በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮ አደጋ የማይኖርበት ጊዜ

የተፈጥሮ አደጋ የማይኖርበት ጊዜ

አንድ ሰው “አደጋ የማይኖርበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል” ቢልህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? “ይህማ የማይመስል ነው። አደጋ ሁሌም ያለ ነገር ነው” ትል ይሆናል። ወይም ደግሞ ‘ምን ይቀልዳል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

የተፈጥሮ አደጋዎች ሊቀሩ የሚችሉ ባይመስሉም እንደሚወገዱ የሚያረጋግጥ ተስፋ አለ። ይሁንና ይህን ለውጥ የሚያመጡት የሰው ልጆች አይደሉም። የሰው ልጆች በተፈጥሮ ውስጥ የሚከሰቱትን ነገሮች ሊቆጣጠሩ ወይም ሊያስወግዱ ይቅርና እነዚህ ነገሮች ለምንና እንዴት እንደሚከሰቱ እንኳ ሙሉ በሙሉ አያውቁም። በጥበቡና በአስተዋይነቱ የሚታወቀው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ማንም ሊያውቅ አይችልም፤ ሰው ለመመርመር ብዙ ቢጥርም፣ ትርጕሙን ማግኘት አይችልም፤ ጠቢብም እንኳ ዐውቀዋለሁ ቢል፣ ፈጽሞ ሊገነዘበው አይችልም።”—መክብብ 8:17

ታዲያ ሰዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን መቆጣጠር ካልቻሉ ይህን ሊያደርግ የሚችለው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማድረግ የሚችለው ፈጣሪያችን እንደሆነ ይናገራል። እንደ ውኃ ዑደት ያሉትን የምድርን ሥርዓቶች ያወጣው እሱ ነው። (መክብብ 1:7) ደግሞም ከሰዎች ፍጹም በተለየ ሁኔታ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይል አለው። ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሐቅ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።” (ኤርምያስ 32:17) ምድርንና የተፈጥሮ ኃይሎችን የፈጠረው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች በሰላምና በደኅንነት መኖር እንዲችሉ እነዚህን ኃይሎች እንዴት እንደሚቆጣጠር ማወቁ የሚያስገርም አይደለም።—መዝሙር 37:11፤ 115:16

ታዲያ አምላክ ይህን ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ በምድራችን ላይ እየተከሰቱ ያሉት በርካታ አስደንጋጭ ነገሮች “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” መድረሱን የሚያሳይ “ምልክት” እንደሆኑ በዚህ መጽሔት ሁለተኛው ርዕስ ላይ ተመልክተን ነበር። ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:3፤ ሉቃስ 21:31) የአምላክ መንግሥት ይኸውም በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መስተዳድር በምድር ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን የተፈጥሮ ኃይሎችን እንኳ ይቆጣጠራል። ይሖዋ አምላክ ይህን ለማድረግ ኃይሉ ቢኖረውም ይህን ሥራ ለልጁ ሰጥቶታል። ነቢዩ ዳንኤል ስለ አምላክ ልጅ ሲናገር “ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት” ብሏል።—ዳንኤል 7:14

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር አስደሳች ቦታ እንድትሆን ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ለውጦች ሁሉ ለማምጣት የሚያስችል ኃይል ተሰጥቶታል። ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችል በትንሹ አሳይቷል። በአንድ ወቅት እሱና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳለ “እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ፤ ማዕበሉም ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ በጣም ፈሩ። እንዳይሞቱ ስለሰጉ ኢየሱስን እንዲረዳቸው ጠየቁት። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? “ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም ‘ጸጥ በል! ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።” ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲያዩ በአድናቆት የተሞሉ ሲሆን “ለመሆኑ፣ ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።—ማርቆስ 4:37-41

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኢየሱስ ወደ መንፈሳዊው ዓለም የገባ ሲሆን ምድር ላይ ሳለ ከነበረው የበለጠ ኃይልና ሥልጣን ተሰጥቶታል። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች በምድር ላይ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖሩ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ለውጥ ለማምጣት ሥልጣኑም ሆነ ችሎታው አለው።

ይሁንና ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ለአብዛኞቹ ችግሮችና አደጋዎች መንስኤ የሆኑት ወይም የሚያባብሷቸው ስግብግብና ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ተግባሮች ናቸው። እንዲህ ዓይነት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አካሄድ የሚከተሉና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን የአምላክ መንግሥት ምን ያደርጋቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ” እንደሚመጣ ይናገራል፤ አክሎም “ከሰማይ የሚገለጠውም በሚንበለበል እሳት ነው፤ በዚያን ጊዜ አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል” ይላል። አዎ፣ ኢየሱስ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋቸዋል]።”—2 ተሰሎንቄ 1:7, 8፤ ራእይ 11:18

ከዚያም “የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራቸዋል። (ራእይ 19:16) የመንግሥቱ ተገዥዎች ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው ያደርጋል። በአየሩ ሁኔታና በወቅቶች መፈራረቅ ምክንያት የሰው ልጆች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙትን የተፈጥሮ ኃይሎች ይቆጣጠራል። በውጤቱም ይሖዋ አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት ለሕዝቡ የገባው ቃል ፍጻሜውን ያገኛል፤ ይሖዋ “ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህልዋን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ” ብሎ ነበር። (ዘሌዋውያን 26:4) ሰዎች ቤት ሲሠሩ በአደጋ ምክንያት አጣዋለሁ ብለው አይሰጉም፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ” ይላል።—ኢሳይያስ 65:21

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ አንተም የተፈጥሮ አደጋዎች የሌሉበት ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸው ተስፋ እንደሚያስደስትህ ጥርጥር የለውም። ታዲያ በዚህ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ‘አምላክን የማያውቁና ለምሥራቹ የማይታዘዙ’ ሰዎች ወደፊት በሚመጣው ከአደጋ ነፃ የሆነ ዓለም ውስጥ ለመኖር ብቁ አይደሉም፤ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ስለ አምላክ መማርና ምድርን ለመግዛት ያደረገውን ዝግጅት መደገፍ እንደሚኖርብህ ግልጽ ነው። አምላክ ስለ እሱ እንድናውቅና በልጁ አማካኝነት ስላቋቋመው መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች እንድንታዘዝ ይጠብቅብናል።

ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በሚኖረው ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቃት ይገልጻል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሩህ ለምን አትጠይቃቸውም? በዚህ ረገድ ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው። ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፦ ስለ አምላክ ለማወቅና ምሥራቹን ለመታዘዝ ጥረት የምታደርግ ከሆነ ምሳሌ 1:33 በአንተ ላይ ይፈጸማል። ጥቅሱ “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” ይላል።