በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን መጽሐፍ ማዘጋጀት

ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን መጽሐፍ ማዘጋጀት

ጥር 1, 2021

 “አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ በጉጉት ስጠብቅ ነበር!” ይህ ወንድማችን ሲጠባበቅ የቆየው ነገር ምንድን ነው? የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአፍ መፍቻ ቋንቋው ማለትም በቤንጋሊ የሚወጣበትን ቀን ነው። ሌሎች ብዙ ሰዎችም አዲስ ዓለም ትርጉምን በራሳቸው ቋንቋ ሲያገኙ ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል። ሆኖም ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚተረጎመውና የሚዘጋጀው እንዴት ነው?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ?

 በቅድሚያ የበላይ አካሉ የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ፣ የትርጉም ቡድን እንዲቋቋም ያደርጋል። አንድ የትርጉም ቡድን መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል? በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የትርጉም አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚያገለግለው ኒኮላስ አላዲስ እንዲህ ብሏል፦ “የሚወስደው ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። የተርጓሚዎቹ ብዛት፣ የቋንቋው ባሕርይ፣ አንባቢዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረውን አኗኗር የመረዳት አቅማቸው እንዲሁም ቋንቋው በተለያዩ ቦታዎች የሚነገርበት መንገድ የሚለያይ መሆን አለመሆኑ ለውጥ ያመጣል። በአማካይ አንድ ቡድን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ብቻ ለመተርጎም ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም ደግሞ አራት ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ሊወስድበት ይችላል። በምልክት ቋንቋ በሚዘጋጅበት ወቅት ከዚህም የበለጠ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።”

 መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎሙ ሥራ የሚካፈሉት ተርጓሚዎቹ ብቻ አይደሉም። የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸው፣ ምናልባትም በተለያየ አገር የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎች የትርጉም ሥራውን አንብበው አስተያየት ይሰጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ያለምንም ክፍያ ነው። እነሱ የሚሰጡት አስተያየት ተርጓሚዎቹን ትክክለኛ፣ ግልጽና ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ይረዳቸዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥልጠና የሚሰጥ አንድ ወንድም እንደገለጸው “ተርጓሚዎቹ በይሖዋና ቃሉን በሚያነቡት ሰዎች ፊት ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ይሰማቸዋል።”

 የትርጉም ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሱ መታተምና መጠረዝ ይኖርበታል። ይህን ሥራ ለማከናወን ቢያንስ አሥር ነገሮች ማለትም ወረቀት፣ ቀለም፣ የመጽሐፍ ሽፋን፣ ማጣበቂያ፣ ሽፋኑ ላይ የሚለጠፍ ነገር፣ ብርማ ወረቀት፣ ሪባኖች፣ ለመጠረዣ የሚያገለግሉ ክሮች፣ ማጠናከሪያዎች እንዲሁም መጽሐፉን አንድ ላይ ለመጠረዝ የሚያስችል ቁስ ያስፈልጋሉ። በ2019 መጽሐፍ ቅዱስን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉትን እነዚህን ነገሮች ለማሟላት ብቻ ከ20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል። በዚያ ዓመት መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማዘጋጀትና ለመላክ በሕትመት ክፍል የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ከ300,000 ሰዓታት በላይ ሠርተዋል።

“መጽሐፍ ቅዱስ ከምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው መጽሐፍ ነው”

 ለዚህ ሥራ ይህን ያህል ጊዜና ገንዘብ ማዋል ያስፈለገው ለምንድን ነው? በዓለም አቀፍ የሕትመት ክፍል ውስጥ የሚያገለግለው ጆኤል ብሉ “መጽሐፍ ቅዱስ ከምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው መጽሐፍ ነው” ብሏል። አክሎም “ስለዚህ የመጽሐፉ ገጽታ የምናመልከውን አምላክና የምንሰብከውን መልእክት የሚያስከብር እንዲሆን እንፈልጋለን” ሲል ተናግሯል።

 ከመደበኛው አዲስ ዓለም ትርጉም እትም በተጨማሪ ለየት ያሉ እትሞችንም እናዘጋጃለን። ለምሳሌ በብሬይል የሚዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም በአሥር ቋንቋዎች ይገኛል። አንድ ሙሉ የብሬይል መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት እስከ ስምንት ሰዓት ሊወስድ ይችላል፤ በተጨማሪም ብዙ ጥራዞች ስለሚኖሩት ቢያንስ 2.3 ሜትር ርዝመት ያለው የጽሑፍ መደርደሪያ ቦታ ያስፈልገዋል። ከዚህም ሌላ የወረቀት ሽፋን ያላቸው መጽሐፎች ብቻ እንዲገቡ በሚፈቀድባቸው እስር ቤቶች ላሉ እስረኞች ለየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም እናዘጋጃለን።

 አዲስ ዓለም ትርጉም በአንባቢዎቹ ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣል። ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ኮንጎ ውስጥ ቶምብ በተባለች ቦታ የሚገኘውን የኪሉባ ቋንቋ ጉባኤ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ቶምብ ከአገሪቱ ዋና ከተማ ከ1,700 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ትገኛለች። በጉባኤው ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸው በኪሉባ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ብቻ ሲሆን እሱም የቆየ ትርጉም ነው። ወንድሞች ለስብሰባ ክፍሎች ለመዘጋጀት ይህን መጽሐፍ ቅዱስ እየተዋዋሱ ይጠቀሙ ነበር። ሆኖም ከነሐሴ 2018 አንስቶ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ በዘመናዊ የኪሉባ ቋንቋ የተዘጋጀውን ሙሉ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ችለዋል።

 ጀርመንኛ ቋንቋ የምትናገር አንዲት እህት ተሻሽሎ ስለተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም እንዲህ ብላለች፦ “አሁን ‘መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ አለብኝ’ ብቻ ብዬ አይደለም የማስበው። ከዚህ ይልቅ ተጨማሪ ምዕራፍ የማነብበት ጊዜ ይናፍቀኛል።” አንድ እስረኛ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ አግኝቻለሁ፤ ይህ ትርጉም በሕይወቴ ላይ ለውጥ እንዳደርግ እየረዳኝ ነው። የአምላክን ቃል በደንብ መረዳት የቻልኩት ይህን ትርጉም መጠቀም ከጀመርኩ በኋላ ነው። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ ማወቅና እንደ እነሱ መሆን የምችለው እንዴት እንደሆነ መማር እፈልጋለሁ።”

 አዲስ ዓለም ትርጉምን የሚጠቀሙ ሁሉ ይህን የትርጉም ሥራ ለመደገፍ ለሚደረገው የገንዘብ መዋጮ አመስጋኞች ናቸው። ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ የሚደረገው donate.jw.org ላይ በተገለጹት መንገዶች ነው። ለልግስናችሁ በጣም እናመሰግናለን።