በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ብራዚል

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ብራዚል

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ሩብያ የተባለች አንዲት እህት (አሁን 30 ዓመቷ ነው) ሳንድራ የተባለችን በደቡባዊ ብራዚል በሚገኝ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት የምታገለግል እህት ለመጠየቅ ሄዳ ነበር። ሩብያ እዚያ እያለች ያጋጠማት ነገር በጥልቅ ስለነካት አኗኗሯን ለመቀየር ተነሳሳች። ያጋጠማት ነገር ምን ነበር? እስቲ እሷ ራሷ የምትለንን እንስማ።

“ጆሮዬን ማመን አቃተኝ”

“ሳንድራ መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናት አንዲት ሴት ጋ አብረን ሄድን። እያጠናን እያለ ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ ‘ሳንድራ፣ አብረውኝ የሚሠሩ ሦስት ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይፈልጋሉ፤ ሆኖም በዚህ ዓመት ፕሮግራምሽ በጣም የተጣበበ እንደሆነ ስለማውቅ ተራቸው እስኪደርስ መጠበቅ እንዳለባቸው ነግሬያቸዋለሁ።’ ይህን ስሰማ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ። ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ተራቸው እስኪደርስ መጠበቅ ነበረባቸው! እኔ ባለሁበት ጉባኤ አንድ ጥናት እንኳ ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረግ አስፈልጎኛል። በዚያች ቅጽበት፣ በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የመርዳት ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የምኖርበትን ትልቅ ከተማ ለቅቄ ሳንድራ በአቅኚነት ወደምታገለግልበት ከተማ መጣሁ።”

ታዲያ ሩብያ ምን አጋጥሟት ይሆን? እንዲህ ብላለች፦ “ወደዚያ በተዛወርኩ በሁለት ወራት ውስጥ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመርኩ። ነገሩ እውነት ባይመስልም፣ ብዙም ሳይቆይ እኔም እንደ ሳንድራ ፕሮግራሜ በመጣበቡ ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ተራ እስኪደርሳቸው እንዲጠብቁ ማድረግ ነበረብኝ!”

አገልግሎቱን መለስ ብሎ እንዲቃኝ አነሳሳው

በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ድዬጎ ፕሩዴንቶፑሊስ በተባለች በደቡባዊ ብራዚል የምትገኝ አነስተኛ ከተማ የሚያገለግሉ የተወሰኑ አቅኚዎችን ለመጠየቅ ሄዶ ነበር። ድዬጎ በዚያ ያሳለፈውን ጊዜ ፈጽሞ አይረሳውም፤ የተመለከተው ነገር አገልግሎቱን መለስ ብሎ እንዲቃኝ አነሳሳው። እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት በየወሩ ጥቂት ሰዓታት ከማሳለፍ ውጪ በጉባኤዬ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ አላደርግም ነበር። ከእነዚህ አቅኚዎች ጋር ጊዜ ማሳለፌ እንዲሁም ተሞክሯቸውን መስማቴ እነሱ በአገልግሎታቸው ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ እንድገነዘብ አደረገኝ፤ በሌላ በኩል ግን እኔ ለአገልግሎት ያን ያህል ቅንዓት እንደሌለኝ ተሰማኝ። አቅኚዎቹ ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ስመለከት እኔም እንደ እነሱ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ተመኘሁ።” ድዬጎ እነዚያን አቅኚዎች ጠይቆ ከተመለሰ በኋላ እሱም አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።

አንተም እንደ ድዬጎ በስብከቱ ሥራ የምትካፈል እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምትገኝ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ብትሆንም አገልግሎት እንዲሁ በዘልማድ የምታከናውነው አሰልቺ ሥራ ሆኖብሃል? ከሆነ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም እንድትችል በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ? በእርግጥ፣ የተደላደለ ኑሮህን ትተህ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አስቸጋሪ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶች ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ በግቦቻቸውና በሚፈልጓቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው ማገልገል ችለዋል። ከእነዚህ መካከል እስቲ የብሩኖን ምሳሌ እንመልከት።

የሙዚቃ ባለሙያ ወይስ አገልጋይ?

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ብሩኖ (አሁን 28 ዓመቱ ነው) በአንድ ታዋቂ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እየተማረ ነበር፤ የኦርኬስትራ ሙዚቃ መሪ የመሆን ግብ ነበረው። እንዲያውም በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ስላገኘ የኦርኬስትራ ሙዚቃ እንዲመራ በተለያዩ ወቅቶች ይጋበዝ ነበር። የተዋጣለት የሙዚቃ ባለሙያ የመሆን አጋጣሚ ከፊቱ ተዘርግቶለት ነበር። “ያም ቢሆን በሕይወቴ ውስጥ የሆነ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር” ይላል ብሩኖ። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሕይወቴን ለይሖዋ ብወስንም ራሴን ሙሉ በሙሉ ለእሱ እንዳልሰጠሁ አውቅ ነበር፤ ይህም ውስጤን ይረብሸኝ ነበር። ይህን ስሜቴን አውጥቼ ለይሖዋ ነገርኩት፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችን አነጋገርኩ። ጉዳዩን በቁም ነገር ካሰብኩበት በኋላ አገልግሎቴን ከሙዚቃ ለማስቀደም ወሰንኩ፤ በመሆኑም ከሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ወጣሁና የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውሬ ማገልገል ጀመርኩ።” ብሩኖ ምን አጋጥሞት ይሆን?

ብሩኖ ከሳኦ ፓውሎ ከተማ 260 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኝ ግዋፒያራ የተባለች ትንሽ ከተማ (7,000 ገደማ ነዋሪዎች አሏት) ተዛወረ። ይህ ትልቅ ለውጥ ማድረግ የሚጠይቅ ነበር። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “በምኖርባት ትንሽ ቤት ውስጥ ማቀዝቀዣ፣ ቴሌቪዥንም ሆነ ኢንተርኔት የለም። ያም ሆኖ በዚህ ቤት በመኖሬ ከዚያ በፊት ያልነበሩኝን ነገሮች ይኸውም በግቢዬ ውስጥ የጓሮ አትክልት የማለማበት መሬትና የፍራፍሬ ዛፎች ያሉበት የአትክልት ቦታ አገኘሁ!” ብሩኖ በዚያ አካባቢ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ የሚያገለግል ሲሆን በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ ምግብ፣ ውኃና ጽሑፎች በቦርሳው ይዞ ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ለመስበክ በሞተር ብስክሌት ይሄዳል። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን ጨርሶ ሰምተው አያውቁም። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “18 ጥናቶች ነበሩኝ። እነዚህ ጥናቶቼ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ሲያደርጉ መመልከቴ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል!” አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በሕይወቴ ውስጥ እንደጎደለኝ ይሰማኝ የነበረውን ነገር እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ፤ ይህም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደም የሚያስገኘው ጥልቅ የእርካታ ስሜት ነው። በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት ብመራ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱን እርካታ ፈጽሞ ማግኘት አልችልም ነበር።” ብሩኖ ‘ታዲያ በምን ትተዳደራለህ?’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ፈገግ ብሎ “ጊታር አስተምራለሁ” በማለት መለሰ። ብሩኖ አሁንም ቢሆን የሙዚቃ ባለሙያ ነው ማለት ይቻላል።

“የግድ እዚያ መቆየት ነበረብኝ”

በ20ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የምትገኘው ማሪያና የነበረችበት ሁኔታ ከብሩኖ ጋር ተመሳሳይ ነው። ጠበቃ የነበረች ሲሆን ዳጎስ ያለ ደሞዝ ታገኝ ነበር፤ ያም ቢሆን እርካታ አልነበራትም። ማሪያና “ሕይወቴ ‘ነፋስን እንደ መከተል’ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። (መክ. 1:17) በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ማሪያናን አቅኚ እንድትሆን አበረታቷት። እሷም ጉዳዩን በጥሞና ካሰበችበት በኋላ ቢያንካካሮሊን እና ጁሊያና ከተባሉ ጓደኞቿ ጋር ሆና ባራ ዱ ቡግሬስ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጉባኤ ለማገልገል ወሰኑ። በቦሊቪያ አቅራቢያ ያለችው ይህች ከተማ የምትገኘው ከሚኖሩበት አካባቢ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ነው። ታዲያ ማሪያና ምን አጋጠማት?

እንዲህ ብላለች፦ “ወደዚያ ስሄድ ያሰብኩት ሦስት ወር ለመቆየት ነበር። ሆኖም ያሰብኩት ጊዜ ሲያልቅ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየመራሁ ነበር! ጥናቶቼ በእውነት ውስጥ እድገት እንዲያደርጉ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም አካባቢውን ለቅቄ ልሄድ እንደሆነ ለጥናቶቼ ለመናገር ድፍረት አጣሁ። የግድ እዚያ መቆየት ነበረብኝ።” ሌሎቹ ሦስት እህቶችም ተመሳሳይ ውሳኔ አደረጉ። ታዲያ ማሪያና ያደረገችው ውሳኔ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ አስችሏታል? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ በእኔ እንደሚጠቀም ማወቄ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርብኛል። ጊዜዬንና ጉልበቴን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሥራ ለማከናወን ማዋሌ ትልቅ በረከት እንደሆነ ይሰማኛል።” ካሮሊን የተናገረችው የሚከተለው ሐሳብ የአራቱን እህቶች ስሜት ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል፦ “ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም የምችለውን ያህል እያደረግሁ ስለሆነ ማታ ወደ መኝታዬ ስሄድ በውስጤ ጥልቅ እርካታ ይሰማኛል። ትኩረቴ በሙሉ ያረፈው ጥናቶቼን መርዳት በምችልበት መንገድ ላይ ነው። ጥናቶቼ እድገት ሲያደርጉ መመልከት ልዩ ስሜት ይፈጥራል። ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ’ የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት በራሴ ሕይወት ተመልክቻለሁ።”—መዝ. 34:8

ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወጣት ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱን ምሥራች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለመስበክ ራሳቸውን ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ሲያቀርቡ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (መዝ. 110:3፤ ምሳሌ 27:11) እነዚህ ፈቃደኛ አገልጋዮች በሙሉ የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ።—ምሳሌ 10:22