“ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው”

“ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው”

“ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው”

“አምላክ ፍቅር ነው።” በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ይህን ሐሳብ ጽፎ ግድግዳ ላይ መስቀል የተለመደ ነው። በእርግጥም ይህ የአምላክን ማንነት ይኸውም የፍቅር ተምሳሌት መሆኑን የሚገልጽ ግሩም ሐሳብ ነው።

ይሁንና ብዙ ሰዎች ይህ ሐሳብ የተወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ አያውቁም። “ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው” ብሎ የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ዮሐንስ ሊቤዥ የሚችለውን የሰው ዘር አስመልክቶም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”​—ዮሐንስ 3:16

አንዳንዶች ከእነዚህ ጥቅሶች አንጻር፣ አምላክ የምናደርገውን ነገር ሁሉ ምንጊዜም በቸልታ እንደሚያልፍ ይሰማቸው ይሆናል። የብዙዎች አኗኗር፣ ምንም አደረጉ ምን አምላክ ለሚፈጽሙት ነገር ተጠያቂ ያደርገናል ብለው እንደማያስቡ ያሳያል። ይሁንና ይህ እውነት ነው? አምላክ ጥሩም ሆነ መጥፎ ሰዎችን በሙሉ ይወዳል? አምላክ ሌሎችን የሚጠላበት ጊዜስ አለ?

የአምላክ ፍቅርና ጥላቻ

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ . . . ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 8) በዚህ ጥቅስ መሠረት፣ አምላክ እጅግ አፍቃሪና ደግ ቢሆንም የሚጠላበት ጊዜም አለ።

በመጀመሪያ ግን “መጥላት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራበት እንመልከት። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ‘መጥላት’ የሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። የማጥቃት ፍላጎት የታከለበትን ሥር የሰደደ የጠላትነት ስሜት ሊያመለክት ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ አንድ ሰው፣ የሚጠላውን ግለሰብ ለመጉዳት እንዲነሳሳ የሚገፋፋው ኃይለኛ ስሜት ሊሆን ይችላል።” ብዙዎቻችን “መጥላት” የሚለውን ቃል ስናስብ በአብዛኛው ወደ አእምሯችን የሚመጣው ይሄኛው ትርጉሙ ሲሆን የዚህ ዓይነት ጥላቻ ያስከተለውን መዘዝ በመላው ዓለም ማየት እንችላለን። ሆኖም ይኸው የማመሣከሪያ ጽሑፍ አክሎ እንዲህ ይላል፦ “‘መጥላት’ የሚለው ቃል አንድ ሰው፣ የሚጠላውን ግለሰብ የመጉዳት ዓላማ ባይኖረውም ግለሰቡን ጨርሶ እንደማይወደው ሊያመለክትም ይችላል።”

በዚህ ርዕስ ውስጥ የምናተኩረው በሁለተኛው ፍቺ ላይ ነው። እንዲህ ያለው ጥላቻ ምቀኝነትን፣ ክፋትን ወይም ሆን ብሎ ሌላውን የመጉዳት ፍላጎትን ሳይሆን አንድን ነገር በጣም መጸየፍንና መራቅን ያመለክታል። አምላክ እንዲህ ዓይነት ጥላቻ ሊያሳይ ይችላል? በ⁠ምሳሌ 6:16-19 ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ልብ በል፦ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦ ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።”

ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የሚጠላቸው አንዳንድ ድርጊቶች አሉ። ይህ ሲባል ግን እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን የፈጸመውን ግለሰብ ይጠላዋል ማለት ላይሆን ይችላል። ሰዎች እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ምክንያት ሊሆኗቸው የሚችሉ እንደ ሰብዓዊ ድክመት፣ አካባቢ፣ አስተዳደግ እንዲሁም አለማወቅ ያሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባል። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮም 5:12) የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ ይህን የሚያብራራ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሟል፤ “አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል” ብሏል። (ምሳሌ 3:12) አንድ ወላጅ የልጁን መጥፎ ምግባር ቢጠላም ልጁን ግን ይወደዋል፤ በመሆኑም ተገቢውን ተግሣጽ በመስጠት ልጁ መጥፎ ምግባሩን እንዲያስተካክል ለመርዳት የተቻለውን ያህል ይጥራል። ይሖዋም ሰዎችን ስለሚወድ አንድ ኃጢአተኛ መስተካከል የሚችል ከሆነ ግለሰቡን ለመርዳት ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል።

ጥላቻ ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ

ይሁንና አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ ቢያውቅም ተግባራዊ ለማድረግ አሻፈረኝ ቢልስ? ይህ ሰው የአምላክን ፍቅር አያገኝም፤ ከዚህ ይልቅ የእሱን ሞገስ ያጣል። ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ሆን ብሎ የሚፈጽም ከሆነ በዚህ አካሄዱ የተነሳ በአምላክ ዘንድ የተጠላ ይሆናል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች።” (መዝሙር 11:5) እንዲህ ያሉ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ምሕረት አያገኙም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደሚከተለው በማለት ይህን ግልጽ አድርጎታል፦ “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን ኃጢአት መሥራትን ልማድ ብናደርግ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ ምንም መሥዋዕት አይኖርም፤ ከዚህ ይልቅ በፍርሃት የሚጠበቅ ፍርድና አምላክን የሚቃወሙትን የሚበላ እሳታማ ቅናት ይኖራል።” (ዕብራውያን 10:26, 27) የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወስደው ለምንድን ነው?

አንድ ሰው ሆን ብሎ ከባድ ኃጢአት የመሥራት ልማድ ከተጠናወተው ክፋት በውስጡ ሥር ሊሰድና ከዚህ ምግባሩ መላቀቅ በጣም አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ግለሰቡ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ፣ ፈጽሞ የማይታረምና የማይስተካከል ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው፣ ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ከማይችል ነብር ጋር ያመሳስለዋል። (ኤርምያስ 13:23) ግለሰቡ ንስሐ ባለመግባቱ መጽሐፍ ቅዱስ “የዘላለም ኃጢአት” ብሎ የሚጠራውን ይቅር የማይባል ኃጢአት ይፈጽማል።

አዳምና ሔዋን እንዲሁም አስቆሮቱ ይሁዳ የዚህ ዓይነቱን ኃጢአት ፈጽመዋል። አዳምና ሔዋን ፍጹም ሆነው ስለተፈጠሩና አምላክ የሰጠውን የማያሻማ ትእዛዝ ሁለቱም በሚገባ ተረድተውት ስለነበር ኃጢአት የሠሩት ሆነ ብለው እንደሆነ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም ድርጊታቸው ይቅርታ የማይገባው ነው። አምላክም ቢሆን ንስሐ እንዲገቡ አልጠየቃቸውም። (ዘፍጥረት 3:16-24) ይሁዳ ፍጹም ባይሆንም እንኳ ከአምላክ ልጅ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው፤ እንደዚያም ሆኖ የአምላክን ልጅ ክዷል። ኢየሱስ ራሱ ይሁዳን ‘የጥፋት ልጅ’ በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 17:12) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለዘመናት በኃጢአት ጎዳና ሲመላለስ የኖረው ዲያብሎስም ሆን ብሎ ኃጢአት የመሥራት ልማድ እንደተጠናወተውና ዕጣው ጥፋት ብቻ እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:8፤ ራእይ 12:12) እነዚህ ሁሉ በአምላክ ዘንድ ጥላቻን አትርፈዋል።

ይሁን እንጂ ኃጢአት የሠራ ሁሉ አካሄዱን ማስተካከል አይችልም ማለት አይደለም፤ ይህን ማወቃችን የሚያጽናና ነው። ይሖዋ በጣም ታጋሽ ሲሆን ባለማወቅ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን መቅጣት አያስደስተውም። (ሕዝቅኤል 33:11) እነዚህ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና ምሕረት እንዲያገኙ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።”​—ኢሳይያስ 55:7

ለፍቅርና ለጥላቻ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን የሚመስሉ እንደመሆናቸው መጠን ‘ለመውደድም ሆነ ለመጥላት ጊዜ እንዳለው’ መገንዘብ አለባቸው። ስሜታዊ መሆን አንድ ሰው ለፍቅርና ለምሕረት ያለውን አመለካከት ሊያዛባበትና ሚዛናዊ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ የተናገረው ሐሳብ ምሕረት በማሳየትና ኃጢአትን በመጥላት ረገድ ሚዛናዊ መሆን እንድንችል ይረዳናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ለሌሎች ምሕረት ማሳየታችሁንም ቀጥሉ፤ ሆኖም ይህን ስታደርጉ ለራሳችሁ መጠንቀቅና በሥጋ ያደፈውን ልብሳቸውን መጥላት ይኖርባችኋል።” (ይሁዳ 22, 23) በመሆኑም መጥፎ የሆነውን መጥላት ቢኖርብንም መጥፎ ድርጊት የፈጸመውን ግለሰብ እንጠላዋለን ማለት አይደለም።

ክርስቲያኖች መልካም በማድረግ ለጠላቶቻቸው ፍቅር እንዲያሳዩም ታዝዘዋል። ኢየሱስ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:44) የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ሲሰብኩ አንዳንዶች ጥሩ ምላሽ ባይሰጧቸውም እንኳ አዘውትረው ከመስበክ ወደኋላ የማይሉት ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው ዓይነት አመለካከት በመያዝ እያንዳንዱን ሰው የይሖዋን ፍቅርና ምሕረት ማግኘት እንደሚችል አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎችን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ሰዎች በጎ ምላሽ በማይሰጡበት፣ በሚቃወሟቸው አልፎ ተርፎም በሚያሳድዷቸው ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን እንዲህ የሚለውን ምክር ይከተላሉ፦ “ስደት የሚያደርሱባችሁን መባረካችሁን ቀጥሉ፤ ባርኩ እንጂ አትርገሙ። . . . ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።” (ሮም 12:14, 17) ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ፍቅሩን የሚያሳያቸውና የሚጠላቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ የሚወስነው ራሱ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከሕይወትና ከሞት ጋር በተያያዘ የመጨረሻው ፈራጅ እሱ ነው።​—ዕብራውያን 10:30

በእርግጥም “አምላክ ፍቅር ነው።” እኛም የእሱን ፍቅር እንደምናደንቅ ማሳየት እንዲሁም ፈቃዱን ለማወቅና በተግባር ለማዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው የአምላክን ፈቃድ እንድታውቅ ሊረዱህ እንዲሁም ፈቃዱን በሕይወትህ ውስጥ እንዴት መፈጸም እንደምትችል ሊያሳውቁህ ፈቃደኞች ናቸው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የአምላክን ጥላቻ ሳይሆን ፍቅሩን ማትረፍ ትችላለህ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦ ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።”​—ምሳሌ 6:16-19

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን ኃጢአት መሥራትን ልማድ ብናደርግ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ ምንም መሥዋዕት አይኖርም፤ ከዚህ ይልቅ በፍርሃት የሚጠበቅ ፍርድ . . . ይኖራል።”​—ዕብራውያን 10:26, 27

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ . . . ይቅርታው ብዙ ነው።”​—ኢሳይያስ 55:7

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ልጁን ለመርዳት ሲል ተግሣጽ ይሰጠዋል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወኅኒ የሚገኙ ብዙዎች ከአምላክ ፍቅርና ምሕረት ተጠቅመዋል