በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን፣ የይሖዋ ምሥክር ባልሆነ ዘመዱ ወይም በሚያውቀው ሰው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘቱ ተገቢ ነው?

ሠርግ አስደሳች ወቅት እንደመሆኑ መጠን አንድ ክርስቲያን በጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት መፈለጉ አያስደንቅም። እርግጥ ነው፣ በሠርጉ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ስለ እነሱ የመጨረሻውን ውሳኔ የማሳለፍ መብት ያላቸው ወላጆቻቸውን ወይም አሳዳጊዎቻቸውን መታዘዝ አለባቸው። (ኤፌሶን 6:1-3) ይሁንና የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሰው ክርስቲያን የሆነች ሚስቱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚፈጸም የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ አብራው እንድትገኝ ቢጠይቃትስ? ሚስትየው፣ ከጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ጋር በሚያያዙ በማንኛውም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ሳትካፈል እንዲሁ በተመልካችነት በሥፍራው ለመገኘት ሕሊናዋ ሊፈቅድላት ይችላል።

በመሠረቱ፣ በአንድ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ወይም አለመገኘት ለግል ውሳኔ የተተወ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያደርገው ምርጫ በይሖዋ ፊት እንደሚያስጠይቀው መዘንጋት የለበትም። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ክርስቲያን እምነቱን በማይጋሩ ሰዎች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ከመወሰኑ በፊት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመርመር ይኖርበታል።

አንድ ክርስቲያን የአምላክን ሞገስ ማግኘትን ከሁሉም በላይ ከፍ አድርጎ ሊመለከተው ይገባል። ኢየሱስ “[አምላክ] መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሃይማኖቶች በሚያከናውኗቸው እንደ ጸሎት ባሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጋጩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ አይካፈሉም።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17

አንድ ክርስቲያን የሚያደርገው ውሳኔ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ማስታወስ ይኖርበታል። በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ብትወስን፣ በሁሉም ዝግጅቶች ላይ አለመሳተፍህ ዘመዶችህን ቅር ያሰኛቸው ይሆን? ውሳኔህ በእምነት አጋሮችህ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖም ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። (ሮሜ 14:13) አንተም ሆንክ ቤተሰብህ የይሖዋ ምሥክር ባልሆነ ሰው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታችሁ ችግር እንደማይፈጥርባችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ያደረጋችሁት ውሳኔ በመንፈሳዊ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን? የአንዳንዶችን ሕሊናስ ይጎዳ ይሆን?

የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ዘመዶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። ሚዜ እንድትሆኑ ብትጠየቁስ? ወይም ደግሞ የትዳር ጓደኛችሁ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንና በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሚካሄዱት በሁሉም ዝግጅቶች ውስጥ እንድትካፈሉ ቢፈልግስ? ጋብቻው የሚከናወነው በማዘጋጃ ቤት ወይም ከመንግሥት ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት ከሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት የዓይን ምሥክር ከመሆን ያለፈ ነገር ማድረግን አይጠይቅ ይሆናል።

በሌላ በኩል፣ የጋብቻው ሥነ ሥርዓት የሚፈጸመው በአንድ ሃይማኖታዊ ሕንጻ ውስጥ ወይም በአንድ ቄስ አማካኝነት ከሆነ ልናስብባቸው የሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ይኖራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናህ የሚነግርህን ለመታዘዝና እምነትህን እንድታላላ ከሚያደርግህ ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ስትል አሊያም ሙሽሮቹን ወይም ቤተሰቦቻቸውን ቅር ላለማሰኘት በማሰብ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ላለመገኘት ትወስን ይሆናል። (ምሳሌ 22:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነታችሁን አስቀድመህ በመግለጽ ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን አላስፈላጊ ከሆነ ጭንቀት መጠበቅ ትችላለህ። በዚህ ወቅት በጋብቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ የምትሆኑት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ መግለጽ ወይም ሌላ አማራጭ መንገድ ካለ መጠቆም ይጠበቅብህ ይሆናል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ሳይካፈሉ የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ሰዎች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ምንም ስህተት የለውም ብለው ይወስኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን በጋብቻው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘቱ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲጥስ የሚፈትነው ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ሊያስብ ይችላል። ይህ ክርስቲያን በጋብቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ሳይሆን ከዚያ በኋላ በሚደረገው የሠርግ ግብዣ ላይ ለመገኘት ከወሰነ ‘ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር ለማድረግ’ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለበት። (1 ቆሮንቶስ 10:31) እነዚህን ዓይነት ውሳኔዎች በማድረግ ረገድ “እያንዳንዱ የራሱን [የኃላፊነት] ሸክም ሊሸከም ይገባዋል።” (ገላትያ 6:5) በመሆኑም ውሳኔህ ምንም ይሁን ምን በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና መያዝ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አትዘንጋ።