በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ በየቀኑ እንዲያነጋግርህ ትፈልጋለህ?

አምላክ በየቀኑ እንዲያነጋግርህ ትፈልጋለህ?

መልክህን በመስታወት የምታየው ምን ያህል ጊዜ ነው? አብዛኞቻችን በየዕለቱ ምናልባትም በቀን ውስጥ ለተደጋጋሚ ጊዜ መስታወት ፊት እንቆም ይሆናል። እንዲህ የምናደርገው ለምንድን ነው? ውጫዊ ውበታችን ስለሚያሳስበን ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ራስን በመስታወት ትኩር ብሎ ከመመልከት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ያዕቆብ 1:23-25) በአምላክ ቃል ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው መልእክት ትክክለኛ ማንነታችንን እንድንረዳ የሚያስችለን ኃይል አለው። ይህ መልእክት “ነፍስንና መንፈስን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል።” (ዕብራውያን 4:12) በሌላ አባባል ከውጪ የሚታየው ማንነታችን ልባችን ውስጥ ካለው እውነተኛ ማንነታችን ተለይቶ እንዲታይ ያደርጋል። እንደ መስታወት ሁሉ የአምላክ ቃልም ማስተካከያ ማድረግ ያለብን የቱ ጋ እንደሆነ ይጠቁመናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገንን ቦታ መጠቆም ብቻ ሳይሆን ማስተካከያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነም ያስተምረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የአምላክ ቃል ከሚሰጠን አራት ጥቅሞች መካከል ሦስቱ ማለትም መገሠጽ፣ ነገሮችን ማቅናትና መምከር በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ የሚጠይቁ ናቸው። ውጫዊ ውበታችን የተስተካከለ መሆኑን ለማረጋገጥ አዘውትረን መስታወት መመልከት የሚያስፈልገን ከሆነ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም!

ይሖዋ አምላክ፣ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ ኢያሱን በሾመው ጊዜ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም።” (ኢያሱ 1:8) በእርግጥም ኢያሱ ስኬታማ መሆን ከፈለገ የአምላክን ቃል “ቀንም ሆነ ሌት” በሌላ አነጋገር አዘውትሮ ማንበብ ነበረበት።

በተመሳሳይም የመጀመሪያው መዝሙር፣ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበብ ያለውን ጥቅም እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ ሰው ብፁዕ ነው። ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” (መዝሙር 1:1-3) እኛም እንደዚህ ሰው መሆን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው።

በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ የዘወትር ልማዳቸው አድርገውታል። አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የሚያነበው ለምን እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ “በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ አምላክ ስጸልይ እንዲሰማኝ የምጠብቅ ከሆነ እኔስ ቃሉን በየዕለቱ በማንበብ አምላክን የማልሰማበት ምክንያት ምንድን ነው? ለአምላክ ጥሩ ወዳጅ መሆን የምንፈልግ ከሆነ እኛ ብቻ ተናጋሪዎች የምንሆንበት ምን ምክንያት አለ?” ይህ ክርስቲያን የተናገረው ሐሳብ ትክክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አምላክ ሲናገር የማዳመጥ ያህል ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በምናነብበት ጊዜ አምላክ ለነገሮች ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ ግንዛቤ እናገኛለን።

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማንበብ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ለማንበብ ፕሮግራም አውጥተህ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበኸዋል? መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ በውስጡ የያዘውን መልእክት ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። ይሁንና አንዳንዶች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ በተደደጋጋሚ ጊዜያት ቢሞክሩም በፕሮግራማቸው መቀጠል ያቅታቸዋል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ገጥሞሃል? ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ያወጣኸውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከዚህ በታች የተሰጡትን ሁለት ሐሳቦች በተግባር ለማዋል ለምን አትሞክርም?

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጊዜ መመደብ ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የዕለት ተዕለት ልማድህ አድርገው። በቀን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ተረጋግተህ እንድታነብ የሚያስችልህን ሰዓት ምረጥ። በተጨማሪም ሌላ አማራጭ ሰዓት መድብ። ይህም በሆነ ምክንያት በመረጥከው ሰዓት ላይ ማንበብ ሳትችል ብትቀር እንኳ በቀን ውስጥ የአምላክን ቃል ሳታነብ እንዳትቀር ይረዳሃል። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የጥንቶቹ የቤርያ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ እየተከተልክ ነው ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነሱ ሲነግረን እንዲህ ይላል፦ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።”—የሐዋርያት ሥራ 17:11

በግልጽ የተቀመጠ ግብ ይኑርህ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሦስት እስከ አምስት የሚደርሱ ምዕራፎችን በየቀኑ ብታነብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ። በቀጣዮቹ ገጾች ላይ የሚገኘው ሣጥን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ መጨረስ የምትችልበትን መንገድ ያሳይሃል። በዚህ ፕሮግራም ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እንድታደርግ እናበረታታሃለን። “ቀን” በሚለው ሥር በአንድ ጊዜ እንድታነባቸው የተመደቡትን ምዕራፎች መቼ እንደምታነብ ጻፍ። ምዕራፎቹን አንብበህ ስትጨርስ ከፊት ለፊቱ ባለው ሣጥን ውስጥ ምልክት አድርግ። ይህ ደግሞ እያደረግህ ያለውን እድገት እንድትከታተል ይረዳሃል።

ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጊዜ ብቻ አንብበህ ማቆም የለብህም። መጽሐፍ ቅዱስን በየዓመቱ ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ይህንኑ ፕሮግራም መጠቀም ትችላለህ፤ በየዓመቱ ከተለያዩ ክፍሎች መጀመርህ ንባብህን አስደሳች ያደርግልህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን ቀስ ብለህ ማንበብ ከፈለግህ በአንድ ጊዜ እንድታነባቸው የተመደቡትን ምዕራፎች በሁለት ወይም በሦስት ቀን ውስጥ ማንበብ ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብክ ቁጥር ከዚህ በፊት አስተውለኻቸው የማታውቃቸውን በሕይወትህ ውስጥ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን አዳዲስ ነገሮች ታገኛለህ። አዲስ ነገር ታገኛለህ እንድንል የሚያደርገን ምክንያት ምንድን ነው? “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ” በመሆኑና አኗኗራችንም ሆነ ያለንበት ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተለዋወጠ በመምጣቱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:31) በመሆኑም በመስታወት በተመሰለው የአምላክ ቃል ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ በየዕለቱ ራስህን ለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ በማድረግ አምላክ በየቀኑ እንዲያነጋግርህ እንደምትፈልግ ታሳያለህ።—መዝሙር 16:8