በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባገኘሁት ልዩ ውርሻ ተባርኬአለሁ

ባገኘሁት ልዩ ውርሻ ተባርኬአለሁ

የሕይወት ታሪክ

ባገኘሁት ልዩ ውርሻ ተባርኬአለሁ

ካረል አለን እንደተናገረችው

ውብ የሆነውን አዲሱን መጽሐፌን ሙጭጭ አድርጌ ይዤ ብቻዬን ቆሜያለሁ። በጣም ፈርቼ ስለነበር እንባዬ በጉንጮቼ ላይ ኮለል እያለ ይወርዳል። ደግሞም ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ በማላውቀው ከተማ ብዙ ሺህ ሕዝብ መሃል ገብቼ በመጥፋቴ ፍርሃት ቢሰማኝ አያስደንቅም!

ከባለቤቴ ከፖል ጋር ፓተርሰን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ውስጥ ያደረግነው ጉብኝት ከ60 ዓመት ገደማ በፊት የነበረውን የልጅነት ትዝታዬን ቀሰቀሰብኝ። ወደ ፓተርሰን የሄድነው ባለቤቴ ለይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በሚሰጠው ኮርስ ሁለተኛ ክፍል እንዲሳተፍ ስለ ተጋበዘ ነበር።

ወለል ባለው የእንግዳ መቆያ ክፍል ውስጥ ሆነን ዓይናችንን ስናማትር የአውራጃ ስብሰባዎች የሚል በትልቁ የተጻፈ መግለጫ አየሁ። ወደ መካከል ገደማ በጣም የተደሰቱ ሕፃናት በልጅነቴ ይዤው የነበረውን መጽሐፍ አንድ አንድ ቅጂ ሲያውለበልቡ የሚያሳይ ጥቁርና ነጭ ፎቶ ግራፍ ተሰቅሏል! ፈጠን ብዬ ፎቶግራፉ ሥር ያለውን መግለጫ አነበብኩ። እንዲህ ይላል:- “1941:- ሚዙሪ ውስጥ በሴይንት ሉዊ በጠዋቱ ፕሮግራም መክፈቻ ላይ ከ5 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው 15, 000 ልጆች በዋናው የመሰብሰቢያ ቦታ ከመድረኩ ፊት ለፊት ተሰበሰቡ። . . . ወንድም ራዘርፎርድ ልጆች (እንግሊዝኛ) የተባለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን አስታወቀ።”

ለእያንዳንዱ ልጅ አንድ አንድ ቅጂ ተሰጥቶ ነበር። ከዚያም ከእኔ በስተቀር ሁሉም ልጆች ወደ ወላጆቻቸው ተመለሱ። እኔ ወላጆቼ ያሉበት ቦታ ጠፋብኝ! አንድ ተግባቢ አስተናጋጅ ወደ ላይ አንስቶ በረጅም መዋጮ ሳጥን ላይ አቆመኝና የማውቀውን ሰው እንድፈልግ ነገረኝ። በሰፊው ደረጃ ላይ ወደ ታች ከሚጎርፈው ሕዝብ መካከል የማውቀውን ሰው ለማግኘት በፍርሃት ተውጬ በዓይኔ ፈለግሁ። ድንገት አንድ የማውቀውን ሰው አየሁ! “አንክል ቦብ! አንክል ቦብ!” ብዬ ተጣራሁ። በመጨረሻ የማውቀው ሰው አገኘሁ! ቦብ ሬይነር እቅፍ አድርጎ ተጨንቀው ወደሚጠብቁኝ ወላጆቼ ወሰደኝ።

ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ሕይወቴን የቀረጹት ሁኔታዎች

ለእይታ የቀረቡትን ፎቶግራፎች ስመለከት የልጅነት ሕይወቴን በመቅረጽ አስደሳች በሆነው በፓተርሰን ለመገኘት ያበቁኝን በጣም ብዙ ትዝታዎች ቀሰቀሱብኝ። በተለይ ከአያቶቼና ከወላጆቼ እሰማቸው ወደነበሩት ከመቶ ዓመት በፊት ወደተከናወኑት ድርጊቶች በትዝታ ተጓዝኩ።

ታኅሣሥ 1894 በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ አያቴን ክሌተን ጄ ዉድዎርዝን ስክራንቶን ፔንሲልቫንያ ዩ ኤስ ኤ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መጥቶ አነጋገረው። ክሌተን ገና ጎጆ መውጣቱ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት ለነበረው ለቻርልስ ቴዝ ራስል ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን ደብዳቤው በሰኔ 15, 1895 መጠበቂያ ግንብ ላይ ታትሞ ወጥቷል። እንዲህ ሲል ነበር የጻፈው:-

“እኛ ለአሥር ዓመት ገደማ የአንድ የይስሙላ ቤተ ክርስቲያን አባላት የነበርን ወጣት ባልና ሚስት ነን። አሁን ግን ከጨለማ ወጥተን ለልዑሉ ላደሩ ልጆች ወደ ጠባው የአዲስ ቀን ብርሃን እንደገባን እናምናለን። . . . ከመተዋወቃችን ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ጌታ ከፈቀደ ወደ ባዕድ አገር ሄደን በሚስዮናዊነት እናገለግላለን የሚል ጽኑ እምነት ነበረን።”

ከጊዜ በኋላ በ1903 ሁለት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተወካዮች በፔንሲልቫንያ ውብ በሆኑት የፖኮኖ ተራሮች አካባቢ በሚገኝ ትልቅ የእርሻ ቦታ ለሚኖሩት ሰባስቸን እና ካትረን ክረዝጊ ለሚባሉት ቅድመ አያቶቼ (በእናቴ በኩል) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሲነግሯቸው በደስታ አዳመጡ። ኮራ እና ማሪ የሚባሉት ሴቶች ልጆቻቸው ዋሽንግተን እና ኤድመንት ሃውል ከሚባሉት ባሎቻቸው ጋር እዚያው ይኖሩ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተወካዮች የነበሩት ካርል ሃመርሊ እና ሬይ ራትክሊፍ አንድ ሳምንት አብረዋቸው ቆይተው ብዙ ነገሮችን አስተማሯቸው። ስድስቱም የቤተሰቡ አባላት አዳመጡ፣ አጠኑና ብዙም ሳይቆይ በቅንዓት የሚሰብኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ።

በዚያው ዓመት በ1903 ኮራ እና ዋሽንግተን ሃውል ካትረን የምትባል ልጅ ወለዱ። እሷና አባቴ ጁኒየር ክሌተን ጄ ዉድዎርዝ የተጋቡበት መንገድ አስገራሚ ሲሆን ይህ ራሱ አስደሳች ታሪክ ይወጣዋል ብዬ አስባለሁ። ሁኔታው የአያቴን የሲኒየር ክሌተን ጄ ዉድዎርዝን ፍቅራዊ አስተዋይነትና አባታዊ አሳቢነት የሚያንጸባርቅ ነበር።

አባቴ ፍቅራዊ እርዳታ ተደረገለት

አባቴ ጁኒየር ክሌተን መስከረም 1906 የሃውል ቤተሰብ እርሻ ከሚገኝበት በግምት 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኝ ስክራቶን በተባለ ቦታ ተወለደ። በዚያ ወቅት አያቴ ዉድዎርዝ በእንግዳ ተቀባይነታቸው ከሚታወቁት የሃውል ቤተሰብ ጋር በጣም ይቀራረብ ነበር። በአካባቢው የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጉባኤ በጣም ይረዳ ነበር። ከጊዜ በኋላ የሃውል ሦስት ልጆች ሲያገቡ የጋብቻቸውን ንግግር እንዲያቀርብ የተጋበዘ ሲሆን አያቴ የራሱን ልጅም የወደፊት ሕይወት የተሳካ እንዲሆን በማሰብ በሦስቱም ሠርጎች ላይ ይዞት ተገኝቷል።

አባባ በዚያ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያከናውኑት የአገልግሎት እንቅስቃሴ ላይ አይካፈልም ነበር። እርግጥ ነው፣ አያቴ አገልግሎት ሲወጣ በመኪና ያደርሰው ነበር። ነገር ግን አያቴ ቢያበረታታውም በአገልግሎት ለመካፈል ፍላጎቱ አልነበረውም። አባቴ በወቅቱ ሙዚቃን ከምንም ነገር በላይ አስበልጦ ይወድ የነበረ ሲሆን እሱን ሙያዬ ብሎ ለመያዝ ይጣጣር ነበር።

የኮራ እና የዋሽንግተን ሃውል ልጅ ካትረንም እንዲሁ ፒያኖን በመጫወትና በማስተማር የተዋጣላት ሙዚቀኛ ነበረች። በዚህ ሙያዋ ለመግፋት የሚያስችላት ጥሩ አጋጣሚ ቢከፈትላትም እሱን ወደ ጎን ትታ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። እንደመሰለኝ ከሆነ አያቴ ለልጁ ከእርሷ የተሻለ ጓደኛ ሊገኝለት እንደማይችል ሳይሰማው አልቀረም! አባባ ተጠመቀና ከስድስት ወር በኋላ ሰኔ 1931 እማማን አገባ።

አያቴ በልጁ የሙዚቃ ችሎታ ሁልጊዜ ይኮራ ነበር። አባባ በ1946 በክሌቭላንድ ኦሃዮ ለሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ትልቅ የሙዚቃ ቡድን እንዲያሠለጥን ሲጠየቅ አያቴ በጣም ተደስቶ ነበር። በቀጣዮቹ ዓመታት አባባ የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጓቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሙዚቃ ቡድኑን መርቷል።

የአያቴ ፍርድ ቤት መቅረብና በእስር ቤት ያሳለፋቸው ዓመታት

እኔና ፖል በፓተርሰን እንግዳ መቆያ ክፍል ውስጥ በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚታየውን ፎቶግራፍ ተመለከትን። አያቴ ከ50 ዓመት በፊት ይህን ፎቶ አሳጥቦ ልኮልኝ ስለነበር ፎቶውን ለመለየት ጊዜ አልወሰደብኝም። አያቴ በስተቀኝ ዳር ላይ የቆመው ነው።

አንደኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድን ጨምሮ (መካከል የተቀመጠው) ስምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያለአግባብ ታስረውና የዋስ መብት ተነፍጓቸው ነበር። ለመከሰሳቸው ምክንያት የሆነው ነገር ያለቀለት ምስጢር (እንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያለው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ሰባተኛ ጥራዝ ላይ የተወሰዱ አባባሎች ናቸው። እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ዩናይትድ ስቴትስ በአንደኛው የዓለም ጦርነት እንዳትካፈል ይቀሰቅሳሉ የሚል የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቷቸው ነበር።

ከብዙ ዓመታት በፊት ቻርልስ ቴዝ ራስል የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባሉትን ስድስት ጥራዞች የጻፈ ሲሆን ሰባተኛውን ከመጻፉ በፊት ሞተ። ስለዚህ እሱ የተወው ማስታወሻ ለአያቴና ለአንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ተሰጠና ሰባተኛውን ጥራዝ እነርሱ ጻፉ። መጽሐፉ ጦርነቱ ከማቆሙ በፊት በ1917 ወጣ። ፍርድ ቤቱ በአያቴና በብዙዎቹ ተከሳሾች ላይ ለቀረበው ለእያንዳንዱ አራት ተደራራቢ ክስ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት በይኖባቸዋል።

በፓተርሰን የእንግዳ መቆያ ክፍል በተሰቀለው ፎቶግራፍ ሥር የተጻፈው መግለጫ እንዲህ ይላል:- “ራዘርፎርድና ባልደረቦቹ ከተፈረደባቸው ከዘጠኝ ወር በኋላ በጦርነቱ ማብቂያ ማግስት መጋቢት 21, 1919 ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለስምንቱ እስረኞች የዋስ መብት የሰጣቸው ሲሆን መጋቢት 26 ለእያንዳንዳቸው የ10, 000 የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ዋስትና ተከፍሎ ከእስር ተፈቱ። ግንቦት 5, 1920 ጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ሌሎቹም እስረኞች ከክሱ ነፃ ሆኑ።”

ስምንቱ ወንድሞች ከተፈረደባቸው በኋላ አትላንታ ወደሚገኘው የፌዴራሉ ወኅኒ ቤት ከመወሰዳቸው በፊት ብሩክሊን ኒው ዮርክ ሬይሞንድ ጎዳና በሚገኘው ወኅኒ ቤት ለጥቂት ቀናት ታስረው ነበር። አያቴ 1.8 በ2.4 ሜትር ስፋት ባለው “ምስቅልቅሉ በወጣና በቆሸሸ ክፍል ውስጥ እንደታሰረ ጽፎልኝ ነበር። እንዲህ አለ:- “በዚህች ክፍል ውስጥ ጋዜጣ ተቆልሏል፤ ይህ ደግሞ እዚያ ምን ያደርጋል ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ብዙም ሳትቆዪ ግን ለንጽሕናና ራስሽን ለመጠበቅ ያለሽ ምርጫ በእነዚህ ወረቀቶች፣ ሳሙና እና ማበሻ ጨርቅ መጠቀም ብቻ እንደሆነ ትገነዘቢያለሽ” ብሎ ነበር።

ሆኖም አያቴ ቀልዱን አልተወም ነበር፤ እስር ቤቱን “ዲ ሬሞንዲ ሆቴል” ብሎ የጠራው ሲሆን “እንግዲህ ኮንትራቴ እስኪያልቅ እዚችው ነው የምቆየው” ሲል ተናግሯል። ግቢው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲል ያጋጠመውንም ጽፏል። አንድ ቀን ፀጉሩን ለመበጠር ለአንድ አፍታ ቆም ሲል አንድ ኪስ አውላቂ የኪስ ሰዓቱን ሞጭልፎ ለመሮጥ ሞክሮ ነበር፤ ሆኖም “ሰንሰለቱ ተበጥሶ ሰዓቴ ተረፈልኝ” በማለት ጽፏል። በ1958 ብሩክሊን የሚገኘውን ቤቴል በመጎብኘት ላይ ሳለሁ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ የነበረው ግራንት ሱተር ወደ ቢሮው ጠርቶ ያንን ሰዓት ሰጠኝ። አሁን ድረስ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጬዋለሁ።

በአባቴ ላይ ያስከተለው ተጽእኖ

በ1918 አያቴ ያለአግባብ በታሰረበት ጊዜ አባቴ ገና የ12 ዓመት ልጅ ነበር። አያቴ ቤቱን ቆላልፋ ከእናቷና ከሦስት እህቶቿ ጋር ለመኖር ይዛው ሄደች። አያቴ ከማግባቷ በፊት አርተር ትባል ስለነበር ቤተሰቦቿ የ21ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የቼስተር አለን አርተር ዘመድ መሆናቸውን በኩራት ይናገሩ ነበር።

አያቴ ዉድዎርዝ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የረጅም ዓመታት እስር ከተፈረደበት በኋላ የአርተር ቤተሰቦች አያቴ በቤተሰቡ ስም ላይ ነቀፋ እንዳመጣ ተሰምቷቸው ነበር። በዚህ ነገር አባቴ ስሜቱ ተጎድቶ ነበር። በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ያቅማማበት አንዱ ምክንያት ይህ ሳይሆን አይቀርም።

አያቴ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ከነቤተሰቡ በስክራንቶ ክዊንዚ ጎዳና ወደሚገኘው ትልቅ የአሸዋ ግርፍ ቤት ተዛወረ። የዚያን ጊዜ ትንሽ ልጅ ብሆንም ቤታቸውንና የአያቴን የሚያማምሩ የሸክላ ሳሕኖች አስታውሳለሁ። ሳሕኖቹን ከእርሷ በቀር ሌላ ማንም እንዲያጥብ ስለማትፈቅድ ቅዱስ ሳሕኖች ብለን እንጠራቸው ነበር። አያቴ በ1943 ከሞተች በኋላ እማማ ብዙ ጊዜ በእነዚያ የሚያማምሩ ሳሕኖች እንግዶችን ለማስተናገድ ትጠቀምባቸው ነበር።

በአገልግሎት ሥራ የበዛልን መሆን

እዚያው ፓተርሰን ሳለን አንድ ቀን ወንድም ራዘርፎርድ በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርብ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አየሁ። ሁሉም የአምላክን መንግሥት በቅንዓት እንዲያስታውቁና በዚያ ስብሰባ ላይ የወጣውን ወርቃማው ዘመን የተሰኘውን አዲስ መጽሔት በአገልግሎት ላይ እንዲጠቀሙ ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር። አያቴ የመጽሔቱ አዘጋጅ ሆኖ የተሾመ ሲሆን በ1940ዎቹ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ለመጽሔቱ ጽሑፍ ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በ1937 የመጽሔቱ ስም መጽናናት የተባለ ሲሆን በ1946 ደግሞ ንቁ! ተብሎ ተጠራ።

አያቴ ጽሑፍ የማዘጋጀት ሥራውን ያከናውን የነበረው ስክራንተን በሚገኘው ቤቱና 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብሩክሊን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ሲሆን በእያንዳንዱ ቦታ ሁለት ሳምንት ይቀመጥ ነበር። ብዙውን ጊዜ ከማለዳው አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ የጽሕፈት መኪናውን ድምፅ ይሰማ እንደነበር አባባ ያስታውሳል። አያቴ ለሕዝብ የሚሰጠውን የስብከት ሥራ በቁም ነገር ይመለከተው ነበር። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን መያዣ ትልቅ የውስጥ ኪስ ያለው የወንድ ሰደርያ ሠፍቶ ነበር። የ94 ዓመቷ አክስቴ ናኦሚ ሃውል እስካሁን አንድ ሰደርያ አላት። ለሴቶች የሚሆን የመጽሐፍ ቦርሳም ሠርቷል።

አንድ ቀን ከአንድ ሰው ጋር አገልግሎት ላይ ሞቅ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ካደረጉ በኋላ የአያቴ የአገልግሎት ጓደኛ “ሲ ጄ አንድ ጥፋት ሠርተሃል” አለው።

አያቴ “ምን አጠፋሁ?” ሲል ጠየቀና ሰደርያውን ፈተሸ። ሁለቱም ኪሶች ባዶ ነበሩ።

“ወርቃማው ዘመን ኮንትራት እንዲገባ መጋበዝ ረሳህ።” ራሱ የሚያዘጋጀውን መጽሔት ኮንትራት ማስገባት በመርሳቱ ሁለቱም ከት ብለው ሳቁ።

የልጅነት ትዝታዎች

ልጅ ሳለሁ አያቴ ጭን ላይ ተቀምጬ እጄን በመዳፉ ላይ አድርጌ “የጣት ተረት” ይነግረኝ የነበረው ትዝ ይለኛል። “ከአውራ ጣት” አንስቶ ወደ “ሌባ ጣት” እየቀጠለ እያንዳንዱን ጣት ልዩ ስለሚያደርገው ነገር ይነግረኝ ነበር። ከዚያም እጁን በደንብ ይጨብጥና “አንዱ ሌላውን እየረዳ ሲተጋገዙ ጥሩ ሥራ ይሠራሉ” ብሎ ይነግረኝ ነበር።

ወላጆቼ ከተጋቡ በኋላ በክሌቭላንድ ኦሃዮ መኖር የጀመሩ ሲሆን እዚያም ከኤድ እና ከማሪ ሁፐር ጋር የሚቀራረቡ ወዳጆች ሆኑ። ቤተሰቦቻቸው ከክፍለ ዘመኑ መጀመሪያ አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። አጎቴና አክስቴ እያልኩ እጠራቸው የነበሩት ኤድና ማሪ ከወላጆቼ ጋር ፈጽሞ አይለያዩም ነበር። ሴት ልጃቸውን በሞት ስላጡ በ1934 እኛ ወደዚያ ስንዛወር ልክ እንደ “ልጃቸው” አድርገው ያዩኝ ነበር። በመንፈሳዊ በበለጸገ እንደዚህ ባለ አካባቢ በማደጌ ስምንት ዓመት ሳይሞላኝ ራሴን ለአምላክ ወስኜ ተጠመቅኩ።

ከልጅነቴ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ ነበረኝ። አምላክ ስለሚያመጣው አዲስ ዓለም የሚናገረው የኢሳይያስ 11:​6-9 ጥቅስ በጣም ከምወዳቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ጥረት ያደረግኩት በ1944 ሲሆን ይህም በልዩ እትም የተዘጋጀው አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን በቡፋሎ ኒው ዮርክ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወጥቶ አንድ ቅጂ ካገኘሁ በኋላ ነበር። ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም “በብሉይ ኪዳን” ውስጥ 7, 000 ጊዜ ገደማ በተገቢው ቦታ የሚገኝበትን ይህን መጽሐፍ በማንበቤ በጣም ተደስቼያለሁ!

ቅዳሜና እሁድ አስደሳች ቀናት ነበሩ። ወላጆቼና የሁፐር ቤተሰብ ለአገልግሎት ገጠር ይዘውኝ ሄደው ነበር። አንድ ወንዝ አጠገብ አርፈን የያዝነውን ምሳ ከበላን በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር እንዲሰሙ የመንደሩን ነዋሪዎች በጠቅላላ ጋብዘን ስለነበር ወደ አንድ ሰው ማሳ ሄድን። ሕይወት አስደሳች ነበር። ከተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። ኤድ ሁፐርን፣ ቦብ ሬይነር እና ሁለት ወንዶች ልጆቹን ጨምሮ ብዙዎቹ የቤተሰባችን የቅርብ ወዳጆች ከጊዜ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነዋል። ሪቻርድ ሬይነር ከባለቤቱ ከሊንዳ ጋር በመሆን አሁንም በዚሁ ኃላፊነት ላይ እየሠራ ነው።

በተለይ የበጋው ወቅት አስደሳች ነበር። ይህን ወቅት በሃውል እርሻ ቦታ ከአክስቴ ልጆች ጋር አሳልፍ ነበር። በ1949 የአክስቴ ልጅ ግሬስ ማልኮልም አለንን አገባች። ከዓመታት በኋላ የእሱን ወንድም አገባለሁ ብዬ አስቤው አላውቅም ነበር። የግሬስ ታናሽ የሆነችው የአክስቴ ልጅ ማሪዮን በኡራጓይ ሚስዮናዊት ነበረች። እሷም በ1966 ሆእርድ ሂልቦርንን አገባች። የአክስቴ ልጆች ሁለቱም ከባሎቻቸው ጋር ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል።

አያቴ እና ትምህርቴን ማጠናቀቄ

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ከአያቴ ጋር እንጻጻፍ ነበር። ከደብዳቤዎቹ ጋር በሚልካቸው ብዙ የቆዩ ፎቶግራፎች ጀርባ ላይ በዝርዝር እየጻፈ የቤተሰባችንን ታሪክ ይነግረኝ ነበር። አብረውት ያለአግባብ ታስረው ከነበሩ ወንድሞች ጋር የተነሳው ፎቶግራፍ የደረሰኝ በዚህ መንገድ ነበር።

በ1951 መጨረሻ ላይ አያቴ በካንሰር ምክንያት ጉሮሮው በመጎዳቱ መናገር ተሳነው። ጣል የሚያደርጋት ቀልዱ ግን አልቀረችም፤ ሆኖም መናገር የሚፈልገውን ነገር ሁልጊዜ ከእጁ በማትለየው ማስታወሻ ደብተር ላይ መጻፍ ነበረበት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የማጠናቅቀው በዓመቱ አጋማሽ ጥር 1952 ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ በታኅሣሥ፣ በምረቃው ዕለት የማቀርበውን ንግግር ቅጂ ላኩለት። አንዳንድ ማስተካከያዎችን ካደረገበት በኋላ በመጨረሻው ገጽ ላይ ልቤን በጥልቅ የነኩትን “አያትሽ ተደስቷል” የሚሉትን ቃላት ጻፈበት። ታኅሣሥ 18, 1951 በ81 ዓመቱ ምድራዊ ሕይወቱን ፈጸመ። a እነዚያ ሁለት ቃላት የተጻፉበት ያ የንግግር አስተዋጽዖ አሁን ድረስ ከእኔ ጋር አለ።

ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የአቅኚነት አገልግሎት ብለው የሚጠሩትን የሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ ጀመርኩ። በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ከ123 አገሮች የመጡ 253, 922 ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር የተገኙበትን ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ተካፍያለሁ። በዚያ ስብሰባ ላይ “ዉድዎርዝ ሚልስ” የሚል ባጅ የለጠፈ ከአፍሪካ ከመጣ አንድ ልዑክ ተዋወቅሁ። በአያቴ ስም የተጠራው ከ30 ዓመት በፊት ነበር!

ባገኘሁት ውርሻ ደስተኛ ነኝ

አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ እናቴ እንደገና አቅኚነት ጀመረች። ከ40 ዓመት በኋላ በ1988 ስትሞትም አቅኚ ነበረች! አባባ ሁኔታው ሲስተካከልለት በአቅኚነት ሠርቷል። እማማ ከመሞቷ ከዘጠኝ ወር በፊት ሞተ። እናስጠናቸው የነበሩ ሰዎች ውድ ጓደኞቻችን ሆነውልናል። አንዳንድ ወንዶች ልጆቻቸው ብሩክሊን በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት እያገለገሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አቅኚዎች ሆነዋል።

ለእኔ 1959 ልዩ ግምት የምሰጠው ዓመት ነበር። ከፖል አለን ጋር የተዋወቅነው በዚህ ዓመት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን ከሚሰለጥኑበት ከጊልያድ ትምህርት ቤት ሰባተኛ ክፍል ከተመረቀ በኋላ በ1946 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። መጀመሪያ በተዋወቅን ጊዜ ፖል ቀጥሎ የሚጎበኘው እኔ በአቅኚነት የምሠራበት ክሌቭላንድ ኦሃዮ ይሆናል ብሎ ማንም አላሰበም። አባባም እማማም ወደዱት። ሐምሌ 1963 በሃውል እርሻ ቦታ በቤተሰቦቻችን ታጅበን የተጋባን ሲሆን የጋብቻ ንግግሩን ያቀረበው ኤድ ሁፐር ነበር። ሕልማችን እውን የሆነበት ጊዜ ነበር።

ፖል መኪና ኖሮት አያውቅም። ከክሌቭላንድ ወደሚቀጥለው ምድብ ቦታው ስንሄድ ጓዛችንን ሁሉ የምንጭነው በእኔ የ1961 ቮልስቫገን ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰኞ ወደ ሌላ ጉባኤ ለመሄድ ዕቃችንን ስንጭን ለማየት ወንድሞች ይመጡ ነበር። ሻንጣዎች፣ ቦርሳዎች፣ የፋይል መያዣ፣ የጽሕፈት መኪና እና ሌሎችንም ነገሮች በዚያች ትንሽ መኪና ውስጥ ስናጭቅ ማየቱ የሰርከስ ትርኢት የምናሳይ እንመስል ነበር።

እኔና ፖል ብዙ ኪሎ ሜትሮች አብረን በተጓዝንባቸው ጊዜያት ክፉውንም ደጉንም አብረን አሳልፈናል። ይህንን ማድረግ የቻልነው ይሖዋ ብቻ በሚሰጠው ብርታት ነበር። ያሳለፍናቸው ዓመታት ለይሖዋ፣ አንዳችን ለሌላው እንዲሁም በቅርብም ሆነ በሩቅ ለምናውቃቸው ወዳጆቻችን ባለን ፍቅር የተሞሉ አስደሳች ዓመታት ነበሩ። ፖል በሥልጠና ላይ እያለ በፓተርሰን ያሳለፍናቸው ሁለት ወራት በሕይወታችን ጉልህ ሥፍራ የምንሰጣቸው ጊዜያት ናቸው። የይሖዋን ምድራዊ ድርጅት በቅርብ ለመመልከት መቻሌ ለእኔ ከተላለፉልኝ ውድ መንፈሳዊ ውርሻዎች መካከል ስለ አንዱ ማለትም ይህ በእርግጥም የአምላክ ድርጅት ስለመሆኑ ያለኝን የጸና እምነት አጠናክሮልኛል። በዚህ ድርጅት ውስጥ ትንሽ እንኳ ድርሻ ማግኘት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የየካቲት 15, 1952 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 128ን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ልጆች” የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ከተቀበልኩበት በ1941 በሴንት ሉዊ ከተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ትንሽ ቀደም ብሎ ከኤድ ሁፐር ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አያቴ በ1948

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሃውል ቤተሰብ እርሻ ቦታ ላይ ወላጆቼ (ክብ የተደረገባቸው) በተጋቡ ጊዜ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1918 ያለአግባብ የታሰሩት ስምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (አያቴ በስተቀኝ በኩል ዳር ላይ የቆመው ነው)

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምንጠቀምባቸውን ዕቃዎች በሙሉ የምንጭነው በቮልስቫገን መኪናችን ውስጥ ነበር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከፖል ጋር