በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 18, 2023
ሞዛምቢክ

የማቴዎስ ወንጌል በፒምቢ ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ ወንጌል በፒምቢ ቋንቋ ወጣ

ነሐሴ 13, 2023 የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ቻርልስ ፎንሴካ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በፒምቢ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። በፒምቢ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ሲታተም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የመጽሐፉ መውጣት የተበሰረው 3,055 ሰዎች በተገኙበትና በፊንጎኤ ከተማ በተካሄደው “በትግሥት ጠብቁ”! የተባለው የ2023 የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው ላይ ለተገኙት የመጽሐፉ የታተመ ቅጂ ደርሷቸዋል። የኤሌክትሮኒክ ቅጂውንም ማውረድና መጫን ተችሏል።

ፒምቢ በዋነኝነት የሚነገረው በሞዛምቢክ ምዕራባዊ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የቴቴ ግዛት ነው። የፒምቢ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር ከ100,000 እንደሚበልጥ ይገመታል። ሞዛምቢክ ውስጥ በፒምቢ ቋንቋ በሚመሩ 20 ጉባኤዎችና 2 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 897 አስፋፊዎች አሉ። የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ እንዲህ ብሏል፦ “የፒምቢ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሁን በቋንቋቸው የማቴዎስ ወንጌልን ማግኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተናል።”

የፒምቢ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችና እህቶቻችን፣ ኢየሱስ ‘ገር’ ለሆኑ ሁሉ የሰጠውን ተስፋ የያዘውን ይህን ስጦታ በማግኘታቸው እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም፤ እኛም የደስታቸው ተካፋዮች ነን።—ማቴዎስ 5:5