በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል የሆነውን ለማድረግ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

ትክክል የሆነውን ለማድረግ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

ትክክል የሆነውን ለማድረግ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

አንድ የተማረ ሰው “በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም። የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። ይህ ሰው የሚመኘውን በጎ ነገር ማድረግ አስቸጋሪ የሆነበት ለምንድን ነው? ይህ የሆነበትን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “ስለዚህ ይህ ሕግ እየሠራ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ፤ ይኸውም በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ። በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ።”—ሮሜ 7:18, 19, 21-23

ከተመዘገቡ ወደ 2,000 ዓመታት ገደማ የሆናቸው እነዚህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት፣ ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ተፈታታኝ የሆነበትን ምክንያት ይጠቁማሉ። በተለይ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ወቅት ትክክለኛ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሙጥኝ ማለት ጠንካራ ሥነ ምግባራዊ አቋም መያዝን ይጠይቃል። ስለዚህ ‘ትክክል የሆነውን ነገር የምናደርግበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

በሥነ ምግባር ረገድ ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው የወደፊት ዕጣው ምን እንደሚሆን ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩትን ተመልከት። መዝሙር 37:37, 38 “ንጹሐንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና። ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤ የክፉዎችም ዘር ይወገዳል” ይላል። እንዲሁም ምሳሌ 2:21, 22 “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ” በማለት ይነግረናል።

እነዚህና ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ተስፋዎች አምላክን የሚያስደስት አካሄድ እንድንከተል የሚያነሳሱን ቢሆንም እንዲህ የምናደርግበት መሠረታዊ ምክንያት ግን ይህ አይደለም። ይህ መሠረታዊ ምክንያት ሁሉንም አስተዋይ ፍጡራን በግለሰብ ደረጃ ከሚመለከት አንድ አከራካሪ ጉዳይ ጋር የሚዛመድ ነው። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የዚህን አከራካሪ ጉዳይ ምንነትና ሁላችንንም የሚነካን እንዴት እንደሆነ ያብራራል።