በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት

አርስቶትል

አርስቶትል

ከ2,300 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የኖረው አርስቶትል በሳይንስና በፍልስፍናው መስክ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አርስቶትል ያመነጫቸው ሐሳቦች እንዲሁም ግኝቶቹና ጽሑፎቹ ለረጅም ጊዜ የሰዎችን ትኩረት ስበው ቆይተዋል፤ በተጨማሪም በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል እንዲሁም ተጠንተዋል። የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ ማክላክላን “አርስቶትል ስለ ተፈጥሮ የነበረው አመለካከት ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት በአውሮፓ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል” በማለት ጽፈዋል። እንዲያውም አርስቶትል ያምንባቸው ከነበሩት ነገሮች አንዳንዶቹ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት እንዲሁም በእስልምና ትምህርቶች ላይ ጭምር ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ስለ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አጥንቷል

አርስቶትል ሥነ ጥበብን፣ ሥነ ፈለክን፣ ሥነ ሕይወትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ቋንቋን፣ ሕግን፣ ሎጂክን፣ መግነጢስን፣ ሜታፊዚክስን፣ እንቅስቃሴን፣ ደስታን፣ ሥነ ግጥምን፣ ፖለቲካን፣ ሥነ ልቦናን እንዲሁም የንግግር ጥበብን አስመልክቶ ጽፏል፤ አርስቶትል ስለ ነፍስም የጻፈ ሲሆን ነፍስ ሟች እንደሆነች ያምን ነበር። በስፋት የሚታወቀው ግን ከሥነ ሕይወትና ከሎጂክ ጋር በተያያዙት ሥራዎቹ ነው።

የጥንቶቹ የግሪክ ምሁራን ተፈጥሮን የሚያብራሩት ነገሮችን ካጤኑ በኋላ፣ ባገኙት እውነታ ላይ ተመሥርተው ከደረሱበት ድምዳሜ አንጻር ነበር። የማያሻማ እውነታ ብለው ባሰቡት ነገር ላይ ተመርኩዘው ነገሮችን በጥንቃቄ ካመዛዘኑ፣ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር።

ይህን ሂደት በመከተል በርካታ ትክክለኛ መደምደሚያዎች ላይ ደርሰዋል፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ፣ ጽንፈ ዓለም በሥርዓት የሚመራ ስለመሆኑ የደረሱበት መደምደሚያ ነው። ይሁንና አንድ መሠረታዊ ችግር ነበራቸው፤ ይኸውም የሚደርሱባቸው መደምደሚያዎች እነሱ በሚያዩአቸው ነገሮች ላይ ብቻ የተመሠረቱ መሆናቸው ነው፤ ይህ ደግሞ አርስቶትልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ወደ ስህተት መርቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፕላኔቶችና ከዋክብት በምድር ዙሪያ እንደሚሽከረከሩ ያምኑ ነበር። በወቅቱ ይህ ሐሳብ በግልጽ የሚታይ እውነታ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ዘ ክሎዚንግ ኦቭ ዘ ዌስተርን ማይንድ የተባለው መጽሐፍ “ነገሮችን በማመዛዘንም ሆነ በሚታዩ ነገሮች ላይ ተመሥርቶ የተደረሰበት ድምዳሜ፣ ምድር የጽንፈ ዓለም እምብርት እንደሆነች የሚገልጸውን የግሪካውያን አመለካከት ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ይመስል ነበር” ይላል።

ይህ የተሳሳተ አመለካከት ተጽዕኖ ያሳደረው በሳይንሱ ዓለም ላይ ብቻ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ብዙም አሳሳቢ አይሆንም ነበር። ተጽዕኖው ግን በዚያ አልተወሰነም።

የካቶሊክ ሃይማኖት የአርስቶትልን ትምህርት ተቀበለ

በመካከለኛው ዘመን፣ ክርስቲያን እንደሆኑ በሚናገሩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ የአርስቶትል ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ ተደርገው ተቀባይነት አግኝተው ነበር። የሮም ካቶሊክ የሃይማኖት ምሁራን፣ በተለይም ደግሞ ቶማስ አኩዋይነስ (1224-1274 ገደማ) የአርስቶትልን ጽሑፎች በሃይማኖት ትምህርታቸው ውስጥ አካተውት ነበር። በመሆኑም ምድር እንደማትንቀሳቀስና የጽንፈ ዓለም እምብርት እንደሆነች የሚገልጸው የአርስቶትል ትምህርት የካቶሊክ ቀኖና ሆነ። እንደ ካልቪን እና ሉተር ያሉት የፕሮቴስታንት መሪዎችም ይህን ትምህርት የተቀበሉ ሲሆን ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ይናገሩ ነበር።—“ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ተረድተውታል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አንዳንድ የአርስቶትል ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ ተደርገው ተቀባይነት አግኝተው ነበር

ቻርልስ ፍሪማን የተባሉት ጸሐፊ “በአንዳንድ ትምህርቶች ረገድ [የአርስቶትልን አመለካከት] ከካቶሊክ ሃይማኖት ትምህርቶች መለየት አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር” በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም አኩዋይነስ፣ አርስቶትልን የካቶሊክ እምነት ተከታይ አድርጎ ‘እንዳጠመቀው’ ይነገር ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን “የአርስቶትልን ትምህርቶች መከተል የጀመረው አኩዋይነስ ነበር” በማለት ፍሪማን ጽፈዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም ጭምር በተወሰነ መጠን የአርስቶትልን ትምህርት መከተል ጀምራ ነበር ማለት ይቻላል። በመሆኑም ጣሊያናዊው የሥነ ፈለክ ተመራማሪና የሒሳብ ሊቅ ጋሊልዮ፣ ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደምትሽከረከር የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሲያቀርብ ኢንኩዊዚሽን በተባለው የካቶሊክ ችሎት ፊት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን የሚያምንበትን ነገር እንዲክድ ተገድዷል። * የሚገርመው ነገር አርስቶትል፣ ሳይንሳዊ እውቀት በጊዜ ሂደት እየተሻሻለ እንደሚሄድና አንዳንድ ጊዜም መስተካከል እንደሚያስፈልገው ይቀበል ነበር። አብያተ ክርስቲያናቱም ተመሳሳይ አመለካከት ቢኖራቸው ምንኛ ጥሩ ይሆን ነበር!

^ አን.11 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሰኔ 2003 ንቁ! ላይ የወጣውን “የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት” የሚል ርዕስ ተመልከት።