በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

ወደ አምላክ ቅረብ

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

የይሖዋ አምላክን ማንነት በአንድ ቃል መግለጽ ቢያስፈልግህ የትኛውን ቃል ትመርጣለህ? በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የተወሰኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት የይሖዋን ማንነት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ቃል ተጠቅመው ሲያወድሱት በራእይ ተመልክቶ ነበር፤ የተጠቀሙበት ቃል “ቅዱስ” የሚል ነው። ኢሳይያስ ያየውና የሰማው ነገር የአድናቆት ስሜት እንዲሰማንና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል። በ⁠ኢሳይያስ 6:1-3 ላይ ያለውን ሐሳብ ስንመረምር አንተም በቦታው ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ።

ኢሳይያስ የተመለከተው ምንድን ነው? ይሖዋን “ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 1) ኢሳይያስ ሉዓላዊ ጌታ የሆነውን ይሖዋን በዓይኑ እየተመለከተ አልነበረም። ሥጋዊ ዓይን መንፈሳዊ አካላትን መመልከት አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 1:18) ከዚህ ይልቅ ኢሳይያስ ያየው ራእይ ነበር። * እንደዚያም ሆኖ ራእዩ በጣም እውን ስለነበረ ኢሳይያስ ይሖዋን ያየ ያህል በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተውጧል።

ከዚያም ኢሳይያስ ምናልባትም ማንም ሰው በራእይ አይቶት የማያውቀውን ነገር ተመለከተ። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሱራፌልም ከእርሱ [ከይሖዋ] በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፍ ነበራቸው። በሁለት ክንፍ ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግራቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበሩ ነበር።” (ቁጥር 2) ሱራፌል ከፍተኛ ቦታ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው። እነዚህን መንፈሳዊ ፍጡራን የጠቀሰው ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ኢሳይያስ ነው። ሱራፌል ይሖዋ የሚያዘውን ማንኛውንም ነገር ለመፈጸም ምንጊዜም ዝግጁዎች ናቸው። ፊታቸውንና እግራቸውን መሸፈናቸው አምላክን እንደሚያመልኩና እንደሚያከብሩ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ በፊቱ ሆነው እሱን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት የሚጠቁም ነው።

ኢሳይያስ በአድናቆት ስሜት እንዲዋጥ ያደረገው ያየው ነገር ብቻ ሳይሆን የሰማውም ነገር ነው። ሱራፌል በሰማይ እንዳለ የመዘምራን ቡድን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይዘምሩ ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንዳቸውም ለሌላው ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው። . . .’ ይሉ ነበር።” (ቁጥር 3 NW) “ቅዱስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ንጹሕና የጠራ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በተጨማሪም ቃሉ “ከኃጢአት ድርጊት ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆንን እንዲሁም መለየትን” ያመለክታል። ሱራፌል እርስ በርስ በመቀባበል በመዝሙራቸው ላይ “ቅዱስ” የሚለውን ቃል ሦስት ጊዜ መጥቀሳቸው ይሖዋ በቅድስናው አቻ የማይገኝለት ለመሆኑ አጽንኦት ለመስጠት አስችሏል። (ራእይ 4:8) እንግዲያው ቅድስና የይሖዋ ማንነት ዋነኛ መገለጫ ነው ሊባል ይችላል። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ የጠራ፣ ንጹሕና እንከን የማይገኝበት ነው።

ይሖዋ ቅዱስ መሆኑን ማወቃችን ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል። ለምን? በሙስና ሊዘፈቁ ከሚችሉትና ጨካኝ ከሆኑት ሰብዓዊ ገዥዎች በተለየ መልኩ ይሖዋ ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ የጸዳ ነው። በመሆኑም ይሖዋ ምንጊዜም ልንተማመንበት የምንችል አባት፣ ጻድቅ ገዥና የማያዳላ ዳኛ ሊሆን እንደሚችል ቅድስናው ዋስትና ይሰጠናል። አዎ፣ የማንነቱ ዋነኛ መገለጫ ቅድስና የሆነው አምላክ ለሐዘን የሚዳርገንን ነገር ፈጽሞ እንደማያደርግ ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችልበት በቂ ምክንያት አለን።

በታኅሣሥ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከኢሳይያስ 1 እስከ 23

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ነቅቶ እያለ አምላክ ራእይ ሲያሳየው ሁኔታውን በዓይኑ የሚመለከተው ያህል ሊመስለው ይችላል። ራእዩን የተመለከተው ሰው ከጊዜ በኋላ ያየውን ነገር ሊያስታውሰው፣ በራሱ አባባል ሊገልጸው ወይም ሊዘግበው ይችላል።”​—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ቅዱስ መሆኑን ማወቃችን ወደ እሱ እንድንቀርብ ሊያነሳሳን ይገባል