‘የተዋበች የበረሃ ፍየል’
‘የተዋበች የበረሃ ፍየል’
ብዙዎቻችን አንድን ፍየል ለመግለጽ የተዋበ የሚለውን ቃል አንጠቀምም። ፍየሎች ማንኛውንም ነገር ማለት ይቻላል የሚመገቡና ጣፋጭ ሥጋና ገንቢ ወተት የሚሰጡ ጠቃሚ እንስሳት ናቸው ብለን እናስብ ይሆናል። ቢሆንም ውብ ብለን አንጠራቸውም።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሚስትን “እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ [“የበረሃ ፍየል፣” የ1980 ትርጉም ]” አድርጎ ይገልጻታል። (ምሳሌ 5:18, 19) የምሳሌን መጽሐፍ የጻፈው ሰሎሞን የእስራኤልን የዱር አራዊት በትኩረት ይከታተል ስለነበር ይህንን ምሳሌ ለመጠቀም ያነሳሳው በቂ ምክንያት እንደሚኖረው አያጠራጥርም። (1 ነገሥት 4:30-33) ምናልባትም ልክ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከሙት ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ወዳለው ዓይንጋዲ አዘውትረው የሚመጡትን የበረሃ ፍየሎች ተመልክቶ ይሆናል።
በይሁዳ በረሃ የሚኖረውና አነስተኛ ቁጥር ያለው የፍየል መንጋ አዘውትሮ ወደ ዓይንጋዲ ምንጭ ይመጣል። ዓይንጋዲ በዚህ ጠፍ በሆነ ምድር የሚገኝ ብቸኛ አስተማማኝ የውኃ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ለብዙ መቶ ዘመናት ለእነዚህ የበረሃ ፍየሎች አመቺ የውኃ መጠጫ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። እንዲያውም ዓይንጋዲ የሚለው ስም ምናልባት “የግልገል ፏፏቴ” ማለትም ሊሆን ስለሚችል ይህ ትንንሾቹ የበረሃ ፍየሎች አዘውትረው በዚህ ቦታ ይገኙ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ንጉሥ ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ስደት በደረሰበት ጊዜ “የበረሃ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው አለቶች” ሄዶ በስደት ለመኖር ቢገደድም 1 ሳሙኤል 24:1, 2
ይህ ቦታ እንደ መሸሸጊያ ሆኖ አገልግሎታል።—ዛሬም ቢሆን በዓይንጋዲ እንስቷ ዋሊያ ወይም የበረሃ ፍየል ግርማ ሞገስ ተላብሳና ረጋ ብላ ተባዕቱን ፍየል በመከተል ወደ ውኃ ምንጭ ዓለታማውን ገደል ስትወርድ ማየት ይቻላል። በዚህ ጊዜ እንስቷ ዋሊያና ታማኝ ሚስት ያላቸውን ተመሳሳይነት ታስተውል ይሆናል። ረጋ ያለው ተፈጥሮዋና ውብ የሆነው አካሏ የእንስትነት ባሕርይዋን አጉልቶ ያሳያል። “የተዋበ” የሚለው ቃል የበረሃ ፍየል ያላትን ግርማ ሞገስና ድንቅ ውበት ለመግለጽ የገባ ይመስላል። a
ሴቷ ዋሊያ ችግር መቋቋም የምትችልና ግርማ ሞገስ ያላት መሆን አለባት። ይሖዋ ለኢዮብ እንደነገረው የበረሃ ፍየል የምትወልደው ሰው በማይደርስባቸው፣ ምግብ ማግኘት በማይቻልበትና ከፍተኛ ሙቀት ባለባቸው ሩቅ አለታማ ገደሎች ውስጥ ነው። (ኢዮብ 39:1) እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉም እንኳ ልጆቿን ትንከባከባቸዋለች። ገደላማዎቹን ዓለቶች ሽቅብ እንዲወጡና ልክ እንደ እርሷ በዓለቶቹ መካከል በቅልጥፍና እንዲዘሉ ሥልጠና ትሰጣቸዋለች። ዋሊያ ግልገሎቿን ከአደጋም ትጠብቃለች። አንድ ታዛቢ አንዲት የበረሃ ፍየል ልጅዋን በጉያዋ ሸሽጋ ለግማሽ ሰዓት ያህል ከአንድ ንስር ጋር ስትፋለም ተመልክተዋል።
ክርስቲያን ሚስቶችና እናቶች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸውን በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለማሳደግ ይገደዳሉ። ልክ እንደ በረሃዋ ፍየል እነርሱም አምላክ የሰጣቸውን ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ከማቅረባቸውም በላይ ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር ያሳያሉ። ልጆቻቸውን ከመንፈሳዊ አደጋዎች ለመጠበቅም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ስለዚህ ሰሎሞን በዚህ ምሳሌ መጠቀሙ ሴቶችን ማቃለሉ ሳይሆን ያላቸውን ውበትና ግርማ ሞገስ ማለትም በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ የሚያንጸባርቋቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት ጎላ አድርጎ መግለጹ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ኒው ብራውን ድራይቨር ብሪግስ ጂሴኒየስ ሂብሩ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ “የተዋበ” ተብሎ የተተረጎመው ቼን የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በዚህ አገባቡ ‘ግርማ ሞገስ ወይም ውብ የአካል ቅርጽ’ ማለት ነው።
[በገጽ 30 እና 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሚስትና እናት ከአምላክ የተሰጧትን ኃላፊነቶች ስትወጣ ውብ መንፈሳዊ ባሕርያትን ታንጸባርቃለች