በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ተአምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ?​—የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦች

በእርግጥ ተአምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ?​—የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦች

በእርግጥ ተአምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ?​—የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦች

የተቃውሞ ሐሳብ 1፦ ተአምራት ከተፈጥሮ ሕግጋት ጋር ስለሚጋጩ ሊፈጸሙ አይችሉም። ስለ ተፈጥሮ ሕግጋት ያለን እውቀት፣ የሳይንስ ሊቃውንት በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች በመመልከት በደረሱበት መደምደሚያ ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህ ሕግጋት ከአንድ ቋንቋ የሰዋስው ሕግጋት ጋር ይመሳሰላሉ፤ የቋንቋው የሰዋስው ሕግጋት የማይሠሩባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ይኖራሉ። ስለ ተፈጥሮ “ሕግጋት” ያለን ግንዛቤም በጣም ውስን ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 38:4) አንድ የሳይንስ ሊቅ ዕድሜውን ሙሉ ስለ አንድ የተፈጥሮ ሕግ አጥንቶ ይሆናል። ሆኖም ይህ ሕግ የማይሠራበት አንድ “የተለየ ሁኔታ” ካጋጠመው ስለዚያ ሕግ የነበረውን እውቀት እንደገና መገምገም ይኖርበታል። ሕጉ የማይሠራበት አንድ ሁኔታ እንኳ ቢገኝ የሕጉን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

ስለ አንድ ነገር የተሟላ መረጃ ከሌለን በቀላሉ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንደምንችል የሚጠቁም አንድ ታሪክ እንመልከት። ስለ ደች አምባሳደርና ስለ ሳያም ንጉሥ የሚገልጸውን ይህን ታሪክ የተናገረው ጆን ሎክ (1632-1704) የተባለው ፈላስፋ ነው፤ የደች አምባሳደር በአገሩ በሆላንድ፣ ዝሆን በውኃ ላይ መሄድ የሚችልበት ወቅት እንዳለ ለንጉሡ ገለጸለት። ንጉሡ ይህን ሐሳብ ሊቀበለው አልፈለገም፤ እንዲያውም አምባሳደሩ እየዋሸው እንደሆነ ተሰማው። ይሁንና ንጉሡ ስለዚህ ጉዳይ የማያውቀው ነገር ስለነበረ እንጂ አምባሳደሩ እየዋሸ አልነበረም። ንጉሡ፣ ውኃ ወደ በረዶነት ሲቀየር በጣም ስለሚጠጥር ዝሆን እንኳ ሊሄድበት እንደሚችል አላወቀም። ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ስላልነበረው አምባሳደሩ የተናገረው ነገር ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ተሰምቶታል።

ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ፈጽሞ ሊሆኑ እንደማይችሉ ተደርገው ይታሰቡ የነበሩ አንዳንድ ዘመናዊ ክንውኖችን እንመልከት፦

● ከኒው ዮርክ የተነሳ አንድ አውሮፕላን ከ800 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ በሰዓት 900 ኪሎ ሜትር እየበረረ አንድም ጊዜ ሳያርፍ ሲንጋፖር መድረስ ይችላል።

● በተለያዩ አህጉራት የሚኖሩ ሰዎች በቪዲዮ አማካኝነት እየተያዩ መነጋገር ይችላሉ።

● አንድ የክብሪት ሣጥን የማታህል ትንሽ መሣሪያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዘፈኖችን መያዝ ትችላለች።

● የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ልብን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ማዘዋወር ይችላሉ።

ከእነዚህ እውነታዎች በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? የሰው ልጆች እንኳ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፈጽሞ የማይቻሉ የሚመስሉ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ከቻሉ፣ አጽናፈ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው አምላክ እኛ ሙሉ በሙሉ መረዳት ወይም በአሁኑ ጊዜ አስመስለን መሥራት የማንችላቸውን አስደናቂ ክንውኖች መፈጸም እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። *​—ዘፍጥረት 18:14፤ ማቴዎስ 19:26

የተቃውሞ ሐሳብ 2፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ተአምራትን የሚጠቅሰው ሰዎች እምነት እንዲያዳብሩ ለማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ተአምራት እንድናምን አያበረታታንም። እንዲያውም በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ በተአምራትና በታላላቅ ምልክቶች ላይ እምነት ከማሳደር ጋር በተያያዘ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። የሚከተለውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ልብ በል፦ “የዓመፀኛው መገኘት በሰይጣን አሠራር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ይህም የሚከናወነው በተአምራት፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሁሉ እንዲሁም ለማታለል ማንኛውንም ዓይነት የክፋት ዘዴ በመጠቀም ነው።”​—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10

ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙዎች የእሱ ተከታዮች እንደሆኑ ቢገልጹም እውነተኛ ተከታዮቹ እንዳልሆኑ ተናግሯል። እንዲያውም አንዳንዶች “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?” እንደሚሉት ገልጿል። (ማቴዎስ 7:22) እሱ ግን እነዚህን ሰዎች እንደ ተከታዮቹ አድርጎ እንደማይቀበላቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:23) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በአምላክ ኃይል የሚፈጸሙት ሁሉም ተአምራት እንዳልሆኑ ጠቁሟል።

አምላክ፣ አገልጋዮቹ በተአምራት ላይ ብቻ ተመሥርተው እምነት እንዲያዳብሩ አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ እምነታቸው በእውነታው ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።​—ዕብራውያን 11:1

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት በሰፊው የሚታወቁ ተአምራት አንዱን ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ተአምር ከተፈጸመ ከዓመታት በኋላ በቆሮንቶስ የሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞት ስለመነሳቱ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች የረዳቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የተጠራጠሩት እምነታቸው ስለተዳከመ እንደሆነ ነገራቸው? በፍጹም። በማስረጃ የተረጋገጡ እውነታዎችን መለስ ብለው እንዲያስተውሉ እንዴት እንደረዳቸው ልብ በል። ኢየሱስ እንደሞተና እንደተቀበረ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት በሦስተኛው ቀን ተነሳ፤ ለኬፋም ታየ፤ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ። በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ ሲሆን አብዛኞቹ እስካሁን በሕይወት አሉ።”​—1 ቆሮንቶስ 15:4-8

እነዚያ ክርስቲያኖች ይህ ተአምር መፈጸም አለመፈጸሙን ማመናቸው ያን ያህል የሚያሳስብ ነገር ነበር? ጳውሎስ “ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችንም ከንቱ ነው” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:14) ጳውሎስ ይህ ጉዳይ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ተሰምቶታል። ኢየሱስ ከሞት ስለመነሳቱ የሚገልጸው ዘገባ እውነት ወይም ሐሰት ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን የግድ አስፈላጊ ነው! ይህ ተአምር ሲፈጸም ያዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዓይን ምሥክሮች ሐዋርያው ዘገባውን ሲጽፍ በሕይወት ስለነበሩ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚገልጸው ዘገባ እውነተኛ መሆኑን እርግጠኛ ነበር። እንዲያውም እነዚህ የዓይን ምሥክሮች ይህን እውነት ከመካድ ሞትን ይመርጡ ነበር።​—1 ቆሮንቶስ 15:17-19

የተቃውሞ ሐሳብ 3ተአምራት ያልተማሩ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የተረዷቸው ተፈጥሯዊ ክስተቶች ናቸው። አንዳንድ ምሁራን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራት ያለ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የተፈጸሙ ተፈጥሯዊ ክንውኖች እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህ ዓይነቱ አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ዘገባዎች ይበልጥ ተአማኒ እንደሚያደርጋቸው ይሰማቸዋል። አንዳንድ ተአምራት እንደ መሬት መናወጥ፣ ቸነፈር እና መሬት መንሸራተት ካሉት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ቢችልም ከላይ ያለው አመለካከት ግምት ውስጥ ያላስገባው አንድ ነገር አለ። ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ተአምራት የተፈጸሙት ልክ በተፈለገው ጊዜ መሆኑን ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ግብፅን የመታው የመጀመሪያው መቅሰፍት ይኸውም የአባይ ወንዝ ወደ ደም መለወጡ ሊከሰት የቻለው ወንዙ ቀይ አፈር ይዞ በመምጣቱ እንዲሁም ፍላጀሌት የተባሉ ቀይ ቀለም ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ውኃው ውስጥ በመኖራቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ወንዙ ወደ ደም እንደተለወጠ እንጂ በቀይ አፈር እንደደፈረሰ አይናገርም። በ⁠ዘፀአት 7:14-21 ላይ ያለውን ዘገባ በጥንቃቄ ስናነብ ተአምሩ የተፈጸመው አሮን ሙሴ ባዘዘው መሠረት ልክ የአባይን ወንዝ በበትሩ ሲመታው እንደሆነ እንገነዘባለን። ወንዙ ወደ ደም የተለወጠው በተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆን እንኳ ይህ የሆነው ልክ አሮን ወኃውን ሲመታ መሆኑ በራሱ ተአምር ነው!

ተአምራቱ የተፈጸሙበትን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባቱ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው ሌላ ምሳሌ ደግሞ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት የተከሰተው ሁኔታ ነው። የዮርዳኖስ ወንዝ ጢም ብሎ ስለሞላ እስራኤላውያን መሻገር አይችሉም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የተከናወነውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ‘አዳም’ ተብላ እስከምትጠራው ሩቅ ከተማ ድረስ በመከማቸት እንደ ክምር ተቈለለ።” (ኢያሱ 3:15, 16) ይህ የሆነው በመሬት መናወጥ ወይም መንሸራተት ምክንያት ነው? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ክንውኑ የተፈጸመበትን ጊዜ ስናይ ተአምር መሆኑ ይገባናል። የዮርዳኖስ ወንዝ መፍሰሱን ያቆመው ልክ ይሖዋ ባለው ጊዜ ነው።​—ኢያሱ 3:7, 8, 13

እስካሁን ካየነው አንጻር በእርግጥ ተአምራት ሊፈጸሙ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ተአምራት እንደሚፈጸሙ ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት ተአምራት እንዲሁ ተፈጥሯዊ ክስተቶች አይደሉም። ይሁንና ተአምራት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናያቸው ክንውኖች ስላልሆኑ ብቻ ፈጽሞ ሊሆኑ አይችሉም ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 አምላክ መኖሩን የምትጠራጠር ከሆነ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? እና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባሉትን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ብሮሹሮች ተመልከት፤ ወይም ይህን መጽሔት ከሰጠህ የይሖዋ ምሥክር ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ብዙዎች በሰዓት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በአየር ላይ መጓዝ ለሰዎች ፈጽሞ የማይቻል ነገር እንደሆነ ይሰማቸው ነበር