቶቻቸውን ከ90 ወደሚበልጡ የምልክት ቋንቋዎች ተርጉመዋል።

የሚተረጉሙት እነማን ናቸው?

ወደ ምልክት ቋንቋ የሚተረጉሙ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ሌሎቹ ተርጓሚዎች ሁሉ ስለሚተረጉሙበት ቋንቋ ጥሩ እውቀት አላቸው። ብዙዎቹ ተርጓሚዎች መስማት የተሳናቸው ሲሆኑ ከልጅነታቸው ጀምሮ የምልክት ቋንቋ ሲጠቀሙ የኖሩ ናቸው፤ ሌሎች ደግሞ መስማት የሚችሉ ቢሆንም ያደጉት መስማት የተሳነው ሰው ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናቸው።

አዳዲስ ተርጓሚዎች ለትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። አንድሩ የተባለ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “በልጅነቴ፣ መስማት ለተሳናቸው በተዘጋጀ ትምህርት ቤት ውስጥ ከመማሬም ሌላ በምልክት ቋንቋ እጠቀም ነበር፤ ያም ቢሆን በተርጓሚነት ያገኘሁት ሥልጠና የቋንቋውን የሰዋስው አወቃቀር በደንብ እንዳውቅ ረድቶኛል። ሌሎቹ ተርጓሚዎች ሐሳቡን በትክክል ለማስተላለፍ፣ በእጄ የማሳየውን ምልክት፣ የፊቴን ገጽታና የሰውነቴን እንቅስቃሴ እንዴት ማሻሻል እንደምችል አስተምረውኛል።”

ጥራት ያለው ትርጉም ማዘጋጀት

ተርጓሚዎቹ የሚሠሩት በቡድን ሆነው ነው። እያንዳንዱ የቡድኑ አባል የራሱ ሚና አለው፤ አንዱ ሲተረጉም ሌሎቹ ትርጉሙ ትክክልና በቀላሉ የሚገባ መሆኑን ይከታተላሉ። ከዚያም አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ትርጉሙን እንዲገመግሙ ይደረጋል። እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት ሐሳብ የትርጉም ሥራውን ጥራት ለማሻሻል ይረዳል። ይህ መደረጉ ተርጓሚዎቹ የሚጠቀሙባቸው ምልክቶችና ፊታቸው ላይ የሚታዩት መግለጫዎች ትክክል መሆናቸውንና መልእክቱ በትክክልና በግልጽ መተላለፉን ለማጣራት ያስችላል።

የፊኒሽ ምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን በእንግሊዝኛው ጽሑፍ ላይ ሲወያይ

አብዛኞቹ የምልክት ቋንቋ ተርጓሚዎች በምልክት ቋንቋ በሚመሩ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ። ተርጓሚዎች ይህን ማድረጋቸው ቋንቋቸውን ለማሻሻል ይረዳቸዋል።

የብራዚል ምልክት ቋንቋ ተርጓሚ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮ ሲቀረጽ

ይህን ያህል ጥረት የሚደረገው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ሰዎች ተስፋና መጽናኛ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንደሚቀበሉ ይናገራል። (ራእይ 7:9) ከእነዚህ ሰዎች መካከል የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ሰዎችም እንደሚገኙበት ጥያቄ የለውም።

ተርጓሚዎቹ ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን እንዲህ ላለው ጠቃሚ ዓላማ መጠቀም በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው። ቶኒ የተባለ አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ራሴ መስማት ስለማልችል ሌሎች መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መረዳት እችላለሁ። መስማት የተሳናቸው ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነተኛ ተስፋ እንዲያውቁ ለመርዳት ምንጊዜም ከልቤ እመኝ ነበር።”

በአንድ የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን ውስጥ የምትሠራው አማንዳም እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት፣ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚያሳውቁ ቪዲዮዎችን ስተረጉም በጣም ውጤታማ በሆነ ሥራ ላይ እንደተካፈልኩ ይሰማኛል፤ ቀደም ሲል ሌላ ሥራ እሠራ በነበረበት ወቅት እንዲህ ተሰምቶኝ አያውቅም።”

አንተ በምትጠቀምበት የምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

ፋይንድ ሳይን ላንግዌጅ ኮንቴንት የሚለው ገጽ ከ​jw.org ድረ ገጽ ላይ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ደረጃ በደረጃ ያሳያል።