በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በኤፌሶን 2:11-15 ላይ አይሁዳውያንን ከአሕዛብ ስለሚለይ ግድግዳ ሲናገር በወቅቱ የነበረን ግድግዳ መጥቀሱ ነበር?

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ እስራኤላውያንን ‘ከባዕዳን’ ጋር በማነጻጸር ጽፏል። ይህ ሐዋርያ፣ እነዚህን ሁለት ቡድኖች ‘የሚለያይ ግድግዳ’ እንደነበር ገልጿል። (ኤፌሶን 2:11-15) እዚህ ላይ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው በሙሴ አማካኝነት ስለተሰጠው “ሕግ” የነበረ ቢሆንም “ግድግዳ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ አንባቢዎቹን በወቅቱ ስለነበረ የግንብ አጥር ሳያስታውሳቸው አልቀረም።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ የተፈቀደላቸው ሰዎች ብቻ የሚገቡባቸው በርካታ አደባባዮች ነበሩት። ማንኛውም ሰው ወደ አሕዛብ አደባባይ መግባት ይችል የነበረ ቢሆንም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወደሚገኙት አደባባዮች መግባት የሚችሉት ግን አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ማንኛውም ሰው መግባት የሚችልበትን አደባባይ አይሁዳውያን ብቻ ከሚገቡበት አደባባይ የሚለይ 1.3 ሜትር ገደማ ርዝመት እንዳለው የሚታመን ሶሬግ የተባለ የግንብ አጥር ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ እንደገለጸው ከሆነ አሕዛብ፣ ቅዱስ ወደሆነው ስፍራ እንዳይገቡ የሚያስጠነቅቁ በግሪክኛና በላቲንኛ የተጻፉ ጽሑፎች በዚህ አጥር ላይ ይገኙ ነበር።

በአጥሩ ላይ የተገኘ አንድ የግሪክኛ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ይህን ግድግዳ ወይም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለውን አጥር አልፎ መግባት አይኖርበትም። ገብቶ የተገኘ ማንኛውም ሰው ለሚደርስበት የሞት ቅጣት ተጠያቂው ራሱ ይሆናል።”

ጳውሎስ አይሁዳውያንን እና አሕዛብን ለረጅም ጊዜ ለያይቷቸው የቆየውን የሙሴን ሕግ ቃል ኪዳን ለማመልከት ሶሬግን እንደ ምሳሌ የተጠቀመበት ይመስላል። የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ሕጉን በማስወገድ ‘የሚለያየውን ግድግዳ አፍርሷል።’

የእስራኤል ነገዶች 13 ሆነው ሳለ መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ 12 እንደሆኑ አድርጎ የሚናገረው ለምንድን ነው?

የእስራኤል ነገዶች የተገኙት እስራኤል የሚል ስም ከተሰጠው ከያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነው። ይህ የእምነት አባት 12 ወንዶች ልጆች የነበሩት ሲሆን እነሱም ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድ፣ አሴር፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። (ዘፍጥረት 29:32 እስከ 30:24፤ 35:16-18) ከእነዚህ ወንድማማቾች መካከል አሥራ አንዱ በስማቸው የሚጠራ ነገድ የነበራቸው ቢሆንም ዮሴፍ ግን አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ሁለት ነገዶች የዮሴፍ ልጆች በሆኑት በኤፍሬምና በምናሴ ስም ተጠርተዋል፤ ኤፍሬምም ሆነ ምናሴ የነገድ አለቆች ተደርገው ይታዩ ነበር። በመሆኑም የእስራኤል ነገዶች በጠቅላላው 13 ነበሩ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ የእስራኤል ነገዶች 12 እንደሆኑ አድርጎ የሚናገረው ለምንድን ነው?

ከእስራኤላውያን መካከል የሌዊ ነገድ የሆኑ ወንዶች፣ መጀመሪያ ላይ በይሖዋ የመገናኛ ድንኳን በኋላ ላይ ደግሞ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያገለግሉ ተመርጠው ነበር። በመሆኑም ሌዋውያን ለውትድርና አገልግሎት አይመለመሉም ነበር። ይሖዋ ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር:- “የሌዊን ነገድ አትቍጠር፤ በእስራኤላውያንም ቈጠራ ውስጥ አታስገባው፤ በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በምስክሩ ማደሪያ፣ በውስጡ ባሉት በመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዙ በማናቸውም ነገሮች ላይ ኀላፊዎች ይሁኑ።”—ዘኍልቍ 1:49, 50

በተጨማሪም ሌዋውያን በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የራሳቸው ርስት አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ በመላው እስራኤል በሚገኙ 48 ከተሞች ውስጥ እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር።—ዘኍልቍ 18:20-24፤ ኢያሱ 21:41

በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ የሌዊ ነገድ በሌሎቹ ነገዶች ዝርዝር ውስጥ አይካተትም ነበር። በመሆኑም የእስራኤል ነገዶች አብዛኛውን ጊዜ 12 ተደርገው ይገለጻሉ።—ዘኍልቍ 1:1-15

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Archaeological Museum of Istanbul