በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በብሔራት መካከልም ሆነ እርስ በርስ በሚደረጉ ጦርነቶች እንደማይካፈሉ የሚያሳይ የረጅም ዘመን ታሪክ አላቸው። “የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት ጊዜ ፈጽሞ የማያወላውል የገለልተኝነት አቋም ይይዛሉ” በማለት አውስትራሊያን ኢንሳይክሎፒዲያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ገልጾ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት እንዳይካፈሉ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከእነዚህ አንዱ እንዲህ ባሉ ግጭቶች ውስጥ እጃቸውን ማስገባታቸው ክርስቲያናዊ ሕሊናቸውን የሚያቆሽሽባቸው መሆኑ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትእዛዝና በተወው ምሳሌ ሕሊናቸውን አሠልጥነዋል። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ሰዎችን እንዲወዱ አዟል። በተጨማሪም “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ” በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል። (ሉቃስ 6:27፤ ማቴዎስ 22:39) ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስን ለመያዝ የመጡትን ሰዎች በሰይፍ ለመከላከል ሲሞክር ኢየሱስ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎታል። (ማቴዎስ 26:52) በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ በጦር መሣሪያ መጠቀም እንደማይገባቸው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ በግልጽ አሳይቷል።

የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት የማይካፈሉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የዓለም አቀፉ የወንድማማች ኅብረት አባላት በመሆናቸው ነው። ጦርነት፣ አንድ ሰው ከወንድሙ ጋር እንዲጋጭ ያደርገዋል፤ ይህ ደግሞ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘እርስ በርስ እንዲዋደዱ’ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር ይቃረናል።—ዮሐንስ 13:35

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፍቅርን በተመለከተ የተሰጡትን ከላይ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅ ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸውም ጭምር ተግባራዊ ያደርጓቸዋል። ከ1939 እስከ 1945 በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የወሰዱትን አቋም እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ፣ ከ4,300 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት አንካፈልም በማለታቸው በፌዴራል ወኅኒ ቤት ታስረዋል። በብሪታንያ፣ ከ300 በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ጨምሮ ከ1,500 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ከጦርነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ግዴታዎችን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እስር ቤት ገብተዋል። በናዚ ጀርመን ከ270 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አንዋጋም በማለታቸው በመንግሥት ትእዛዝ ተገድለዋል። በናዚ አገዛዝ ወቅት ከ10,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በወኅኒ ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተጥለዋል። በጃፓን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ከባድ መከራ ደርሶባቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተነሳ በየትኛውም ጦርነት የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሁሉ፣ አንድም የይሖዋ ምሥክር ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂ እንደማይሆን እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

ቮልፍጋንግ ኩሰሮ የተባለ ወጣት ከመገደሉ በፊት የተናገረው ሐሳብ የይሖዋ ምሥክሮች ለጦርነት ያላቸውን አመለካከት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። በ1942 ናዚዎች ይህ የ20 ዓመት ጀርመናዊ ወጣት ወደ ጦርነት አልሄድም በማለቱ አንገቱን ቀልተውታል። (ኢሳይያስ 2:4) ቮልፍጋንግ፣ በወታደራዊ ችሎት ፊት በቀረበበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር:- “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን የአምላክ ሕግ ተምሬ ያደግሁ የይሖዋ ምሥክር ነኝ። አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ሕግጋት ሁሉ የሚበልጠውና እጅግ ቅዱስ የሆነው ሕግ ‘አምላክህን ከምንም ነገር በላይ አስበልጠህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው። ሌላው ትእዛዝ ደግሞ ‘አትግደል’ ይላል። ታዲያ ፈጣሪያችን ይህን ሁሉ ያስጻፈው ለዛፎች ይመስላችኋል?”—ማርቆስ 12:29-31፤ ዘፀአት 20:13

የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ላይ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር [እንደሚያስወግድ]” የገባውን ቃል የሚፈጽምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።—መዝሙር 46:9