በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በድፍረት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት

በድፍረት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

በድፍረት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት

ሕዝቡ አንድን ታዛዥ የአምላክ አገልጋይ ደብድቦ ለመግደል በቁጣ ገንፍሎ ወጥቷል። ልክ በዚህ ጊዜ የሮማ ወታደሮች ሰውየውን ከሕዝብ መሃል ነጥቀው በማውጣት በቁጥጥር ሥር አዋሉት። ይህን ተከትለው የተከሰቱት ሁኔታዎች ለአምስት ዓመታት ዘለቁ። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቦታ ያላቸው በርካታ የሮም ባለ ሥልጣናት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስማት ችለዋል።

እንዲህ ያለው መከራ የደረሰበት ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። በ34 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ኢየሱስ፣ ጳውሎስ (ሳውል) የእርሱን ስም “በነገሥታት ፊት” እንደሚሸከም ተናግሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:15) ሆኖም ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሁኔታ በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላም ገና አልተፈጸመም ነበር። ሐዋርያው ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ወደማጠናቀቁ ሲቃረብ ግን ሁኔታዎች ተለዋወጡ።

ሕዝቡ ቢያምጽበትም ወደኋላ አላለም

ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ባለበት ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖች “በመንፈስ” ተነሳስተው በሚሄድበት ከተማ ኃይለኛ ስደት እንደሚጠብቀው አስጠነቀቁት። እርሱ ግን በድፍረት “እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳን ዝግጁ ነኝ” በማለት መለሰላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 21:4-14) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ እንደደረሰ፣ በእስያ ሳለ በወንጌሉ ስብከት ሥራ ያገኘውን ስኬት የሚያውቁ ከዚያው የመጡ አይሁዳውያን እርሱን ለመግደል ሕዝቡን አነሳሱ። በዚህ ጊዜ የሮም ወታደሮች በፍጥነት መጥተው ረዱት። (የሐዋርያት ሥራ 21:27-32) ይህ ሁኔታ፣ ጳውሎስ ለተቃዋሚዎችና ለከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት ለማወጅ የሚያስችል ልዩ የሆነ አጋጣሚ እንዲያገኝ አደረገው።

በቀላሉ ለማይገኙ ሰዎች መስበክ

ወታደሮቹ፣ ለደኅንነቱ ሲሉ ጳውሎስን የአንቶኒያ ግንብ ተብሎ ወደሚጠራው ምሽግ አወጡት። a ከዚያም ሐዋርያው በምሽጉ ደረጃዎች ላይ ቆሞ በቁጣ ለገነፈለው ሕዝብ ጠንከር ያለ ምሥክርነት ሰጠ። (የሐዋርያት ሥራ 21:33 እስከ 22:21) ሆኖም ለአሕዛብ እንዲሰብክ የተላከ መሆኑን ሲናገር በድጋሚ ረብሻው ተቀሰቀሰ። ሉስዮስ የሚባለው የጦር አዛዥ፣ አይሁድ በጳውሎስ ላይ እንዲህ የሚጮኹበትን ምክንያት ለማወቅ እየተገረፈ እንዲመረመር ትእዛዝ አስተላለፈ። ሆኖም ጳውሎስ ዜግነቱ ሮማዊ መሆኑን ሲናገር እንዳይገረፍ ተደረገ። በሚቀጥለው ቀን ሉስዮስ፣ አይሁድ ለምን እንደከሰሱት ለማወቅ ጳውሎስን በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቆመው።—የሐዋርያት ሥራ 22:22-30

ጳውሎስ በዚህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት በቆመ ጊዜ ወገኖቹ ለሆኑት አይሁዳውያን ለመመሥከር ሌላ ጥሩ አጋጣሚ አገኘ። በዚህ ወቅት ይህ ደፋር ወንጌላዊ በትንሣኤ እንደሚያምን ተናገረ። (የሐዋርያት ሥራ 23:1-8) ጳውሎስን ለመግደል የፈለጉት አይሁዳውያን ጥላቻቸው እየባሰ በመሄዱ ወታደሮቹ፣ ጳውሎስን ወደ ጦር ሠፈር ወሰዱት። በሚቀጥለው ሌሊት ጌታ እንዲህ በማለት አበረታታው:- “አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል።”—የሐዋርያት ሥራ 23:9-11

አዛዡ፣ ጳውሎስ በሮም አስተዳደር ሥር የነበረችው የይሁዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ቂሳርያ በምሥጢር እንዲወሰድ በማድረጉ እርሱን ለመግደል የተጠነሰሰው ሤራ ከሸፈ። (የሐዋርያት ሥራ 23:12-24) ጳውሎስ በቂሳርያም “በነገሥታት ፊት” ለመመሥከር የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ አግኝቷል። በመጀመሪያ ግን ሐዋርያው፣ በእርሱ ላይ የተነሳው ክስ ማስረጃ የሌለው መሆኑን ለአገረ ገዢው ለፊልክስ ነገረው። በኋላም ጳውሎስ ለአገረ ገዢውና ለባለቤቱ ለድሩሲላ ስለ ኢየሱስ፣ ራስን ስለ መግዛት፣ ስለ ጽድቅና ስለሚመጣው ፍርድ ሰበከላቸው። ፊልክስ፣ ጳውሎስ ጉቦ እንደሚሰጠው ተስፋ በማድረግ ለሁለት ዓመታት በእስር እንዲቆይ ቢያደርግም ጳውሎስ ግን አልሰጠውም።—የሐዋርያት ሥራ 23:33 እስከ 24:27

ፊስጦስ በፊልክስ እግር በተተካ ጊዜ አይሁዳውያን ክሳቸውን በድጋሚ በማንሳት ጳውሎስ እንዲፈረድበትና እንዲገደል ጥያቄ አቀረቡ። ክሱ በድጋሚ በቂሳርያ እንዲሰማ የተደረገ ሲሆን ጳውሎስ ጉዳዩ በኢየሩሳሌም ፍርድ ቤት እንዲታይ ስላልፈለገ “አሁንም ቢሆን . . . በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ . . . ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ” በማለት ተናገረ። (የሐዋርያት ሥራ 25:1-11, 20, 21) ከጥቂት ቀናት በኋላ ጳውሎስ፣ በዳግማዊ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ፊት ጉዳዩን ከተናገረ በኋላ ንጉሡ “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው! [የ1980 ትርጉም]” ብሎታል። (የሐዋርያት ሥራ 26:1-28) ጳውሎስ በ58 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ወደ ሮም ተላከ። ይህ ዘዴኛ ሐዋርያ ከሁለት ዓመታት በላይ ታስሮ በነበረበት ወቅት ስለ ክርስቶስ የሚሰብክበትን መንገድ ይፈልግ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:16-31) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በንጉሠ ነገሥት ኔሮ ፊት ቀርቦ ጥፋተኛ አለመሆኑ ስለተፈረደለት በነጻ ተለቅቆ በሚስዮናዊነት ማገልገሉን የቀጠለ ይመስላል። ከጳውሎስ በስተቀር ሌሎች ሐዋርያት ለታላላቅ ሰዎች ምሥራቹን የመንገር አጋጣሚ እንዳገኙ የሚናገር ምንም ዘገባ የለም።

ከላይ ያለው ታሪክ እንደሚያሳየው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ብለው በአይሁድ ሸንጎ ፊት ከተናገሩት መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ሰዎች የጳውሎስን ሥራ ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም እንኳ ሐዋርያው የተሟላ ምሥክርነት እንዲሰጥ የተነገረውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ ታዟል። ጳውሎስ ያለማወላወል ለአምላክ በመታዘዝ “የተመረጠ ዕቃ” ሆኖ “በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት” የኢየሱስን ስም እንዲሸከም የተሰጠውን ተልእኮ ፈጽሟል።—የሐዋርያት ሥራ 9:15

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ኅዳር/ታኅሣሥ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ጳውሎስን በዋነኝነት ያሳሰበው ለራሱ መከላከያ ማቅረቡ ነበር?

ይህን ጥያቄ አስመልክተው ሣልሣዊ ቤን ዊዘሪንግተን የተባሉ ደራሲ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ከጳውሎስ . . . አመለካከት መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስን በዋነኝነት ያሳሰበው ለራሱ መከላከያ ማቅረቡ ሳይሆን ወንጌሉን ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት ባለ ሥልጣናት መመሥከሩ ነበር። . . . እንዲያውም ለፍርድ የቀረበው ወንጌሉ ነበር።”