በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት

አል ክዋሪዝሚ

አል ክዋሪዝሚ

ሰዎች ክብደታቸውን ለመለካት ወይም ከገበያ የገዙትን ሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ለማስላት በአብዛኛው የሚጠቀሙት የሂንዱ ዓረብኛ ቁጥሮችን ነው። “ሂንዱ ዓረብኛ” የሚለውን ስያሜ መጠቀም ያስፈለገው ለምንድን ነው? በዘመናችን የምንጠቀምባቸው ከዜሮ እስከ ዘጠኝ ያሉት ቁጥሮች መጀመሪያ ሥራ ላይ የዋሉት በሕንድ ሲሆን ለምዕራቡ ዓለም የተዋወቁት ደግሞ በዓረብኛ ፊደላት ይጽፉ በነበሩ የመካከለኛው ዘመን ምሁራን አማካኝነት ነው። ከእነዚህ ምሁራን መካከል ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል ክዋሪዝሚ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ይህ ሰው በ780 ዓ.ም. ገደማ በአሁኗ ኡዝቤክስታን እንደተወለደ የሚገመት ሲሆን “የዓረብኛ ሒሳብ ሊቅ” የሚል ስም አትርፏል። እንዲህ ያለውን እውቅና ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

“የዓረብኛ ሒሳብ ሊቅ”

አል ክዋሪዝሚ የአሥርዮሽ የቁጥር ሥርዓት ወይም ዴሲማል ስላለው ጠቀሜታ የጻፈ ሲሆን አንዳንድ የሒሳብ ስሌቶችን መሥራት ስለሚቻልበት መንገድ ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷል። ይህን ዘዴ ዘ ቡክ ኦቭ ሪስቶሪንግ ኤንድ ባላንሲንግ በተባለው መጽሐፉ ላይ አብራርቷል። ኪታብ አል ጃብር ወል ሙካቤላ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው አልጀብራ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው አል ጃብር ከሚለው የዓረብኛ ቃል ነው። የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ኤሳን ማሰኡድ፣ አልጀብራ “እስከ ዛሬ ከተፈለሰፉት የስሌት ዘዴዎች ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትና ለሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ ይታሰባል” ብለዋል። *

አንድ ጸሐፊ “በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች [አል ክዋሪዝሚ] እንዲህ ያለውን ነገር ለምን ፈጠረ ብለው ሲያማርሩ ኖረዋል” በማለት በቀልድ መልክ ተናግረዋል። አል ክዋሪዝሚ ግን ዓላማው ከንግድ፣ ከውርስ ክፍፍል፣ ከቅየሳና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር የተያያዙ ስሌቶችን በቀላሉ መሥራት እንዲቻል ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ጋሊልዮንና ፊቦናቺን ጨምሮ ምዕራባውያን የሒሳብ ሊቃውንት ስሌቶችን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ማብራሪያ በመስጠቱ ለአል ክዋሪዝሚ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። የአል ክዋሪዝሚ ማብራሪያዎች በአልጀብራ፣ በአሪትሜቲክና በትሪጎኖሜትሪ ለሚደረጉ ተጨማሪ ጥናቶች መንገድ ከፍተዋል። ትሪጎኖሜትሪ የመካከለኛው ምሥራቅ ምሁራን የባለ ሦስት ጎን ቅርጾችን ማዕዘኖችና የጎን ርዝመቶች ለማስላት እንዲችሉ እንዲሁም በሥነ ፈለክ መስክ ይበልጥ ጥናት እንዲያካሂዱ አድርጓል። *

አልጀብራ፦ “እስከ ዛሬ ከተፈለሰፉት የስሌት ዘዴዎች ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት”

የአል ክዋሪዝሚን ግኝቶች መሠረት ያደረጉ ሰዎች የአሥርዮሽ ክፍልፋዮች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉባቸውን አዳዲስ መንገዶች ከማግኘታቸውም በላይ ስፋትንና ይዘትን ለማስላት የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎችን አዳብረዋል። የመካከለኛው ምሥራቅ መሐንዲሶችና ግንበኞች እንደነዚህ ባሉት ዘመናዊ ዘዴዎች መጠቀም የጀመሩት ከምዕራባውያን አቻዎቻቸው ቀድመው ነው። ምዕራባውያኑ ከዚህ ዘዴ ጋር የተዋወቁትና ይህን ዘዴ ወደ አገራቸው እንዲገባ ያደረጉት በመስቀል ጦርነት ወቅት በማረኳቸው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የተማሩ ምርኮኞችና ስደተኞች አማካኝነት ነው።

የዓረብኛ ሒሳብ ተስፋፋ

ከጊዜ በኋላ የአል ክዋሪዝሚ ሥራዎች ወደ ላቲን ተተረጎሙ። የፒዛው ሌኦናርዶ በሚል ስያሜም ይታወቅ የነበረው ጣሊያናዊው የሒሳብ ሊቅ ፊቦናቺ (1170-1250 ገደማ) የሂንዱ ዓረብኛ ቁጥሮችን ለምዕራቡ ዓለም እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል። ፊቦናቺ ስለ እነዚህ ቁጥሮች ያወቀው በሜድትራንያን አካባቢዎች ጉዞ ባደረገበት ወቅት ነው፤ ከጊዜ በኋላ ቡክ ኦቭ ካልኩሌሽን (የስሌት መጽሐፍ) የተባለውን መጽሐፍ ጽፏል።

የአል ክዋሪዝሚ ሥራዎች በሚገባ ሳይታወቁ በርካታ ምዕተ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ግን እሱ ያስተዋወቃቸው ዘዴዎችና እነዚህን ዘዴዎች መነሻ ያደረጉት ስሌቶች ለንግድና ለኢንዱስትሪ እንዲሁም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ደም ሥር ሆነዋል።

^ አን.5 በዘመናዊ አልጀብራ፣ በአንድ ስሌት ውስጥ ዋጋቸው ምን ያህል እንደሆነ ያልታወቁ ቁጥሮች እንደ x ወይም y ባሉ ፊደላት ይወከላሉ። ለምሳሌ x + 4 = 6 የሚለውን ስሌት እንመልከት። ከውጤቱ ላይ 4 ብንቀንስ የx ዋጋ 2 ይሆናል።

^ አን.7 የግሪክ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች፣ የባለ ሦስት ጎን ቅርጾችን የጎን ርዝመትና ማዕዘን የማስላትን ዘዴ በግንባር ቀደምትነት አስፋፍተዋል። የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ምሁራን መካ የሚገኝበትን አቅጣጫ ለማወቅ በትሪጎኖሜትሪ ተጠቅመዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ፊታቸውን ወደ መካ አቅጣጫ አድርገው መጸለይ ይመርጣሉ። ሰው ሲሞት አስከሬኑን ወደ መካ አቅጣጫ አዙረው እንዲቀብሩ እንዲሁም ከብት አራጆች ከብቶችን በሚያርዱበት ጊዜ ፊታቸውን ወደ መካ እንዲያዞሩ የሚያዝ ወግ ነበራቸው።