በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ የሐዋርያት

‘እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ የሐዋርያት

ወደ አምላክ ቅረብ

‘እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ የሐዋርያት

ሥራ 17:24-27

የሰው ልጆች ግዙፍ ከሆነው ከዚህ ጽንፈ ዓለም ጋር ሲወዳደሩ ኢምንት ናቸው። ‘እዚህ ግቡ የማይባሉት የሰው ልጆች ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር በእርግጥ የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ?’ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል። ይህ ሊሆን የሚችለው፣ ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ ከፈለገ ብቻ ነው። ታዲያ አምላክ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አለው? የዚህ ጥያቄ መልስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና ለነበሩ የተማሩ ሰዎች በተናገረው ልብ የሚነካ ሐሳብ ላይ ይገኛል፤ ይህ ሐሳብ በሐዋርያት ሥራ 17:24-27 ላይ ሰፍሯል። ጳውሎስ፣ እዚህ ላይ ስለ ይሖዋ የጠቀሳቸውን አራት ነጥቦች ልብ በል።

አንደኛ፣ አምላክ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ [እንደፈጠረ]” ጳውሎስ ተናግሯል። (ቁጥር 24) ሕይወት አስደሳች እንዲሆን ያደረጉት ውበት የተላበሱ ልዩ ልዩ ፍጥረታት፣ ሠሪያችን አሳቢና አፍቃሪ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣሉ። (ሮሜ 1:20) በመሆኑም አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ከፈጠራቸው የሰው ልጆች ጋር መቀራረብ አይፈልግም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

ሁለተኛ፣ ይሖዋ “ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ [ሰጥቷል]።” (ቁጥር 25) ይሖዋ በሕይወት እንድንቀጥል የሚያስችሉንን ነገሮች ሁሉ የሚሰጥ አምላክ ነው። (መዝሙር 36:9) ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑት አየር፣ ውኃና ምግብ ከፈጣሪያችን ያገኘናቸው ስጦታዎች ናቸው። (ያዕቆብ 1:17) ታዲያ ለጋስ የሆነው አምላካችን ሰዎች እንዳያውቁትና እንዳይቀርቡት ሲል ራሱን ያገላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

ሦስተኛ፣ አምላክ “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው [ፈጥሯል]።” (ቁጥር 26 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ አድልዎ የማያደርግ ከመሆኑም በላይ ለሰዎችም ጭፍን ጥላቻ የለውም። (የሐዋርያት ሥራ 10:34) ይሖዋ እንዲህ ያለ ባሕርይ ያለው አምላክ አይደለም። ሁሉም የሰው ዘር የተገኘው አምላክ ከፈጠረው “አንድ ሰው” ማለትም ከአዳም ነው። የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) በመሆኑም የቆዳችን ቀለም፣ ዜግነታችን ወይም ዘራችን ምንም ይሁን ምን ወደ አምላክ የመቅረብ አጋጣሚ ተከፍቶልናል።

በመጨረሻም ጳውሎስ በጣም የሚያበረታታ ሐሳብ ተናገረ፤ ‘[ይሖዋ] ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ ብሏል። (ቁጥር 27) ይሖዋ ላቅ ያለ ቦታ ቢኖረውም ወደ እሱ የመቅረብ ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሁሉ በማንኛውም ጊዜ ሊቀርቡት ይችላሉ። አምላክ ከእኛ የራቀ እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ “ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ” መሆኑን ቃሉ ያረጋግጥልናል።—መዝሙር 145:18

ጳውሎስ ከተናገረው ሐሳብ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ አምላክ ወደ እሱ እንዲቀርቡ አጋጣሚውን የሚሰጠው እሱን ‘ለመፈለግ’ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል። (ቁጥር 27) ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ‘[መፈለግ] ተብሎ የተተረጎመው ግሥ፣ ሊሳካ የሚችል ምኞትን እንደሚያመለክት’ ገልጿል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ የምታውቀው ቤት ውስጥ በጨለማ ገባህ እንበል። የቤቱን ማብሪያ ማጥፊያ ወይም በር ለማግኘት መፈለግ ይኖርብህ ይሆናል፤ እንደምታገኘው ግን ምንም አትጠራጠርም። በተመሳሳይም አምላክን ከልባችን የምንፈልግ ከሆነ ጥረታችን እንደሚሳካ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ጳውሎስ፣ አምላክን በእርግጥ ‘እንደምናገኘው’ ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ቁጥር 27

ታዲያ ወደ አምላክ ለመቅረብ ትፈልጋለህ? አምላክን እንደምታገኘው በመተማመን እሱን ‘መፈለግ’ ብትጀምር ጥረትህ መና ሆኖ እንደማይቀር እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ ስላልሆነ’ ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት አስቸጋሪ አይደለም።